photo_2024-06-28_16-29-46

ሰኔ  21፤2016 – በዩኒቨርስቲ ተማሪዋ ግድያ  ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በይግባኝ በእድሜ ልክ እስራት መቅጣቱን ፖሊስ አስታወቀ

የአሶሳ ዩንቨርሲቲ ተማሪ የሆነችውን ግለሰብ በጩቤ ሶስት ቦታ በጀርባዋ በመውጋት የግድያ ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣቱ ይታወሳል።

ሆኖም በይግባኝ በእድሜ ልክ እስራት መቅጣቱን በአሶሳ ከተማ አስተዳደር የወረዳ አንድ ፖሊስ አስታውቋል ።ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በግምቱ ከጧቱ 2፡45 ሰዓት አከባቢ ተከሳሽ አ/ቶ ዩሀንስ መርጋ ኢተቻ የተባለው ግለሰብ የሴት ጓደኛው የሆነችው ተማሪ ደራርቱ ለሜሳ የተባለችው ላይ ጭካኔ በተሞላበት የግድያ ወንጀል ፈፅሟል።

ተከሳሽ በፈፀመው ሰው መግደል  ወንጀል ተከሶ ከዚህ በፊት የ18 ዓመት እስራት ውሳኔ ተላልፎበት ነበር ።ይሁን እንጅ በውሳኔው ቅር የተሰኘው  የአሶሳ ከተማ አስተዳደር አቃቤ ህግ ይግባኝ በመጠየቅ የእስራቱ ውሳኔ እንዲሻሻልላቸው በጠየቀው መሠረት ጉዳዩን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሲመለከተው ቆይቷል ።

ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ሲመርምር ከቆየ በኃላ የኢ/ፌ /ድ/ሪ የወንጀል ህግ  አንቀጽ 539 /1ሀ ስር የተመለከተው  መተላለፉ ካረጋገጠ በኃላ ተከሳሹ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ በመሆኑ በይግባኝ ችሎት ሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት እሱንም ያርማል ማህበረሰቡንም ያስተምራል በማለት በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንድቀጣ ወስኗል ።

በአበረ ስሜነህ

photo_2024-06-28_16-18-00

ሰኔ  21፤2016 – በህንድ ዴሊ አየር ማረፊያ በጣለዉ ከባድ ዝናብ በጣሪያ መደርመስ የተነሳ የሰዉ ህይወት አለፈ

በዴሊ አየር ማረፊያ የጣለውን ከባድ ተከትሎ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ አራት ሰዎች ቆስለዋል።በአውሮፕላን ማረፊያው ተርሚናል 1 ላይ በቆሙ መኪኖች ላይ ጣሪያው ሲደረመስና ግዙፍ ምሰሶዎች ሲወድቅ የተሰራጩ ምስሎች አመላክተዋል፡፡ከተርሚናሉ የሚመጡ ሁሉም በረራዎች ለጊዜው ታግደው መግቢያ በሮች ተዘግተዋል።በአውሮፕላን ማረፊያው የነፍስ አድን ስራ ለተጎጂዎች የተሰራ ሲሆን ወደ ሆስፒታል ለተጨማሪ ህክምና መላካቸዉ ተሰምቷል፡፡የሕንድ አቪዬሽን ተቆጣጣሪ አየር መንገዶች ተሳፋሪዎችን በተለዋጭ በረራዎች እንዲያስተናግዱ ወይም ተመላሽ እንዲያደርጉ መክሯል።

አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ በረራዎች ከተርሚናል 1 የሚነሱ በመሆናቸው አደጋው በሺዎች በሚቆጠሩ የጉዞ እቅዶች ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል።አንዳንድ አየር መንገዶች የበረራ ስራዎችን ወደ ቀሪዎቹ ሁለት ተርሚናል ኤርፖርት ቀይረዋል።የፌደራል አቪዬሽን ሚኒስትር ራም ሞሃን ናይዱ ኪንጃራፑ ለሟች ቤተሰብ የ2 ሚሊየን ሩፒ ወይም 24 ሺ የአሜሪካን ዶላር ካሳ እንደሚከፍሉ እና ለተጎዱ ሰዎች ደግሞ 300,000 ሩፒዎች ማካካሻ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።ለጋዜጠኞችም እንደተናገሩት ሁኔታው በቁጥጥር ስር እንደሆነ እና ምንም አይነት ችግር እንዳይፈጠር የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመላዉ ሀገሪቱ ተመሳሳይ መዋቅር ያላቸው ኤርፖርቶች ላይ ፍተሻ እንደሚደረግላቸው አክለዋል።ክስተቱ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ትችት ሲሰነዘርበት የነበረ ሲሆን በርካታ ተጠቃሚዎች የአየር ማረፊያዉ ተርሚናል በቢሊዮኖች ሩፒ ወጪ ከፍተኛ እድሳት ከተደረገለት በኃላ በመጋቢት ወር በጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ተመርቋ፡፡ የቅርብ ጊዜ አጠቃላይ ምርጫ ከመጀመሩ ከአንድ ወር በፊት ምርቃት ተደርጎለታል፡፡ሆኖም ሚኒስትሩ ኪንጃራፑ የተደረመዉ የኤርፖርቱ ክፍል የታደሰው አይደለም ብለዋል፡፡በጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የተመረቀው ሕንፃ በሌላ በኩል እንደሆነ እና የፈረሰው ሕንፃ አሮጌ ሕንፃ መሆኑን እና ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡

ከትላንት ሃሙስ እለት ጀምሮ ከባድ ዝናብ በደልሂ ከተማ እየጣለ ይገኛል፡፡ የህንድ ዋና ከተማ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በከባድ የሙቀት መጠን ዉስጥ የቆየች በመሆኑ ዝናቡ እንደ ፋታ ተወስዷል፡፡ነገር ግን ዝናቡ ከተማዋን ትርምስ ውስጥ ከቶታል ምክንያቱ ደግሞ በርካታ መንገዶች በውሃ የተሞሉ በመሆናቸው የትራፊክ መጨናነቅን አስከትሏል።የሕንድ ሜትሮሎጂ ዲፓርትመንት እንዳስታወቀዉ በሳምንቱ መጨረሻ ከባድ ዝናብ መጣሉን እንደሚቀጥል ተንብዮአል።

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-06-28_13-31-48

ሰኔ  21፤2016 – በቦንጋ ከተማ ከተወለደች ሰባት ቀን የሞላት ህፃን ተጥላ በህይወት ተገኘች

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ አስተዳደር 01 ቀበሌ ማሪያም ቤተክርስቲያን አከባቢ ከተወለደች ሰባት ቀናት የሚሆናት ጨቅላ ህፃን ተጥላ መገኘቱን የቦንጋ ከተማ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ምክትል ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን  እንደገለፁት የአከባቢው ህብረተሰብ አመሻሽ ላይ የህፃን ድምፅ ሰምተው፤ ህፃኗን በህይወት መኖሯን ሲያረጋግጡ ለፖሊስ በማሳወቅ ወደ ህክምና ወስደዋል። የህፃኗ ጤንነት ተረጋግጦ ለቦንጋ ከተማ ሴቶችና ህፃናት የስራ ሂደት ዳይሬክቶሬት እንደተሰጠች ገልፀዋል፡፡

በከተማዉ በተደጋጋሚ ጊዜ ተወልደዉ የሚጣሉ ህፃናት እየተበራከቱ በመምጣቱ ተወልደው የሚጣሉ ህፃናት ማቆያ አለመኖሩ ችግር እንደሆነ ተገልፆል።

ከዚህ ቀደም በከተማ ዉስጥ ተወልደዉ የተጣሉ ሁለት ወንድና ሁለት ሴት ህፃናት መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን በቦንጋ ገብረፃዲቅ ሆስፒታል ትብብር በማድረግ በጊዜያዊነት እንዲቆዩ ተደርጓል።በጉድፈቻ ለማሳደግ የሚፈልግ ሰዉ ቦንጋ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት በአካል ቀርቦ በሕጋዊ መንገድ መውሰድ ይችላል ተብሏል፡፡

የሰባት ቀን ጨቅላ  ህፃን ልጆን  ወልዳ የጣለችዉን እናት ፖሊስ እያፈላለገ እንደሚገኝ ምክትል ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በሳምራዊት ስዩም

