ኬንያ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቃሚ ማዕድን የሆነዉን ኮልታን ማግኘቷን የሀገሪቱ የማዕድን ሚኒስትሩ አስታዉቀዋል፡፡
ብርቅዬው ማዕድን የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪዎች፣ ሞባይል ስልኮች እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ለማምረት ያገለግላል።ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዓለም የኮልታን ክምችት የያዘች ሀገር እንደሆነች ይታወቃል፡፡
ይህ ሀብት ግን ለኮንጎ ከበረከትይልቅ እርግማን ሆኖባት ለአስርት አመታት ማዕድኑ በሚገኝበት በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የትጥቅ ግጭት እንዲባባስ አድርጓል።በኬንያ የሚገኙት የኮልታን ክምችቶች ምን ያህል እንደሆኑ ግን ግልጽ አይደለም::የማዕድን ባለስልጣናት ቀደም ሲል ኬንያ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ማዕድን ሊኖራት እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዉ ነበር፡፡
የኬንያ የማዕድን፣ የሰማያዊ ኢኮኖሚ እና የባህር ጉዳዮች ሚኒስትር ሳሊም ምቩርያ እንደተናገሩት ኬንያ የኮልታን ክምችት እንዳላት “አሁን ይፋ ሆኗል” ብለዋል።የማእድኑ ሀብቱ በሀገሪቱ በስድስት ክልሎች ውስጥ ተገኝቷል::ነገር ግን የክምችቱን መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
የማዕድኑ ክምችት ካላቸው ስድስት አውራጃዎች አንዱ የሆነው በምስራቅ ኬንያ የሚገኘው የኢምቡ ክልል ነዋሪዎች መሬታቸውን ከመሸጥ እንዲቆጠቡ ምክር ተለግሷቸዋል፡፡የክልሉ የፓርላማ አባል የሆኑት ነባርት ሙሪዩኪ ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት “ውድ የሆነ ማዕድን ተገኝቷል እና ጥቅም ለማግኘት ከፈለጋችሁ መሬታችሁን አትሽጡ” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ምቩርያ እንዳሉት ግኝቱ ተጨማሪ የስራ እድል ይፈጥራል እንዲሁም የየኬንያን ማዕድን ኢንዱስትሪ ያሰፋል ብለዋል።
የማዕድን ቁፋሮ ከኬንያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ከ1 በመቶ በታች ቢሆንም እስከ 10 በመቶ ለማዋጣት የሚያስችል አቅም እንዳለው የኬንያ ብሄራዊ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ገልጿል።ኮልታን ብዙውን ጊዜ በብረታ ብረት ታንታለም ውስጥ ይጣራል ፡፡ከዚያም የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ለማምረት ያገለግላል፡፡የኮልታን ዋጋ ምን በያዘዉ ታንታለም መሰረት ይወሰናል፡ ነገርግን በአማካይ አንድ ኪሎ ግራም ማዕድኑ 48 ዶላር ያስገኛል ሲል ፎርብስ ዘግቧል።
ተንታኞች እንደሚናገሩት ዓለም አቀፉ የኮልታን ፍላጎት በፍጥነት እያደገ ሲሆን በምስራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ለተፈጠረው ግጭት መንስኤ ከሆኑት መካከል አንዱ ተቀናቃኝ ሚሊሻዎች ኮልታን እና ሌሎች ጠቃሚ ማዕድናትን የሚያመርቱ ስፍራዎችን ለመቆጣጠር በመፈለጋቸዉ የተነሳ ነው፡፡ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከጎረቤቷ ሩዋንዳ ጋር በመሆን በዓለማችን ከፍተኛ የኮልታን አቅራቢ ሀገራት የሚለዉን ስም ይዘዋል፡፡
በስምኦን ደረጄ
2 Responses