photo_2024-03-25_15-21-25

መጋቢት 16፤2016 – በቤንች ሸኮ ዞን በዝሆነ በሽታ ለተጠቁ ከ200 በላይ ሰዎች ህክምና መሰጠቱ ተነገረ

 

በቤንች ሸኮ ዞን በሼይቤንች ወረዳ በሁሉም ጤና ጣቢያዎች በዝሆነ በሽታ ለተጠቁት የህብረተሰብ ክፍሎች የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል ።

የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት በጽህፈት ቤቱ ስር በሚገኙ ስድስት ጤና ጣቢያዎች በዝሆነ በሽታ ለተጠቁ ሰዎች የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ በወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት የእናቶችና ህፃናት ቡድን መሪ አ/ቶ ሰለሞን ሀይለማሪያም ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ።

ለተጠቃሚዎች የህክምና አገልግሎቱን ለመስጠት ከወረዳው የተውጣጡ የህክምና ባለሙያዎች ስልጠና መውሰዳቸው አንስተዋል ።  በዚህም መሠረት ህክምናው በተጠናከረ ሁኔታ ተሰጥቶ ከ200 በላይ ሰዎች አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልፀዋል ።

በቀጣይም የሚሰጠው ህክምና የሚቀጥል መሆኑና አገልሎቱ ለተሰጣቸው የሚደረገው ክትትል ቀጣይነትም ያለው ነው ብለዋል ። የተደረጉ ድጋፎች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን የዝሆነ በሽታ በስፋት በመኖሩ እንዲሁም በሽታው እግር ላይ የሚከሰት በመሆኑ በዚሁ በሽታ ለተጠቁ ሰዎች የሚሆን የጫማ ግባት ችግር እንዳለ ተጠቁሟል ።

አያይዘውም በሽታው በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠው ያነሱት አ/ቶ ሰለሞን በተለይም ተጠቂዎች ከፈጣሪ እንደሆነም የማሰብ ሁኔታም እንዳለ ተናግረዋል ።

በአበረ ስሜነህ

photo_2024-03-25_15-20-59 (2)

መጋቢት 16፤2016 – በጋዛ የሚፈጸመውን ጥቃት በመቃወም የረሃብ አድማ በማድረግ ላይ የነበረች ካናዳዊት ተማሪ ራሷን ሳተች

 

ተማሪዋ የምትማርበት ማክጊል ዩኒቨርሲቲ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ በሚያቀርቡ ኩባንያዎችን በመቃወም ለ34 ቀናት የረሃብ አድማ ካደረገች በኋላ ነው ራሷን የሳተችው፡፡

በሞንትሪያል በሚገኘው የማክጊል ዩኒቨርሲቲ የምትማረው ራኒያ አሚን ራሷን ከሳተች በኋላ አሁን በሆስፒታል ውስጥ  ክትትል ላይ እንደሆነች ሚድል ኢስት አይ ዘግቧል። አሚን፣ ማክጊል ዩኒቨርሲቲ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ከሚያቀርቡ ኩባንያዎች ራሱን እንዲያርቅ ግፊት ለማድረግ የረሃብ አድማ ከጀመሩ የተማሪዎች ቡድን አንዷ ናት።

በረሃብ አድማው 17 የሚደርሱ ተማሪዎች እየተሳተፉ ነው። እርሷ ከሌሎቹ በተለየ የረሀብ አድማውን ጠንከር አድርጋ ስትገፋበት ቆይታለች፡፡የማክጊል ዩኒቨርስቲ ድረ-ገጽ እንደሚያሳየው ተቋሙ ሎክሂድ ማርቲን በተባለ የኤሮስፔስ እና የጦር መሳሪያ አምራች ላይ የአክስዮን ድርሻ አለው፡፡ ይህ ኩባንያ ለእስራኤል ተዋጊ ጄቶችን በማቅረብ ይታወቃል፡፡

ሌላኛው ዩኒቨርስቲው ገንዘቡን ያፈሰሰበት ድርክት ሳፋራን የተባለ የፈረንሳይ የጦር መሳሪያ አምራች ነው። ይህም ኩባንያ ለቴልአቪቭ መሳሪያ ከሚያቀርቡት መሀል ይገኝበታል፡፡ተማሪዎቹ እንደሚሉት ማክጊል ዩኒቨርሲቲ 20 ሚሊዮን ዶላር በጦር መሳሪያ አምራቾች እና ሌሎች ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ባላቸው ኩባንያዎች ላይ ፈሰስ አድርጓል። እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ መጠነ-ሰፊ የሆነ ጥቃትን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከ32,000 በላይ የጋዛ ነዋሪዎች መገደላቸውን ተከትሎ በዓለም ዙሪያ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ተቃውሞዎች እየተካሄዱ ናቸው፡፡