Capture

ሰኔ  21፤2016 – በአሜሪካ በግድያ እና የ18 ዓመቷን ግለሰብ አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ በኬሚካል መርፌ በሞት ተቀጣ

በቴክሳስ የሞት ፍርድ የተፈረደበት እስረኛ ራሚሮ ጎንዛሌስ እ.ኤ.አ በ2001 በአንዲት ወጣት ግድያ እና አስገድዶ መድፈር ወንጀል ለአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢልም በስተመጨረሻ በሞት ተቀጥቷል።

ጎንዛሌስ እሮብ እለት መሞቱ ተነግሯል። በሃንትስቪል በሚገኘው የመንግስት ማረሚያ ቤት የኬሚካል መርፌ የሞት ቅጣቱ ተፈፅሞበታል። በወንጀል ድርጊቱ የተገደለችው የ18 ዓመቷ ብሪጅት ታውንሴንድ የተባለች በደቡብ ምዕራብ ቴክሳስ የምትኖረውን ሴት አስክሬኗ በ2001 ከጠፋ ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ የተገኘ ሲሆን ተከሳሹ ተኮሶ መግደሉን አምኗል።በቴክሳስ የወንጀል ፍትህ ዲፓርትመንት በተለቀቀው መግለጫ ጎንዛሌስ ለተጎጂዋ ቤተሰብ ግድያው ከሚፈፀምበት ክፍል በመሆን ደጋግሞ ይቅርታ ጠይቋል።

እኔ በራሴ ላይ ያመጣሁት ህመም፣ የተጎዳሁት ጉዳት ከፍተኛ ነው ከምንም በላይ የነጠቅኩትን ህይወት መመለስ አልችልን የተቀበልኩት ቅጣት በቃላት መግለጽ የማልችለው ነው ብላል። ይህ ይቅርታ በቂ እንዳልሆነ ተስፋ አደርጋለሁ ሲል አክሏል። ይቅር እንድትለኝ መጸለይን አላቆምኩም እናም አንድም ቀን ይቅርታ ለመጠየቅ እድሉን አግኝቼ አላውቅም። ግን አንድ ቀን ይቅር እንደምትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ ሲል ተናግሯል።ሟች ታውንሴንድ በህይወት ብትኖር በዚህ አመት 41 ዓመቷን ትይዝ ነበር።እኤአ በጥር 2001 ከቤቷ ታፍና በጎንዛሌዝ የፆታ ጥቃት ተፈፅሞባት ተገድላለች።

ጎንዛሌዝ ሌላን ሴት በማፈን እና አስገድዶ በመድፈር በእድሜ ልክ እንዲቀጣ ከተፈረደበት በኋላ በታውንሴንድ ግድያ ወንጀለኛ መሆኑ ተደርሶበታል። የሟቿ ታውንሴንድ ወንድም ዴቪድ የጎንዛሌዝን በሞት መቀጣት ከተመለከተ በኋላ በመጨረሻ ፍትህ ሲሰጥ አይተናል ብሏል። ይህ ቀን ለቤተሰባችን ረዥሙ የስቃይ ጉዞ ያበቃበት ቀን ነው ሲል ተደምጧል። ከሁለት አስርት አመታት በላይ፣ ሊታሰብ በማይቻል ስቃይ እና የልብ ህመም አሳልፈናል ሲል ተናግሯል።ዴቪድ የጎንዛሌስ ሞት ትንሽ ሰላም ይሰጠናል ሲል ግን ደስተኛ እንዳልሆንን መናገር እፈልጋለሁ ብሏል።

የጎንዛሌስ ጠበቆች፣ ቦርዱ የሞት ፍርድን ወደ እስር ቅጣት እንዲቀይር ጠይቀው ነበር። እራሱን ለማሻሻል፣ ለማሰላሰል እና ለጸሎት በትጋት ሲደክም ነበር ፤እናም ወደ ጎልማሳ፣ ሰላማዊ፣ ደግ፣ አፍቃሪ እና ጥልቅ ሀይማኖተኛ ተቀይሬ ሲሉ ለዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥያቄ ቢያቀርቡም ውድቅ ሆኗል።በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከቴክሳስ እና ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ 11 የሀይማኖት መሪዎች ቡድን የይቅርታ ቦርዱን እና የቴክሳስ ገዥውን ግሬግ አቦትን ግድያው ውድቅ እንዲያደርጉ እና ምህረት እንዲደረግለት ጠይቀዋል።

ሆኖም የምህረት ቦርዱ የጎንዛሌስን የሞት ፍርድ ወደ እስር ለመቀየር 7 ለ 0  ድምፅ በመስጠቱ የሞት ፍርዱ ተግባራዊ ሆናል። የጎንዛሌስ ግድያ በዚህ ዓመት በቴክሳስ ሁለተኛው ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ደግሞ ስምንተኛው የሞት ቅጣት ተደርጎ ተመዝግቧል። በተመሳሳይ ሐሙስ እለት ኦክላሆማ እኤእይ በ1984 የ 7 ዓመቷን ህጻን ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈር እና ግድያ የፈፀመው ሪቻርድ ሮጀም በሞት እንዲቀጣ ቀጠሮ ተይዞለታል።

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-06-28_10-05-13

ሰኔ  21፤2016 – በጋምቤላ ወደ ጤና ተቋማት ከሚሄዱ ነፍሰጡር ሴቶች 26 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ናቸው ተባለ

በጋምቤላ ክልል በእናቶችና ህፃናት ጤና ዙሪያ የሚከሰትን ህመምና ሞት ለመከላከል የአፍላ ወጣትነት እርግዝናን መታደግ እንደሚገባ የክልሉ ጤና ቢሮ ያስታወቀ ሲሆን ያለዕድሜ ጋብቻ፣ የአፍላ ወጣቶች እርግዝና እንዲሁም በኤች አይ ቪ ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱ ተገልጿል ።

በክልሉ ጤና ተቋማት ለእርግዝና ክትትል ከሚሄዱ ነፍሰጡር ሴቶች 26 በመቶ ከ18 አመት እድሜ በታች ናቸው የተባለ ሲሆን ይህም በሴት አፍላ ወጣቶች በሚፈጸም ያለዕድሜ ጋብቻና እርግዝና በእናቶችና ህፃናት ላይ ለሚስተዋለው ህመምና ሞት ከፍተኛ ድርሻ አለው ተብሏል ።

ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የሚያስከትለው የአፍላ ወጣትነት እርግዝና እንዲሁም በኤች አይ ቪ ኤድስ የመያዝ መጠን ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር የሚከሰቱ ችግሮች የመታደግ ጉዳይ የአንድ አካል ሃላፊነት ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላትና የእያንዳንዱ ሰው የተጠናከረ ተሳትፎን እንደሚጠይቅ ተጠቁሟል ።

ወጣቶችን  ከኤች አይቪ ኤድስና ካልታቀደ እርግዝና እንዲሁም ጥንቃቄ ከጎደለው ጽንስ ማቋረጥ እና የአዕምሮ እክል ከሚፈጥሩ ነገሮች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይገባል መባሉን የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ ይጠቁማል ።

በአበረ ስሜነህ

photo_2024-06-27_12-14-50

ሰኔ  20፤2016 – አሜሪካ ፥ የኬንያ መንግስት ከሰሞኑ አጋጥሞት የነበረዉን ተቃዉሞ ያበረደበትን መንገድ አደነቀች

አሜሪካ ፥ የኬንያ መንግስት ከሰሞኑ አጋጥሞት የነበረዉን ተቃዉሞ ያበረደበትን መንገድ አድንቃለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ  አንቶኒ ብሊንከን እና የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በአፍሪካ ስላለው ሁኔታም በስልክ ተወያይተዋል ተብሏል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኬንያውን ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶን ያለውን ውጥረት ለመቀነስ የወሰዱትን ርምጃ አድንቀዉ  ከተቃዋሚዎች እና ከሲቪል ማህበረሰቡ ጋር ለመወያየት ቃል ስለገቡ ፕሬዝዳንት ሩቶ አመስግነዋል” ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ጠቅሷል።

ፕሬዚዳንት ሩቶ በመላ ሀገሪቱ ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ያስነሳና ከ 20 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን አከራካሪ የግብር ረቂቅ ህግ አንፈርምም ማለታቸዉ ይታወሳል።

