Screenshot 2024-04-13 201651

ሚያዝያ 5፤2016 – በዲላ ከተማ ንፋስ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሁለት ሰዎች ተጎድተል

 

በዛሬዉ እለት በዲላ ከተማ ከባድ የተባለ ዝናብ መጣሉን ብስራት ሰምቷል። በጌዴኦ ዞን በዲላ ከተማ ንፋስ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያትም ሆኗል።

አደጋው የተከሰተው ዝናብ ተጠልለው ባሉት ልጆች ላይ በግንባታ ላይ ያለ አጥር ተደርምሶ ሲሆን በዚህም  የ 2 ሰዉ ህይወት ስያልፍ በ 2 ሰዉ ደግሞ ከባድ ጉዳት ማድረሱን ነዉ የዲላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ምክትል እንስፔክተር እድገት ህርባዬ መናገራቸውን ዳጉ ጆርናል የሰማዉ።

ከዚህም በተጨማሪ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን  ኢንስፔክተር እድገት ህርባዬ መናገራቸውን ብስራት የደረሰዉ መረጃ ያመላክታል።

Screenshot 2024-04-13 195833

ሚያዝያ 5፤2016 – 18 ሰዓታት በፈጀ  የቀዶ ህክምና 20 ሳ.ሜ ከፍታ ያለው የጭንቅላት እጢ በተሳካ ሁኔታ ተወገደ

 

18 ሰዓታት በፈጀ የጭንቅላት እጢ በቀዶ ህክምና ማስተካከል መቻሉን የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታውቋል።በሆስፒታሉ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አለምሰገድ ጫኔ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት  በቀዶ ህክምናው ዋና ዋና ተግባራት በጭንቅላቱ ላይ የነበረውን 20 ሳንቲሜትር ከፍታ የለው እብጠት በቀዶ ህክምና እንዲወጣ ተደርጓል ።

አያይዘውም እብጠቱ የወጣበትን ቦታ በሌላ የሰውነት ክፍል የመተካት ተግባር ተከናውኗል።በሶስተኛ ደረጃ ከታካሚው ከተለያዮ የሰውነት ክፍሎች ማለትም ከእጆቹ ላይ ደም ቅዳና ደም መልስ ተመሳሳይ ደም ስሮችን ወደጭንቅላቱ እንዲደርስ ተደርጓል  በማለት ለጣቢያችን ገልፀዋል።

በአራተኛ ደረጃ ደግሞ በቀዶ ህክምና  ወቅት በሰውነት ክፍሉ የደም መፍሰስ ችግር እንዳይኖር አስቀድሞ በቂ ደም የመያዝና  የደም ስሮችን የመቋጠር ተግባር  መከናወኑ ተገልጿል።በመጨረሻም ታካሚው ከ18 ሰአታት በኋላ በፅኑ ህሙማን ክፍል እንደቆየ ተደርጓል ያሉት አቶ አለምሰገድ በአሁኑ ሰአት  በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ ይገኛል ሲሉ ገልፀዋል።

በዚህም የተሳካ ቀዶ ህክምና የተሳተፉ የተለያዩ  ስፔሻሊስቶች ፣  ሰብ ስፔሻሊስት ሀኪሞች፣ አኒስቴትክስ፣ ነርሶች ፣ፖርተሮች እና ፅዳቶች  ሲያከናውኑ የነበሩ የቡድን አባላቶች ስራ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ  ተጠቅሷል።ዶ/ር አብዱራዛቅ  የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ስፔሻሊስት ባለሙያና የማክሮ ሰርጀሪ ሰብ ስፔሻሊስት በዚህ ህክምና ላይ ለተሳተፉ አጠቃላይ ሰራተኞች  ምስጋናቸውን  አቅርበዋል።

በቅድስት ደጀኔ

photo_2024-04-08_18-00-21

መጋቢት 30፤2016 – በኦሮሚያ ክልል በአንድ ሳምንት ውስጥ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ23 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ

 

በኦሮሚያ ክልል ከመጋቢት 23 እስከ መጋቢት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናቶች በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች የ24 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ፤ በ20 ሰዎች ላይ ከባድ እና በዘጠኝ ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡

በንብረት ላይ የደረሰዉ ዉድመት በገንዘብ ሲተመን ከ2 ሚሊየን 6መቶ ሺ ብር በላይ እንደሚገመት የኦሮሚያ ክልል የትራፊክ ቁጥጥር ክፍል ባለሙያ የሆኑት ኢንስፔክተር መሰለ አበራ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