አሚን “የማክጊል ዩኒቨርሲቲ ምንም አይነት አማራጭ አላስቀረንም፡፡ ምክንያቱም ሰላማዊ ተቃውሞዎችን፣  ችላ ተብሏል” ስትል ወድቃ ሆስፒታል ከመግባቷ በፊት ለዘ-ጋርዲያን ተናግራለች። “ማክጊል በመጨረሻ ይህንን ከባድ እርምጃ እንድንወስድ አድርጎናል፡፡ የመማሪያ ገንዘባችንን በዚህ መንገድ ኢንቨስት ለማድረግ መጠቀማቸው በፍጹም ተቀባይነት የለውም” ስትልም አክላለች።

ባለፈው ህዳር የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች በጋራ ተፈራርመው ድርጊቱ እንዲቆም ቢጠይቁም፣ ማክጊል ግን ከኩባንያዎቹ ገንዘቡን ለማውጣት ፈቃደኛ አልሆነም።

በሳምራዊት ስዩም

photo_2024-03-25_15-20-19

መጋቢት 16፤2016 – ኢትዮጵያ ባለፏት ስድስት ወራት ከእንጆሪ ሽያጭ ከ3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች

 

ኢትዮጵያ ባለፏት ስድስት ወራት ለውጪ ገበያ ካቀረበችው የእንጆሪ ምርት ሽያጭ 3 ሚሊዮን 1 መቶ 91 ነጥብ 84 የአሜሪካን ዶላር ገቢ አግኝታለች ሲል የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሚኒስቴሩ የግብርና ኢንቨስትመንት እና ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈጳሚ አቶ ደረጄ አበበ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የእንጆሪ ምርት በበርካታ የአለም ሀገራት ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጥቷል።

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት  ለውጪ ገበያ ከቀረቡት የተለያዮ የፍራፍሬ አይነቶች መካከል  ትልቁን ገቢ በማስገኘት በኩል የእንጆሪ ምርት  ቀዳሚው ነው ሲሉ  ተናግረዋል።ባለፏት ስድስት ወራት ከፍራፍሬ  የውጪ ንግድ  7 ነጥብ 44  ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር  መገኘቱን መሪ ስራ አስፈጻሚው ገልፀው  የእንጆሪ ምርት ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።

በዚህም በበጀት አመቱ ግማሽ አመት ወደ ውጪ ሀገራት ከተላኩት የፍራፍሬ ምርቶች ውስጥ ከእንጆሪ ምርት ብቻ  ከ3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል ያሉት አቶ ደረጄ በዋናነት ምርቱ ወደ ተለያዮ የአውሮፓ፣  ፣ኤዥያ እና አፍሪካ ሀገራት መላኩን ተናግረዋል።

የገበያ መዳረሻ ከሆኑት ሀገራት መካከልም ጀርመን፣ጋና፣ጋቦን ፣ሴራሊዮን፣ኢኳቶሪያል ጊኒ፣እንዲሁም ኔዘርላንድ ተጠቃሾች ናቸው ተብሏል።የሆለታ እንጆሪ ከሌሎች ሀገራት በጣእሙ ተወዳጅ በመሆኑ በተለይም  በአውሮፓና አሜሪካ ላይ ምርቱ ያለው ተፈላጊነት ከፍተኛ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ይህን ፍላጎት ተከትሎ ባለሀብቶች ሆለታ ላይ የእንጆሪ ምርትን እያመረቱ እንደሚገኙ የተናገሩት መሪ ስራ አስፈጳሚው  ይህም ምርቱን በብዛት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ አስተዋጵኦ አድርጓል ነው ያሉት ።

ምርቱን በቀጥታ አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡ በርካታ አምራችና ላኪዎች  በዘርፉ መሰማራታቸውን ገልፀዋል።ይሁን እንጂ ባለሀብቶቹ ምርቱን ከዚህ በበለጠ በተሻለ ለማምረትና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ፍላጎት ቢኖራቸውም  የማስፋፊያ ጥያቄ እንደሚያነሱ ተገልጻል።

በዘርፏ የተሰማሩ አምራችና ላኪዎች ምርቱን በብዛት አቅርበው ለገበያ የሚያቀርቡበትን መንገዶች የማመቻቸት እና  ከማስፋፊያ ስራ ጋር ተያይዞ ለሚያነሱአቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት  ጥረት እንደሚደረግ ሚኒስቴሩ ገልጻዋል።

በቅድስት ደጀኔ

photo_2024-03-21_21-11-57

መጋቢት 12፤2016 – የታመመ መስሎ መንገድ ዳር በመተኛት የመኪና ስፖኪዮ የሰረቀን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ

 