የኬንያ ወጣቶች ከሰሞኑ ይህን የግብር ረቂቅ ህግን በመቃወም ተከታታይ ሰላማዊ ሰልፎችን እንዳደረጉና ከፖሊስና ጸጥታ አካላት ጋር ግጭት ዉስጥ ገብተዉ እንደነበር ይታወሳል። ተቃዉሞዉ በፈጠረዉ ጫናም መንግስት ረቂቅ ህጉን ዉድቅ አድርጎታል። በተቃዉሞዉ ከጸጥታ አካላት ጋር ግጭት ዉስጥ ከገቡ ሰዎች ዉስጥ ከ 20 በላይ ያህሉ ህይወታቸዉ አልፏል።

በበረከት ሞገስ

photo_2024-06-26_15-24-21 (2)

ሰኔ  18፤2016 – በሞተር ሳይክል እየተንቀሳቀሱ ከግለሰቦች ሞባይል በመንጠቅ ሱቅ ውስጥ ሲያከመቹ የነበሩ 4 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አቶ ሱራፌል ቢያብል   የተባሉ የግል ተበዳይ በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 14   ዋና ስራ አስፈፀሚ  ሲሆኑ   ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም  በክፍለ ከተማው  ልዩ ቦታው ኢምፔሪያል አካባቢ እየተሰራ ያለውን  የኮሪደር ልማት ስራዎችን ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ እያደረጉ በነበሩበት ወቅት 2 ተጠርጣሪዎች በጥቁር ሞተር ሳይክል ኮድ 2,A 19,21,6 ደ.ሕ( ደቡብ ህዝብ)  መልኩ ጥቁር በሆነ 1ኛ ተጠርጣሪ  እያሽከረከረ ፣ 2ኛ ተጠርጣሪ ሞተር ሳይክል ላይ ከኋላ በመሆን ከግለሰቡ  ነጥቀው በፍጥነት እያሽከረከሩ ከአካባቢው ይሰወራሉ።

የግል ተበዳይ ወንጀሉ እንደተፈፀመባቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለገርጂ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ቀርበው ያመለክታሉ ። ፖሊስም የግል ተበዳዩን አቤቱታ በመቀበል  ባደረገው ክትትል ከሁለቱ ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ ከሌቦቹ የሚረከቡ 2 ተጠርጣሪዎች  በድምሩ  4 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ህግን በተከተለ አግባብ ባደረገው ብርበራ  ተጠርጣሪዎቹ ተከራይተው የሞባይል ጥገና የሚሰሩበት ሱቅ ውስጥ በተለያየ  ጊዜ ከተለያዩ ግለሰቦች ተቀምተው የተከማቹ 32 ስማርት ሞባይል ስልኮችን በኤግዚቢት ተይዘዋል ።

የንግድ ሱቆችን በመከራየት ወንጀል የሚፈፅሙ እና የሚያስፈፅሙ ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በቁጥጥር ስር እያዋለ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል ።

ሞባይል  ስልክ  ጠፍቶብኛል የሚል ግለሰብ በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ  በአካል  በመቅረብና ትክክለኛ ማስረጃ በማቅረብ ንብረቱን መውሰድ  እንደሚችል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

photo_2024-06-25_21-52-01

ሰኔ  18፤2016 – ተሽከርካሪ ሰርቃ የተሰወረችው ግለሰብ በሰዓታት  ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለች

ተጠርጣሪዋ የስርቆት ወንጀሉን የፈፀመችው ሰኔ  17 ቀን 2016 ዓ.ም  በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ቢጫ ፎቅ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡

በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ከቤተል አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው  በወቅቱ በግምት ከጠዋቱ 12:30 ሰዓት ገደማ የግል ተበዳይ በስፍራው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B32912 አ.አ የሆነ ተሽከርካሪያቸውን  መኖሪያ ቤታቸው በር ላይ ሞተር አስነስተው እያሞቁ የነበሩ ሲሆን ወደ ስራ ለመሄድ ጃኬት ሊደርቡ ወደ ቤት በገቡበት ቅስፈት ተሽከርካሪያቸውን ከቆመበት ቦታ እንደሌለ አረጋግጠው ለፖሊስ ሪፖርት ያደርጋሉ።  የኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አቤቱታው ከደረሰው ሰዓት ጀምሮ ተሰውሮ የነበረውን ተሽከርካሪ ለማግኘት ግማሽ ቀን በፈጀ ጠንካራ ክትትልና መረጃ የማሰባሰብ ሥራ ተጠርጣሪዋን ከነተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር አውሏታል።

