ኢትዮጵያ ባለፏት ስድስት ወራት ለውጪ ገበያ ካቀረበችው የእንጆሪ ምርት ሽያጭ 3 ሚሊዮን 1 መቶ 91 ነጥብ 84 የአሜሪካን ዶላር ገቢ አግኝታለች ሲል የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴሩ የግብርና ኢንቨስትመንት እና ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈጳሚ አቶ ደረጄ አበበ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የእንጆሪ ምርት በበርካታ የአለም ሀገራት ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጥቷል።
በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ለውጪ ገበያ ከቀረቡት የተለያዮ የፍራፍሬ አይነቶች መካከል ትልቁን ገቢ በማስገኘት በኩል የእንጆሪ ምርት ቀዳሚው ነው ሲሉ ተናግረዋል።ባለፏት ስድስት ወራት ከፍራፍሬ የውጪ ንግድ 7 ነጥብ 44 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን መሪ ስራ አስፈጻሚው ገልፀው የእንጆሪ ምርት ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።
በዚህም በበጀት አመቱ ግማሽ አመት ወደ ውጪ ሀገራት ከተላኩት የፍራፍሬ ምርቶች ውስጥ ከእንጆሪ ምርት ብቻ ከ3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል ያሉት አቶ ደረጄ በዋናነት ምርቱ ወደ ተለያዮ የአውሮፓ፣ ፣ኤዥያ እና አፍሪካ ሀገራት መላኩን ተናግረዋል።
የገበያ መዳረሻ ከሆኑት ሀገራት መካከልም ጀርመን፣ጋና፣ጋቦን ፣ሴራሊዮን፣ኢኳቶሪያል ጊኒ፣እንዲሁም ኔዘርላንድ ተጠቃሾች ናቸው ተብሏል።የሆለታ እንጆሪ ከሌሎች ሀገራት በጣእሙ ተወዳጅ በመሆኑ በተለይም በአውሮፓና አሜሪካ ላይ ምርቱ ያለው ተፈላጊነት ከፍተኛ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ይህን ፍላጎት ተከትሎ ባለሀብቶች ሆለታ ላይ የእንጆሪ ምርትን እያመረቱ እንደሚገኙ የተናገሩት መሪ ስራ አስፈጳሚው ይህም ምርቱን በብዛት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ አስተዋጵኦ አድርጓል ነው ያሉት ።
ምርቱን በቀጥታ አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡ በርካታ አምራችና ላኪዎች በዘርፉ መሰማራታቸውን ገልፀዋል።ይሁን እንጂ ባለሀብቶቹ ምርቱን ከዚህ በበለጠ በተሻለ ለማምረትና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ፍላጎት ቢኖራቸውም የማስፋፊያ ጥያቄ እንደሚያነሱ ተገልጻል።
በዘርፏ የተሰማሩ አምራችና ላኪዎች ምርቱን በብዛት አቅርበው ለገበያ የሚያቀርቡበትን መንገዶች የማመቻቸት እና ከማስፋፊያ ስራ ጋር ተያይዞ ለሚያነሱአቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ጥረት እንደሚደረግ ሚኒስቴሩ ገልጻዋል።
በቅድስት ደጀኔ

2 Responses