በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ዳሮለቡ ወረዳ ዳዳታ ሮታ ቀበሌ በወንድሙ ትዳር ደስተኛ ያልሆነው እና መርዝ ልትሰጠኝ ሞክራለች በማለት በሜንጫ የግድያ ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በእስራት መቀጣቱ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ገልጿል ፡፡
የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ዋና ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ቱራ ለታ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን አንደተናገሩት ዘኮ አብዱላሂ የተባለው ተከሳሽ ከቤተሰቦቹ ሁሉ በተለየ ሁኔታ በሚቀርበው ወንድሙ ትዳር ደስተኛ እንዳልነበር እና በተደጋጋሚም በትዳራቸው ጣልቃ ይገባ የነበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወንድሙ ቀሽርቱ ይስባህ የተባለች ወጣት በአካባቢ ባህል መሰረት ሽማግሌ ልኮ ትዳር ቢመሰርትም ተከሳሽ ዘኮ በወንድሙ ትዳር ጣልቃ ይገባ ነበር።በዚህም ሚስት ቀሽርቱ ደስተኛ እንዳልነበረች እና ለባለቤቷም ለምን በእኛ ትዳር ጣልቃ ይገባል በእኔ እና በአንተ መካካል ችግር ካለ እኛ ራሳችን ነን መፍታት ያለብን እሱ አንተን አልፎ እንዴት ይናገረኛል ብትልም ምንም አይነት መፍትሄ ማግኘት አለመቻሏ ተጠቁሟል፡፡
ይህ ችግር ሳይፈታ ተከሳሽ ዘኮ አብዱላሂ በድንገት የጤና ችግር ይገጥመዋል። ነገር ግን ወደ ህክምና አልሄድም የወንድሜ ሚስት መርዝ አብልታኛለች ለዛ ነው የታመምኩት በሚል ቂም ይይዛል። ተከሳሽ ታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም የወንድሙን ሚስት መንገድ ላይ ጠብቆ በሜንጫ በመምታት ህይወቷ እንዲያልፍ በማድረግ ከአከባቢው ለመሰወር ይሞክራል።
ፖሊስ ተከሳሹ ድርጊቱን ከፈፀመ በኃላ ብዙም ሳይርቅ በቁጥጥር ስር አውሎት ምርመራ ማድረግ ይጀምራል።አስከሬኑ ለምርመራ ወደ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ተልኮ ከተጣራ በኋላ ዓቃቢ ህግ ክስ ይመሰርታል፡፡
የክስ መዝገቡን የተመለከተው የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምንም ማስረጃ ባልተረጋገጠበት መርዝ ያበላችኝ የወንድሜ ሚስት ናት በሚል የወንድሙን ሚስት መግደሉን ያረጋግጣል።
ተከሳሽ ጥፋተኛ መሆኑ በሰው እና በህክምና ማስረጃ በመረጋገጡ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ. ም በዋለው ችሎት በ16 ዓመት ከ6 ወር እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ያስተላለፈበት መሆኑን ኮማንደር ቱራ ለታ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡
በኤደን ሽመልስ
2 Responses