ተጠርጣሪው ያሬድ ሳሙኤል ይባላል መተዳደሪያውን ጎዳና ላይ ያደረገ ሲሆን በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 2 በተለምዶ ኩኩ ሰብስቤ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የተገኘው ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም በተለያዩ ቦታዎች እየተንቀሳቀሰ ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ይፈፅም እንደነበረ  ለፖሊስ በሰጠው ቃል ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪ ያሬድ ሳሙኤል በአካባቢው ካልተመቸው ህመምተኛ መስሎ መንገድ ዳር በመተኛት ከወጪ ወራጁ ምፅዋት የሚጠይቅ ሲሆን መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ከሰው እይታ ውጪ የሆነ መስሎት ከቆመ ተሸከርካሪ ላይ የ10 ሺ ብር ዋጋ ያለው  ስፖኪዮ በመገንጠል ሰርቆለማምለጥ ሲሞክር በፖሊስ እጅ ላይ ወድቋል፡፡

ከክ/ከተማው ፖሊስ ባገኘነው መረጃ መሰረት ምርመራ የማስፋት ስራ መቀጠሉን ገልጿል፡፡
አንዳንድ ወንጀል ፈፃሚዎች በተለያዩ ቦታዎች ላይ በመንቀሳቀስ ካልተመቻቸው ችግረኛ እና ህመምተኛ በመምሰልና እርዳታ በመጠየቅ ምቹ ሁኔታ ካጋጠማቸው ደግሞ ልዩ ልዩ ወንጀሎችን እንደሚፈፅሙ ህብረተሰቡ ይወቀዉ ሲል የአዲስአበባ ፖሊስ አሳስቧል።

photo_2024-03-21_21-11-57

መጋቢት 12፤2016 -የጥቁር አንበሣ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሀሰተኛ የሜዲካል ቦርድ ሰነድ በማዘጋጀት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሲፈፅም የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ ጌቱ ደጀን ወልደአረጋይ የተባለ የጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ሠራተኛ የሆስፒታሉን ሀሰተኛ የሜዲካል ቦርድ ሰነድ በማዘጋጀት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎችን ሲፈፅም በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

 

ግለሰቡ ወደ ውጭ ሀገር በሕገ-ወጥ መንገድ ለሚሰደዱ ኢትየጵያውያን በህመም ምክንያት ከሀገር ውጭ ሄደው እንዲታከሙ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቦርድ ወስኗል የሚል ሀሰተኛ ደብዳቤ በማዘጋጀት ፣ ከኢምባሲው ስለ ትክክለኛነቱ የይጣራ ጥያቄ ሲቀርብ ሰነዱ ትክክለኛ ነው የሚል ምላሽ በመስጠት እና ባንኮች የውጭ ምንዛሬ በሀሰት ታማሚ ለተባሉ ግለሰቦች በመስጠት እንዲተባበሯቸው የሚገልፅ ደብዳቤ በመጻፍ ሕገ-ወጥ የገንዘብ እና የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሲፈጽም እንደነበረ ፖሊስ ደርሼበታለሁ ብሏል።

ተጠርጣሪው በሀሰተኛ ስም ዶ/ር አባይ ገብረስላሴ በመባል የሚጠራ ግለሰብ ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ሀገራት መሄድ ፍላጎት ያላቸውን ግለሰቦች በማፈላለግ በህመም ምክንያት ከሀገር ወጥተው እንዲታከሙ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቦርድ አመራር ወስኗል የሚል ሀሰተኛ የጥቁር አንበሣ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ደብዳቤ በማዘጋጀት ተጠርጥሮ ከመጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት መሆኑን ፖሊስ ገልጿል፡፡

ፖሊስ የፍርድ ቤት የብርበራ ትዕዛዝ አውጥቶ በተጠርጣሪው ቢሮ ውስጥ ባደረገው ብርበራ ግለሰቡ ያዘጋጃቸው ሀሰተኛ፦
1. የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ክብ ማህተም፣

2. Addis Ababa university faculty medicine ክብ ማህተም፣

3. የጤና ሣይንስ ኮሌጅ የሥነ-ምግባር እና ፀረ ሙስና መከታተያ ክፍል ክብ ማህተም፣

4. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ክብ ማህተም

5. የጤና ሚኒስቴር ክብ ማህተም፣

6. Addis Ababa university dep’t of surgical medical faculty ክብ  ማህተም፣

7. የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የራዲዮቴራፒ ሕክምና ማዕከል ክብ ማህተም፣

8. የኢ.ፌ.ዲ.ሪ አ.አ.ዩ ህክምና ፋካልቲ የጥቁር አንበሣ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ክብ  ማህተም፣

9. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና የመድሃኒት እንክብካቤ አሰተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ክብ ማህተም፣

10. የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአጥንት ቀዶ ህክምና ትምህርት ክፍል ክብ ማህተም፣

11. የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ኬዝ ቲም 11 ክብ ማኅተም
፣
12. ጤና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የዜጎች ጤና ለሀገር ብልፅግና የሚል ክብ ማህተም፣

