በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ በተጫዋችነት፣ ጋዜጠኝነት እና በመፅሐፍ ደራሲነት ለረጅም ዓመታት ያገለገለው ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ባደረበት ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም ንጋት ላይ ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል።
ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) በእግር ኳስ ተጫዋችነት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ጨምሮ ለሌሎች ክለቦችም ተጫውቷል። ከተጫዋችነት ከተገለለ በኋላ ከ30 ዓመታት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት አሳልፏል፡፡በበርካቶች ዘንድ”ተንቀሳቃሹ ቤተ መፅሐፍት”የሚል ቅፅል ስም የተሰጠው ገነነ መኩርያ ኢህአፓና ስፖርት”1፣ 2፣ 3፣ ሊብሮ፣ እና ፍትሃዊ የጠጅ ክፍፍል የሚሉትን ጨምሮ ስምንት ያህል መፅሐፍትንም ለንባብ አብቅቷል።
ገነነ መኩርያ ሊብሮ” የተሰኘ ጋዜጣንም ለረጅም ዓመታት ለአንባቢው አድርሷል። በተጨማሪም በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው በተወዳጁ ብስራት ኤፍ ኤም 101.1 “መሴ ሪዞርት” እና ሌሎች ዝግጅቶች ላይ ታሪክና ስፖርትን አዋህዶ ሲያቀርብ ቆይቷል። ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ለእግር ኳሱ ላበረከተው የላቀ አስተዋፅኦም በአዲስ አበባ በተሰናዳው የካፍ ኮንግረስ ላይ የረጅም ዘመን አግልግሎት ሜዳይ ተበርክቶለታል።
ካፍ በ2009 ዓ.ም የ60 ዓመት ጎንደል ኦፍ ሜሪት የሸለመው ሲሆን፤ ስድስት ጋዜጠኞች ብቻ ያገኙትን ሽልማት በመውሰድ ገነነ ከምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው እንደሆነም ይነገራል። ጋዜጠኛው መጋቢት 5 ቀን 1957 ዓ.ም በይርጋለም ከተማ እንደተወለደ ሲሆን፤ እድገቱ ደግሞ በሻሸመኔ ከተማ እንደሆነ የህይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ስርዓተ ቀብሩ በዛሬዉ እለት ጥር 15 ቀን በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ቤተሰብ ፣ወዳጅ ዘመድና የሙያ ዘጋሮቹና አድናቂዎቹ በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡
ብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን በአንጋፋዉ ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ(ሊብሮ) የተሰማዉን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ መጽናናትን ይመኛል፡፡

2 Responses