የተባበሩት መንግስታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ እንደገለጸው ከጥቅምት 7 ጀምሮ በጋዛ ሰርጥ ከሚገኙት ሕንፃዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በእስራኤል ጥቃቶች ወድመዋል።የተባበሩት መንግስታት የሳተላይት ማእከል መረጃን በመጥቀስ በኤክስ ላይ ባሰፈረዉ መልዕክት “በጋዛ የደረሰው ውድመት ሊገለጽ የማይችል ነው” ሲል አስታዉቋል፡፡
“ፍርስራሹን ማጽዳት ዓመታት ይወስዳል። ከዚህ ጦርነት የስነ ልቦና ጉዳት መዳን ብዙ ጊዜ ይወስዳል” ሲል አክሎ የተኩስ ማቆም ጥሪ አቅርቧል።“ይህ መከራ ማብቃት አለበት” ሲልም አሳስቧል፡፡ በሌላ በኩል በእስራኤል መንግሥት ውስጥ ያለውን ጥልቅ ክፍፍል በግልጽ ያሳያል በተባለ ውሳኔ የአገሪቱ የጦር ካቢኔ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ የአስቸኳይ ጊዜ መንግስቱን ለቀዋል።
የሚንስትሩ ውሳኔ ከጋዛ ጦርነት በኋላ ባለው ዕቅድ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር የተፈጠረው ልዩነት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።ጋንትዝ እሑድ ዕለት በቴል አቪቭ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ሲያሳውቁ ውሳኔውን “ቀልል አልነበረም” ብለዋል።”እንደ አለመታደል ሆኖ ኔታንያሁ ወደ እውነተኛው ድል እንዳንቀርብ እየከለከለን ነው። ይህም ለቀጠለው ቀውስ ማሳያ ነው” ብለዋል።በአንዳንዶች የእስራኤል ቀጣዩ ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን ዕድል እንዳላች የሚነገርላቸው ጋንትዝ፤ ኔታንያሁ የምርጫ ቀን እንዲወስኑ ጠይቀዋል።
የሃመስ መሪ ሃኒዬ ለአልጀዚራ አረብኛ በሰጡት አስተያየት የእስራኤል ጦር ካቢኔ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ የስራ መልቀቂያ በተመለከተ “ጀልባው ከመስጠሟ በፊት ለመዝለል እየሞከሩ ነው” ብለዋል።የእስራኤል ባለስልጣናት የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸዉ የእስራኤል የፖለቲካ ስርዓት “በመውደቅ” ላይ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ሃኒዬ ተደምጠዋል።
ሃኒዬ በተጨማሪም ከኔታንያሁ ዉጪ እንደ አማራጭ የሚታዩት ጋንትዝ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ምንም ልዩነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።“ሁለቱም ጥፋት የሚፈልጉ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው” ሲሉ አክለዋል፡፡
በስምኦን ደረጄ

2 Responses