13. HILINA TADESSE TIYO (MD) Medical service General Directorate Director General የሚል ቲተር፣ በተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የተዘጋጁ የራስጌ ማህተሞችን ፖሊስ በኤግዚቢትነት መያዙን አስታዉቋል።

ከዚህም ባሻገር ተጠርጣሪው ያዘጋጃቸው የጥቁር አንበሣ ሆስፒታል የህክምና ቦርድ የታካሚዎች ሀሰተኛ ሰነዶች፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓለም አቀፍ ባንኮች ግንኙነት መምሪያ የተዘጋጁ ሀሰተኛ ሰነዶች እና የተለያዩ የግለሰቦች ፓስፖርት እና ሌሎች የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶች በተደረገው ብርበራ የተገኙ መሆኑን ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።

photo_2024-03-03_09-33-36

የካቲት 24፤2016 – በህንድ የፖሊስ የደንብ ልብስ በመልበስ ተቆጣጣሪ በመምሰል የገዛ እህቱ ፈተና እንድትኮርጅ ያደረገው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

አንድ ህንዳዊ የፖሊስ የደንብ ልብስ በመልበስ እና የገዛ እህቱ የ12ኛ ክፍል ፈተና እንድትኮርጅ በማድረጉ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተሰምቷል። የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ፈተና በህንድ ማሃራሽትራ ግዛት ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች ከየካቲት 21 አንስቶ መስጠት ተጀምሯል። ይህ የፈተና ወቅት በህንድ አስገራሚ የኩረጃ ተግባር የሚፈፀምበት እንደሆነ የመገናኛ ብዙሃኑ መረጃ ያሳያል።

የ24 አመቱ ወጣት በፓቱር ከተማ ሻህባቡ ኡርዱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለራሱ ዓላማ ሲል ከባድ ፈተናውን እህቱ እንድታልፍ የፖሊስ ካኪ የደንብ ልብስ ለብሶ ተገኝቷል። አኑፓም ማዳን ካንዳሬ  የፖሊስ የደንብ ልብሱን በመልበስ ከመንግስት የተመደበ ተማሪዎቹን ይቆጣጠራሉ በሚል ሰበብ ወደ ፈተና ማዕከሉ ሰርጎ ለመግባት እና እህቱ ፈተናውን እንድታልፍ አስፈላጊውን መረጃ ለመስጠት አቅዷል። ነገር ግን ነገሮች እርሱ እንዳቀደው በትክክለኛው አቅጣጫ አልሄደለትም። ካንዳሬ ወደ ሻህባቡ ኡርዱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በቀላሉ መግባት ችሏል።

እቅዱን ለመፈጸም በዝግጅት ላይ ሳለ ግን አንድ ትክክለኛ የፖሊስ ተቆጣጣሪ እና የፖሊስ አባላቱ በፈተናው ደህንነት ዙሪያ መነጋገር እርሱ ወዳለበት ስፍራ ይመጣሉ። ሀሰተኛው ፖሊስ የፖሊስ ባልደረቦቹን ሰላም ለማለት ሲሞከረ ግን ወጣ ያለ ሰላምታ የሆነበይ አንዱ ፖሊስ ወዲያው ጥርጣሬውም ይገልጻል። እውነተኛዎቹ ፖሊሶች የ 24 ዓመቱን የደንብ ልብስ የለበሰውን ፖሊስ በሚገባ መመርመር ሲጀምሩ ግን  አለመጣጣም በደንብ ያስተውላሉ።

በመጀመሪያ፣ በዩኒፎርሙ ላይ ያለው ስም ትክክል እንዳልሆነ፣ ከዚያም የደንብ ልብሱ ጥራት ጉድለት እንዳለበት አይተዋል። በመቀጠል ኪሱን ሲፈትሹ የ12ኛ ደረጃ ፈተና እየወሰደች ያለችውን እህቱን ለማስኮረጅ የያዛቸውን የፈተና ወረቀት አግኝተዋል። የ24 አመቱ የውሸት ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውሎ የመንግስት ሰራተኛን በማስመሰል ወንጀል ተከሷል። አሁን ለትክንቱ ምክንያት ጊዜውን ከእስር ቤት ሊያጠፋ ይችላል።

በህንድ በአካዳሚክ ትምህርት የላቀ ደረጃ ላይ ለመድረስ አስፈላጊው የፈተና ወቅት ሲደርስ የማጭበርበር፣ የማስመሰል እና ሌላው ቀርቶ ፈተና እስከ ማሰረቅ የሚደርሱ ድርጊቶች የተለመዱ ሆነዋል። በርካቶች ስርዓቱ የሚደረገው ክትትል አፅንዖት በመስጠት እና የበለጠ ጥብቅ ፍተሻዎች እንደሚያስፈልገው ያምናሉ።

በስምኦን ደረጄ