photo_2024-06-13_20-22-51

ሰኔ 6፤2016 – ለዓረፋ በዓል ወደ ወራቤ የሚያቀኑ መንገደኞች እስከ አምስት እጥፍ የደረሰ ጭማሪ የተደረገበት ታሪፍ እንዲከፍሉ መገደዳቸዉን ተናገሩ

የስልጤ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ በበኩሉ ተሽከርካሪዎቹ ወራቤ ሲደርሱ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ብሏል

የፊታችን እሁድ ለሚከበረዉ የዓረፋ በዓል በርካታ ዜጎች ወደ ወራቤ እና ስልጦ ዞኖች የሚጓዙ መንገደኞች ከታሪፍ በላይ እንዲከፍሉ እየተጠየቁ መሆኑን ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ቅሬታቸዉን ለጣቢያችን የተናገሩት አንድ መንገደኛ ከአዲስአበባ ወራቤ እስከ 1 ሺህ 500 ብር እንዲከፍሉ እየተጠየቁ መሆኑን ገልፀዋል። በህጋዊ ታሪፉ መሰረት 350 ብር ገደማ ለሚጠይቀዉ መንገድ እስከ አምስት እጥፍ ጭማሪ የታየበትን ገንዘብ እንዲከፍሉ መገደዳቸዉን ገልጸዋል። ተሽከርካሪዎቹ ከመናህሪያ ዉጪ ጫኝ መሆናቸዉንም ተጓዡ ተናግረዋል።

ብስራት የስልጤ ዞን የትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ አቶ ሱልጣን ራህመቶን የጠየቀ ሲሆን ፤ መምሪያዉ ጣልቃ መግባት የማይችል ቢሆንም ተሽከርካሪዎቹ ወደ ዞኑ እና ወደ ወራቤ ከተማ ሲደርሱ ግን ግጣት እንደሚጠብቃቸው ገልጸዋል። “መንገደኞች ጥቆማ መስጠት አለባቸዉ” ያሉት አቶ ሱልጣን ፤ ከታሪፍ በላይ የከፈሉትን ገንዘብ እስከማስመለስ የደረሰ አገልግሎት እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

አንድ አሽከርካሪ ከታሪፍ በላይ ጭኖ የተገኘ እንደሆነ የ 500 ብር ቅጣት የሚጣልበት ሲሆን ይህ ደግሞ እንደክልል ደንቡ ያለዉን ክፍተት የሚያሳይ ነዉ ብለዋል። በቅርቡ ግን ክልሉ ተግባራዊ አድርጎታል ያሉት ሌላ የቅጣት ደንብ ግን ከታሪፍ በላይ ያስከፈለን አሽከርካሪ የራስ ጥቅምን በማስቀደም በሚል 2 ሺህ 500 ብር እንደሚቀጣ ደንግጓል ብለዋል። በዚህ መሰረትም አሽከርካሪዎች ፤ ተጓዦች ከታሪፍ በላይ የከፈሉትን ገንዘብ ከማስመለስ ጀምሮ ቅጣቱ እንደሚጣልባቸው አስጠንቅቀዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ተሽከርካሪ ወደ ዞኑ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት ሃላፊዉ የመንገድ መጨናነቅ እንዳይከሰትም በቂ  ዝግጅት አድርገናል ባይ ናቸዉ። መምሪያ የመጣለትን ጥቆማ ተከትሎ በአዲስአበባ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አንስተዉ ከመነሻዉ ማስተካከል የሚቻልበት አማራጭ እንዳለም የስልጤ ዞን የትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ አቶ ሱልጣን ራህመቶ ጨምረዉ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በበረከት ሞገስ

Tags: No tags

2 Responses

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *