በምዕራብ አርሲ ዞን ወንዶ ወረዳ ከበቆሎ እርሻ ዉስጥ ከበቆሎ ጋር የተዘራ አደንዛዥ እፅ እንዲወገድ መደረጉን የወንዶ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ገለፀ።
የወንዶ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ኑሩ ጃርሶ ለብስራት ቴሌቬዥንና ራዲዮ እንደገለፁት በበቆሎ እርሻ ዉስጥ ከበቆሎ ጋር ተደባልቆ የተዘራ አደንዛዥ እፅ እንዲወገድ የተደረገዉ ህብረተሰቡ ለፖሊስ በሰጠዉ ጥቆማ መሆኑን ገልፀዋል።
በሻሸመኔ ዙሪያ በሻላና በወንዶ ገነት አካባቢ አርሶ አደሩ ከሰብል ምርቶች ጋራ በመቀላቀል ሀሽሽን በድብቅ ዘርቶ እንዲያበቅል የተደረገ በመሆኑ ማህበረሰቡ እራሱ ባደረገዉ ዉይይት ሀሽሽን ከአዝዕርት ጋራ ቀላቅሎ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ከበድ ያለ ዉሳኔ እዲተላለፍባቸዉ መወሰኑን ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም አንዳንድ አርሶ አደርች ሀሽሽን ከሚያዘዋዉሩ ነጋዴዎችና ደላሎች በመታለል ከዲርጊቱ ያልተቆጠቡ በመሆናቸዉ ስር ነቀል ልዉጥ ለማምጣት ሰፊ እርምጃና የማነቃቂያ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ምክትል ኢንስፔክተር ኑሩ ጃርሶ ጨምረዉ ተናግረዋል።
በበቀለ ጌታሁን