ግለሰቧ የግል ተበዳይ ወደቤት በገቡበት ቅስፈት ተሽከርካሪውን አስነስታ ብትሰወርም  በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ  ልዩ ቦታው ሰሚት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በግምት ከቀኑ 9 ሰዓት ገደማ ከነተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር  ውላለች ። የተለያዩ ዘዴዎችንን በመጠቀም የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ የሁሉም ስው ኃላፊነት መሆኑን ያሳሰበው ፖሊስ
የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ መኪናቸውን አቁመውና የተሽከርካሪውን ቁልፍ በውስጡ ትተው በሚሄዱበት አጋጣሚ ለተመሳሳይ የስርቆት ወንጀል ሊዳረጉ ስለሚችሉ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ  የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል ።

photo_2024-06-25_10-52-56

ሰኔ  18፤2016 – የአዕምሮ ህመምተኛ በመምሰል እና ሌሎች ዘዴዎችን በመፈፀም የመኪና ዕቃ ሰርቀዋል የተባሉ ሁለት ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ ተያዙ

አንደኛው ግለሰብ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥሮ  በፍርድ ቤት በዋስትና የተለቀቀ መሆኑ ተነግሯል

የመኪና ዕቃ ስርቆትና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል ፖሊስ እያከናወነው ያለው ተግባር ምቹ ሁኔታ ያሳጣቸው አንዳንድ ወንጀል ፈፃሚዎች ከፖሊስ ጥርጣሬ ውጪ ለመሆን በማሰብ የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ ወንጀል ለመፈፀም እንደሚንቀሳቀሱ የአዲስአበባ ፖሊስ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ 02  ነዋሪ መሆኑን በኪሱ ውስጥ የተገኘው የነዋሪነት መታወቂያ የሚያስረዳው አንደኛው ተጠርጣሪ የአዕምሮ ህመምተኛ መስሎ እየተንቀሳቀሰ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ፊጋ አካባቢ መሲ ህንፃ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ  ቆሞ ከነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2- C34174 አ.አ ከሆነ ተሽከርካሪ ላይ የግራ ስፖኪዮ መስታወት ነቅሎ ለማምለጥ ሲሞክር እጅ ከፍንጅ እንደተያዘ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሲ.ኤም.ሲ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር  አባይ ወርቁ  ገልፀዋል፡፡

እራሱን  የአዕምሮ ህመምተኛ በማስመሰል ከተጠያቂነት ለማምለጥ ጥረት አድርጎ ያልተሳካለት ይኸው ግለሰብ  ሚያዚያ 3 ቀን 2016 ዓ/ም  በዚሁ ክፍለ ወረዳ 8 ሰሚት ሳፋሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የዋጋ ግምቱ 60 ሺ ብር የሚያወጣ የተሽከርካሪ ስፖኪዮ ሰርቆ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በፍርድ ቤት በመዋስትና መለቀቁን እና የተለያዩ ስሞችን እንደሚጠቀም ኢንስፔክተር አባይ አስረድተዋል፡፡

በተጠርጣው ላይ የምርመራ መዝገብ ተደራጅቶ ጉዳዩ በህግ አግባብ እየታየ እንደሚገኝም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና አንዲት ግለሰብ ቤተ ክርስቲያን የመጣች በመምሰል ነጠላ ለብሳ የመኪና ዕቃ ስርቆት ስትፈፅም እጅ ከፍንጅ ተይዛለች፡፡ ተጠርጣሪዋ ወንጀሉን ፈፅማለች የተባለው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ነው ብሏል ፖሊስ፡፡

በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ከቤተል አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው እሌኒ ታደሰ የተባለችው ግለሰብ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ/ም ከቀኑ 8 ሰዓት ገደማ  ቤተክርስቲያን የመጣች በመምሰል ነጠላ ለብሳ እየተንቀሳቀሰች  በአካባቢው ቆሞ ከነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ  2- C49561 አ.አ ከሆነ ተሽከርካሪ ላይ 16 ሺህ ብር የዋጋ ግምት ያለው ስፖኪዮ ነቅላ ለመሰወር ስትሞክር በፖሊስ አባላትና በህብረተሰቡ ትብብር እጅ ከፍንጅ ተይዛለች፡፡

photo_2024-06-24_06-48-38

ሰኔ  17፤2016 – በሩሲያ በቤተክርስቲያን እና ምኩራብ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ የ15 ሰዎች ህይወት አለፈ