አደጋዎቹ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ለሊቱ 8 ፡00 ሰዓት የተመዘገቡ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሞት አደጋዎች የደረሱት በጭነት ተሽከርካሪ፣በህዝብ ማመላለሻ እና በባለ ሦስት እግር (በተለምዶ ባጃጅ) የተከሰቱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የአደጋዎቹ መንስኤዎቹ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማስከርከር፣ለእግረኛ ቅድሚያ አለመስጠት፣የተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር፣ርቀትን ጠብቆ አለማሽርከር፣ ምልክቶችን አለማክበር ፣የጥንቃቄ ጉድለት መሆኑን ኢንስፔክተር መሰለ አበራ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በሳምራዊት ስዩም

photo_2024-04-08_17-58-07

መጋቢት 30፤2016 – በጣሊያን ብልት ለማስረዘም ቀዶ ህክምና የተደረገለት ግለሰብ የብልት መቆም ችግር ያጋጠመው በመሆኑ ዶክተሩ ላይ ክስ መሰረተ

 

የ40 አመቱ ጣሊያናዊ ወንድ ብልት የማሳደግ ቀዶ ህክምና ከተደረገለት በኋላ በተፈጠረበት “የአቅም ማነስ እና የብልት መቆም ችግር” ዶክተር እና ሁለት የህክምና ክሊኒኮች ላይ ክስ መስርቷል።በቱስካኒ፣ ጣሊያን ነዋሪ የሆነው ግለሰብ ለቀዶ ህክምናው 5,400 የአሜሪካን ዶላር ከፍሎ ነበር፣ ነገር ግን ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ዶክተሩን በመደወል ስለ አካላዊ ሁኔታው የደረሰበትን ቅሬታ አቅርቧል።

የጣሊያን የዜና ማሰራጫዎች ከፍርድ ቤት ሰነዶች እንደተመለከቱ ግለሰቡ በተደረገለ ሁለት ቀዶ ህክምና ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ስብ ወደ ብልቱ እንዲዛወር በማድረግ ቅርፁን እንዲያስተካክል ተደርጓል። በሚያሳዝን ሁኔታ ግብ የወንዱ ብልት የሚጠበቀው ቅርፅ እና መጠን ስላልያዘ የተፈለገውን ውጤት አላሳየም። የጣሊያን ጋዜጣ ላ ሪፑብሊካ እንደዘገበው ግለሰቡ በብልት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማስተካከል ሌሎች በርካታ ሂደቶችን አድርጓል ተብሎ ቢነገርም ነገሩን የበለጠ እንዳባባሰው ጽፏል።

በ12 የህክምና ሂደቶች ጉዳት የደረሰበት ግለሰቡ የህክምና ተቋማት ክስ ለመመስረት ወስኗል። ሐኪሙ 60 በመቶውን ካሳ እንዲከፍል የታዘዘ ሲሆን ክሊኒኮቹ እያንዳንዳቸው 20 በመቶ እንዲከፍሉ ተወስኗል። የካሳ ክፍያው 153,000 ዩሮ እንዲሆን ተወስኖ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን 110,000 ዩሮ አካባቢ ተሰጥቶታል። ምክንያቱ ደግሞ ብልቱ ላይ የደረሰው ጉዳት 30 በመቶው በራሱ ጥፋት ነው። ግለሰቡ በቤት ውስጥ ብልቱ ላይ በተመሳሳይ ሀኪም ታዝዘዋል ያላቸውን መርፌ መሰጠቱን አምኗል ይህም ፍርድ ቤቱ ለአካል ጉዳተኝነት እና ለብልት መቆም አስተዋጽኦ አድርጓል ሲል ወስኗል።

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-04-08_16-40-19

መጋቢት 30፤2016 – ከ35 ሺህ በላይ ዜጎች የምገባ አገልግሎት እያገኙ መሆኑ ተነገረ

 

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ 20 የምገባ ማዕከላት ከ35 ሺህ በላይ ዜጎች የምገባ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በዝቅተኛ ኑሩ ደረጃ የሚኖሩ እና በቀን አንድ ግዜ መመገብ ለማይችሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ስንታየው ማሞ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የተናገሩ ሲሆን ከተማ አስተዳደሩ በቀን ከ35ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በ20 የመመገቢያ መአከላት የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛልም ብለዋል፡፡

