በባሌ ዞን ጋስራ ወረዳ የጋሰራ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሰራተኛ ናት በማለት ደሞዝ ሲከፍሉ የነበሩ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ።
ለስምንት ወራት ወርሃዊ ደሞዝ ሲከፍሉ የነበሩት የጋሰራ ወረዳ የፋይናንስ ኃለፊዎች እና ተባባሪዎች በእስራት መቀጣታቸውን የጋሰራ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል ምርምራ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር መሃመድ ሃጂ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
አንደኛ ተከሳሽ የጋሰራ ወረዳ ፋይናንስ ጽ/ቤት የሂሳብ ሰራተኛ የሆነው ሀሰን አብዱል ቃድር የተባለው ግለሰብ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ የተከሳሿ ባለቤት የሆነዉ የጋስራ ጽ/ቤት ሰራተኛ ፣ ሶስተኛ ተከሳሽ የሁለተኛ ተከሳሽ ባለቤት የሆነችዉ ወ/ሮ መስታዉት ፣ አራተኛ ተከሳሽ አሰፋ ንጋቱ የወረዳዉ ትምህርት ቤቶች መምህራን ሃላፊ እና አምስተኛ ተካሳሽ የማዘጋጃ ቤት ሰራተኛ በመሆን ድርጊቱን መፈጸማቸው ተረጋግጧል።
ለሁለተኛ ተከሳሽ ባለቤት ለሆኑት ወይዘሮ መስታወት ተሾመ የጋስራ ወረዳ ት/ት ጽ/ቤት ሰራተኛ ናቸው በማለት በወር 8 ሺህ ብር ለስምንት ወር እንዲከፈላቸው ሲያደርጉ መቆየታቸው በማስረጃ ተረጋግጧል ። የባሌ ዞን ፖሊስ በተከሳሾች ላይ በሙስና ክስ መስርቶ ከዓቃቢ ህግ ጋር የመዝገቡን አጣርቶ ለፍርድ ቤት ይልካል።
ክሱን ሲመለከት የነበረው የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ አሰተላልፏል። 1ኛ ተከሳሽ በስምንት ዓመት እስራት እና በ20 ሺህ ብር ፣ 2ተኛ ተከሳሽ በ5 ዓመት እስራት እና በ10ሺህ ብር ፣ 3ኛተከሳሽ ያለዓግባብ ደሞዝ በመቀበል 2 ዓመት እስራት እና 5ሺህ ብር እንድትቀጣ ወስኗል፡፡
በተጨማሪም 4ተኛ ተከሳሽ በ2 ዓመት እና 5 ሺህ ብር ፣ 5ተኛ ተከሳሽ በ1 ዓመት እና በ5 ሺህ እንዲቀጡ ውሳኔ መተላለፉን ምክትል ኢንስፔክተር መሃመድ ሃጂ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
በኤደን ሽመልስ

2 Responses