ጥቃቱን አይኤስ መፈፀሙ ተነግሯል

በሩሲያ ሰሜን ካውካሰስ ሪፐብሊክ ዳግስታን ውስጥ በፖሊስ መኮንኖች፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ምኩራቦች ላይ በደረሰ ጥቃት የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፏል። በጴንጤቆስጤ የሩሲያ ኦርቶዶክስ በዓል ላይ ታጣቂዎች በደርቤንት እና ማካችካላ ከተሞች ላይ ጥቃት አድርሰዋል። ከሟቾቹ መካከል ቢያንስ 15 የፖሊስ አባላት፣ ቄስ እና የጥበቃ ሰራተኛ ይገኙበታል። ከአጥቂዎቹ መካከል ስድስቱ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ፖሊስ ሌሎችን እያደነ ይገኛል።

የአጥቂዎቹ ማንነት ባይታወቅም በዳጌስታን ከዚህ ቀደም ተከታታይ ጥቃቶች ሲደርሱ ቆይቷል።በእሁዱ ጥቃት ሁለት አብያተ ክርስቲያናት እና ሁለት ምኩራቦች ኢላማ ተደርገዋል። የዳግስታን ትልቋ ከተማ በሆነችው በማካችካላ አንድ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ተገድለዋል።15 ፖሊሶች በጥቃቱ መገደላቸውን የዳግስታን ሪፐብሊክ መሪ ሰርጌ ሜሊኮቭ ተናግረዋል። በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተለጠፉት ምስሎች እንዳሳዩት የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪዎች  ወደ ስፍራው ከመድረሳቸው በፊት ጥቁር ልብስ የለበሱ ሰዎች በፖሊስ ተሽከርካሪ ላይ ሲተኩሱ ያሳያል።

በቴሌግራም የመልእክት መላላኪያ መተግበሪያ ላይ ያለ ይፋዊ ባልሆነ ገፅ ማሽ ታጣቂዎች በደርቤንት በሚገኝ ህንፃ ውስጥ እንደነበሩ ተነግሯል። በሰርጎካል መንደር የፖሊስ መኪና ጥቃት ደርሶበታል።ዳግስታን በጣም ድሃ ከሆኑት የሩስያ ክፍሎች አንዷ ስትሆን አናሳ ክርስቲያኖች መኖሪያ ነች። እ.ኤ.አ. ከ 2007 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት የካውካሰስ ኢሚሬትስ የተባለ ቡድን በዳግስታን እና በአጎራባች የሩሲያ ሪፑብሊኮች በቼችኒያ ፣ኢንጉሼቲያ እና ካባርዲኖ-ባልካሪያ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወሳል።

በመጋቢት ወር በሞስኮ አቅራቢያ በሚገኘው ክሮከስ ከተማ አዳራሽ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ፣ የአይኤስ ቡድን ድርጊቱን ስለ መፈፀሙ ኃላፊነቱን ቢወስድም የመንግስት ባለስልጣናት ግን ለጥቃቱ ጥፋተኛ ሲሉ ጣታቸውን በዩክሬን እና በምዕራቡ ዓለም ላይ ቀስረዋል። በወቅቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ሩሲያ በአክራሪ የአሸባሪዎች ጥቃት ዒላማ ልትሆን አትችልም” ምክንያቱም “በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ልዩነት እና በሃይማኖቶች እና በጎሳ መካከል ያለውን አንድነት የሚያሳይ ልዩ ተምሳሌት ነው” ብለው አጥብቀው ተናግረው ነበር። ከሶስት ወራት በፊት የሩሲያ የሀገር ውስጥ ደህንነት አገልግሎት ኤፍ.ኤስ.ቢ በሞስኮ ምኩራብ ላይ ጥቃት ለማድረስ የአይኤስ ሴራ ማክሸፉን ማስታወቁ ይታወሳል።

በስምኦን ደረጄ