የቆቃ ግድብ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቁሟል።የእንቦጭ አረም ፕሮጀክት ዋና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ኢማና ጌቱ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የእንቦጭ አረም የግድቡን ደህንነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው ይገኛል።
የቆቃ ሀይቅ ያለበትን ሁኔታ በሚመለከት ከዚሁ አረም ጫና ጋር ተያይዞ ቀድሞ የነበረው የውሀ መጠን እንዲቀንስ አድርጎታል።በግድቡ ላይ የተስፋፋውን የእንቦጭ አረም በአፋጣኝ ማስወገድ ካልተቻለ ግድቡ የጣና ሀይቅ እጣ ሊያጋጥመው ይችላል ሲሉ ፕሮፌሰሩ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
የእንቦጭ አረም በከፍተኛ ሁኔታ እራሱን መተካት የሚችል በመሆኑ ትኩረት የሚሻ ነው ያሉት ተመራማሪው ይህንን ሀይቅ ለመታደግ የተለያዮ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው ሲሉ ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።በተደረገው የምርምር ስራ የእንቦጭ አረም በሀይቁ ላይ በመስፋፋቱ ግድቡን ዘግቶታል ፣ ውሀው እንዳይተላለፍ ጫናን ስለመፍጠሩ መረዳት ተችሏል።
ይህም የውሀውን ደህንነት ስለሚጎዳው ልዮ ትኩረት ሊሰጠው እና ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል በማለት አሳስበዋል።የሀይቁን ደህንነት ለመታደግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመተባበር በቆቃ ግድብ ላይ የተስፋፋውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ የማስጀመሪያ እና የካርታ ርክክብ መርሃ ግብር በአዳማ ከተማ ማካሄዱ ተገልጿል።
በቅድስት ደጀኔ
2 Responses