በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ደደር ወረዳ ቼካ ቀበሌ ከባለቤቱ የተላከለትን የእስር ማዘዣ አልቀበልም በማለቱ ደብድበው ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረጉት ግለሰቦች በእስራት መቀጣታቸውን የደደር ወረዳ ፖሊስ አስታውቋል።
አልየ ሃምዳ የተባለው ግለሰብ ከባለቤቱ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሁለት ልጆቿን ይዛ ከቤት መውጣቷን እንዲሁም የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይሁን እና ባለቤቱ ከቤት ከወጣች በኋላ የገንዘብ ችግር ያጋጥማታል፡፡ በዚህም ሰዓት ንብረቴን ትካፈለኛለች በማለት ንብቱን ማሸሽ ፣ መሸጥ ፣ መለወጥ ጅምሮ እንደነበር የደደር ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ግዛቸው ተፈራ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በፍርድ ቤት የወጣውን የንብረት እግድ የያዘ የትዕዛዝ ደብዳቤ ለማድረስ የአካባቢው የጸጥታ አካላት የሆኑት አብዱልዓማን የሱፍ ፣ ጀማል አቡበከር ፣ ጃፋር ሶፊያን ትእዛዙን ለማድረስ ወደ ተጎጂው መኖሪያ ቤቱ ያመራሉ ። ነገር ግን ትዕዛዙን አልቀበልም በሚል በመካከላቸው ግጭት ይፈጠራል ።
ሶስቱ ግለሰቦች አልታዘዘንም በማለት ወደ ቀበሌ ጽ /ቤት ለመውሰድ ሲሞክሩ አልሄድም እንዳለቸው ቃላቸውን ለፖሊስ ሰጥተዋል። የተፈጠረው ግጭት ከቃላት አልፎ ወደ ዱላ ይቀየር እና በያዙት ዱላ ጆሮ ግንዱን መተው እጅ እና እግሩን አስረው ወደ ቀበሌ ጽ/ቤት ይወስዱታል፡፡
ወደ ቀበሌ ጽ/ቤት ሲደርስ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረ በመሆኑ ወዲያው ወደ ህይወት ፋና ሆስፒታል ይወስዱታል፡፡ ለሁለት ቀናት የህክምና ክትትል ሲደግለት ቢቆይም ህይወቱ ማትረፍ አልተቻለም፡፡
ሶስቱ ግለሰቦችም የተሰጣቸውን ስልጣን በመጠቀም አላግባብ በኃይል በታገዝ መንገድ ሰው ለመያዝ በመሞከር እና በመደብደብ ወንጀል ዓቃቢ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው የምስራቅ ሀረረጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ተከሳሾችን ጥፋተኛ በማለት እያንዳንዳቸውን በስምንት ዓመት ከስድስት ወር እስራት እና በአራት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ቅጣት የወሰነባቸው መሆኑን ኢንስፔክተር ግዛቸው ተፈራ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡
በኤደን ሽመልስ