በናይጄሪያ ሰሜናዊ ምስራቅ ክልል ውስጥ አጥፍቶ ጠፊዎች ቅዳሜ እለት በፈፀሙት በርካታ ፍንዳታዎች ቢያንስ 18 ሰዎች መገደላቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በሰሜናዊ ምስራቅ ቦርኖ ግዛት በጉዎዛ ከተማ በቀብር ሥነ ሥርዓት እና በጋብቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ የአጥፍቶ ጠፊዎች የቦምብ ፈንጂዎ ጥቃት መድረሱን የቦርኖ ግዛት የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኤጀንሲ ኃላፊ ባርኪንዶ ሳኢዱ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ሦስተኛው ፍንዳታ በናይጄሪያ-ካሜሩን ድንበር ላይ በምትገኘው ከተማ ውስጥ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ፍንዳታ ከደረሰ ከደቂቃዎች በኋላ በመንግስት ሆስፒታል አካባቢ መከሰቱን አስረድተዋል።
እስካሁን ድረስ ህጻናት፣ አዋቂ ወንድ፣ ሴት እና ነፍሰ ጡር ሴትን ጨምሮ 18 ሰዎች እስከ ሰኞ ረፋድ ድረስ ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል ሲሉ ሰኢዱ ተናግረዋል። በከባድ ጉዳት የደረሰባቸው 19 ሰዎች በግዛቱ ዋና ከተማ ማይዱጉሪ ወደሚገኝ የህዝብ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ገልፀዋል።በድምሩ 23 ሰዎች ቆስለዋል። ቦኮ ሃራም እና የአይኤስ ታጣቂ የሽብር ቡድኖች ከአስር አመታት በላይ የፈፀሙትን የሽብር ጥቃቶች በመጋፈጥ ላይ የቆየችው ናይጄሪያ በዚህ አመት እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት በአንድ ቀን ሲፈፀም የመጀመሪያው ነው።
ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኒዩ ጥቃቱን “ተስፋ የቆረጡ ኃይሎች የሽብር ድርጊቶች” ሲሉ አውግዘዋል።በግዎዛ ከተማ ለተፈፀመው ግድያ ተጠያቂ በሆኑ አካላት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀው ይህ ጥቃት በቅርብ ጊዜ በታጣቂዎች ላይ የናይጄሪያ ጦር ያገኘውን ስኬት የሚያደናቅፍ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ የግፍ ጥቃት ፈጣሪዎች ለወሰዱት እርምጃ መንግስታቸው የናይጄሪያ ህዝብ ወደ ፍርሀት፣ እንባ፣ እና ሀዘን ውስጥ እንዲገባ ስለማይፈቅድ የአፀፋ ምላሽ ይሰጣል ሲሉ አረጋግጠዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በናይጄሪያ ቦርኖ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲያቆም አሳስቧል።እነዚህ አሰቃቂ ጥቃቶች ለሰው ልጅ ህይወት ያላቸውን ንቀት ያሳያል ሲል ቡድኑ ኮንኗል። በናይጄሪያ የሚገኘው የአሜሪካ ተልዕኮ ጥቃቱን “አሰቃቂ” ሲል ገልጿል። “እነዚህ አስጸያፊ የጥቃት ድርጊቶች ጨካኝ እና ምህረት የለሽ ለሰው ሕይወት ግድየለሽነትን ያሳያሉ። እነዚህ አስጸያፊ ጥቃቶች በክልሉ ውስጥ የሽብርተኝነትን ቀጣይነት ያለው ስጋት የሚያስታውሱ ናቸው በማለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ጎዛ በ2014 በቦኮ ሃራም ቁጥጥር ስር የነበረች ሲሆን በ2015 የናይጄሪያ ጦር ድል አድርጎ ቡድኑን አባሯል። ነገር ግን ቦኮሀራም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በከተማዋ አቅራቢያ ጥቃቶችን እና አፈናዎችን ማድረጉን ቀጥሏል። በግዎዛ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች ታጣቂዎች እራሳቸውን ለማደስ እና አሁንም ጉዳት የማድረስ አቅም እንዳላቸው ለማሳየት እየሞከሩ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬን አንግቧል። ባለፈው ህዳር 20 ሰዎች በአጎራባች ዮቤ ግዛት የቀብር ስነስርዓት ጨርሰው ሲመለሱ በቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ተገድለዋል።
ጥቃቱ የተፈፀመው ታጣቂዎች በጉሮካያ መንደር ባደረጉት ወረራ 17 ሰዎችን ከገደሉ ከአንድ ቀን በኋላ የመንደሩ ነዋሪዎች የመኸር ግብር የተባለውን ግብር ለመክፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው ሲል ፖሊስ አስታውቋል።ቦኮ ሃራም በታሪክ ከነበሩት ታጣቂ ቡድኖች በበለጠ በርካታ ሴቶችን ለአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ይጠቀም እንደነበር አንድ ጥናት አመልክቷል። የቅርብ ጊዜ ቁጥሮች እንደሚጠቁሙት ቦኮ ሃራም ከሚጠቀምባቸው አጥፍቶ ጠፊዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ብዙዎች እንደሚጠቁሙት የሴቶች የአለባበስ ሁኔታ ፈንጂዎችን ለመደበቅ ቡድኑ ይጠቀምበታል።
በስምኦን ደረጄ

2 Responses