እንደከተማ ከ90 ሺ በላይ ሰዎች በቀን አንዴ መብላት አይችሉም ተብሎ እንደሚገመት እና በሂደት እነዚህን ዜጎች በምገባ አገልግሎቱ ተጠቃሚ የማድረግ ስራም እየተሰራ እንደሆነ ኤጀንሲው አስታውቃል፡፡

የምገባ ማዕከላቱ በበጎ አሳቢ ግለሰቦች እና ተቋማት ትብብር እውን መሆናቸውን ያነሱት ምክትል ዳይሬክተር ስንታየው አሁንም እነዚህ በጎ አሳቢ ሰዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው በመቀጠል በከተማዋ የሚስተዋሉትን ማህበራዊ ችግሮች በአብሮነት በመተባበር ማቃለል እንደሚቻል አንስተዋል፡፡

ኤጀንሲው በ2016 ዓ.ም በምገባ አገልግሎት በአዲስ አበባ በ477 ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ 629 በድምሩ 1ሺ አንድ መቶ ስድስት በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ለሚገኘ  ከሰባት መቶ ሺ በላይ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉን ብስራት መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በትግስት ላቀዉ

photo_2024-04-02_15-41-01

መጋቢት 23፤2016 – ወደ ጎረቤት ሀገራት በህገወጥ መንገድ ሊሰደዱ የነበሩ ከ 1 ሺህ 100 በላይ ወጣቶች ወደመጡበት አካባቢ ተመለሱ

 

የባሌ ዞንን መሸጋገሪያ በማድረግ ወደ ኬንያ እና ሶማሊያ አጎራባች ሀገራት በህገወጥ መንገድ ሲያዘዋዉሩ የነበሩ 1 ሺህ 115 ወጣቶች በቁጥጥር ስር ዉለዉ ወደመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ ተደርጓል።

በባሌ ዞን የዲንሾ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማደር እሸቱ ለማ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ፤ በዲንሾ ኬላ ላይ በተደረገ ፍተሻ እድሜያቸው ከ 18 እስከ 30 የሚገመቱ ወንዶች በህገወጥ መንገድ ወደ ምስራቅ ባሌ ፣ ቦረና እና ሶማሌ ክልል በማቅናት ወደ ኬንያ እና ሶማሊያ ለመሰደድ ሲጓዙ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ ከአራቱ የወለጋ እና የሸዋ ዞኖች እንዲሁም ከምዕራብና ምስራቅ አርሲ እና ከደብረብርሃን የመጡ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል ብለዋል።

ወጣቶቹ በህገወጥ አዘዋዋሪዎች ተታለዉና ፈቅደዉ የተጓዙ ሲሆን በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላም የተሃድሶ ስልጠና ወስደዉ ወደመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ መደረጉን የዲንሾ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማደር እሸቱ ለማ ጨምረው ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ ሙሉ በሙሉ ወንዶች ሲሆኑ አብዛኞቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ እንዳልያዙም አክለዋል። ኮማንደር እሸቱ እንዳሉት አንዳንዶቹ ተጓዦች ወደየት ሀገር እየተጓዙ መሆኑንም በቂ መረጃ የሌላቸው ነበሩ ብለዉናል። በዚህ ብዛት ደረጃ ወደ ባሌ ዞን የገቡ ህገወጥ ስደተኞች በቁጥጥር ስር ሲዉሉም ይህ የመጀመሪያው ነው።

በበረከት ሞገስ

photo_2024-04-02_15-27-46

መጋቢት 24፤2016 – የሐማስ መሪ እስማኤል ሃኒዬ እህት በእስራኤል በቁጥጥር ስር ዋለች

 

የእስራኤል ፖሊስ በደቡብ እስራኤል ባደረገው ዘመቻ የ57 አመቷን የሃማስ መሪ እስማኤል ሃኒዬህ እህት መያዙን አስታዉቋል።የእስራኤል ዜጋ የሆነችው ሳባህ አብደል ሳላም ሃኒዬህ በቴልሼቫ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋለች ሲሆን የእስራኤል የደህንነት ኤጀንሲ ሺን ቤትን ያካተተ የምርመራ ዘመቻን መደረጉን ተከትሎ ነዉ።የሃኒዬ እህት መሆኗን ያረጋገጡት የፖሊስ ቃል አቀባይ “ከሃማስ ኦፕሬተሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና ከድርጅቱ ጋር በመገናኘት በእስራኤል ውስጥ የሽብርተኝነት ድርጊቶችን በማነሳሳት እና በመደገፍ ተጠርጥራለች” ብለዋል፡፡

በቤቷ ውስጥ “በእስራኤል መንግስት ላይ ከባድ የደህንነት ጥፋቶችን የሚያሳዩ ሰነዶች፣ ሚዲያዎች፣ ስልኮች፣ ሌሎች ግኝቶች እና ማስረጃዎች”መያዙን ፖሊስ አስታዉቋል፡፡በሌላ በኩል በፈረንሣይኛ ስያሜው ኤም ኤስ ኤፍ የሚታወቀው ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን፣ በአል አቅሳ ሆስፒታል የሚሠራው ስራ እሁድ ዕለት በእስራኤል የአየር ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ሥራ ማቆሙን እና ሽፋን እየፈለገ መሆኑን አስታዉቋል፡፡

“ቡድናችን በአቅራቢያው ከፍተኛ ፍንዳታ ሲሰማ ጥቃቱ ማለቁ እስኪረጋገጥ ድረስ በሆስፒታሉ ውስጥ የነበረንን ስራ አቁመናል” ሲሉ አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል።ኤም ኤስ ኤፍ “አፋጣኝ እና ቀጣይነት ያለው” የተኩስ አቁም ጥሪውን በድጋሚ አቅርቧል።በጥቃቱ ቢያንስ አራት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 17 ሰዎች ቆስለዋል።

የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስራኤል ወታደሮቿን እና ታንኮችን ከጋዛ አል-ሺፋ የህክምና ኮምፕሌክስ ዉስጥ አውጥታለች ብሏል።ሚኒስቴሩ በደርዘን የሚቆጠሩ አስከሬኖች ከፍርስራሽ ዉስጥ ተገኝተዋል ብሏል፡፡የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ ከአል-ሺፋ ሆስፒታል የተገኙት ምስሎች “አስፈሪ እና አስደንጋጭ ናቸው” ብለዋል።‹‹ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ኃላፊነታቸውን ይወጡ ይሆን? የታወቁ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች የዚህን ግልጽ የጦር ወንጀል ስፋት በተመለከተ አለም አቀፍ ምርመራን ይደግፋሉ ወይንስ መራጭ እና አድሎአዊ ባህሪው ይቀጥላል? በማለት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ በኤክስ ገጻቸዉ ላይ አስፍረዋል፡፡

የእስራኤል ጦር በበኩሉ ከጥቅምት 7 ጥቃት ወዲህ የተገደሉበት ወታደሮች ቁጥር 600 መድረሱን አስታዉቋል፡፡

በስምኦን ደረጄ

መጋቢት 24፤2016 -የእንቦጭ አረም ለቆቃ ግድብ ደህንነት ስጋት ሆኗል ተባለ

 

የቆቃ ግድብ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቁሟል።የእንቦጭ አረም ፕሮጀክት ዋና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ኢማና ጌቱ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የእንቦጭ አረም የግድቡን ደህንነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው ይገኛል።

የቆቃ ሀይቅ ያለበትን ሁኔታ በሚመለከት ከዚሁ አረም ጫና ጋር ተያይዞ ቀድሞ የነበረው የውሀ መጠን እንዲቀንስ አድርጎታል።በግድቡ ላይ የተስፋፋውን የእንቦጭ አረም በአፋጣኝ ማስወገድ ካልተቻለ ግድቡ የጣና ሀይቅ እጣ ሊያጋጥመው ይችላል ሲሉ ፕሮፌሰሩ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

የእንቦጭ አረም በከፍተኛ ሁኔታ እራሱን መተካት የሚችል በመሆኑ ትኩረት የሚሻ ነው ያሉት ተመራማሪው ይህንን ሀይቅ ለመታደግ የተለያዮ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው ሲሉ ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።በተደረገው የምርምር ስራ የእንቦጭ አረም በሀይቁ ላይ በመስፋፋቱ ግድቡን ዘግቶታል ፣ ውሀው እንዳይተላለፍ ጫናን ስለመፍጠሩ መረዳት ተችሏል።

ይህም የውሀውን ደህንነት ስለሚጎዳው ልዮ ትኩረት ሊሰጠው እና ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል በማለት አሳስበዋል።የሀይቁን ደህንነት ለመታደግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመተባበር በቆቃ ግድብ ላይ የተስፋፋውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ የማስጀመሪያ እና የካርታ ርክክብ መርሃ ግብር በአዳማ ከተማ ማካሄዱ ተገልጿል።

በቅድስት ደጀኔ