በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B48631 አ.አ በሆነ ተሽከርካሪ ወንጀል ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው፡፡ ግለሰቦቹ በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው 6 ኪሎ ዩኒቪርሲቲ አንደኛ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በፈፀሙት ወንጀል እንደተያዙ በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የመነን አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ሃላፊ ኢንስፔክተር ታዲዮስ ወ/አረጋይ ተናግረዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ባንኮች ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ እና ይህንን ወንጀል ከመፈፀማቸው በፊት በሌሎች ስድስት ባንኮች ውስጥ በመግባት ሞክረው አልተሳካለቸውም። በስተመጨረሻ ከሁለቱ አንደኛው ተጠርጣሪ 5 ኪሎ አካባቢ በሚገኝ የአንድ ባንክ ቅርንጫፍ ውስጥ በመግባት ከኤንጂኦ እንደመጣ በመግለፅ እና በድርጅቱ ስም የባንክ አካውንት ለመክፈት የፈለገ በማስመሰል ከባንኩ ስራ አስኪያጅ ጋር ይግባባል፡፡
ስራ አስኪያጁም አካውንት ለመክፈት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ይነግሩታል። ተጠርጣሪውም ፎቶን ጨምሮ ሌሎች መስፈርቶችን አሟልቶ በድጋሚ እንደሚመለስ ከገለፀላቸው በኋላ ድርጅታችን በቅናሽ ዋጋ የሚሸጣቸው ባለ 53 ኢንች ሁለት ቴሌቪዥኖች ስላሉ የሚገዙ ከሆነ ውሰዱ ብሎ የባንኩን ስራ አስኪያጅ ይጠይቃቸዋል፡፡
ስራ አስኪያጁም ቴሌቪዥኑን መግዛት እንደሚፈልጉ፣ ነገር ግን ለጊዜው በእጃቸው ያለው 3 ሺህ ብር ላይ 12 ሺህ ብር ከሌላ ሰው ተበድረው በድምሩ 15 ሺህ ብር መስጠት እንደሚችሉ ይነግሩታል፡፡ ተጠርጣሪውም ቀሪውን ገንዘብ ሌላ ጊዜ እንደሚወስድ እና ቴሌቪዥኑን ለመረከብ ሌላ ሰው እንዲልኩ ስራ አስኪያጁን ካግባባ በኋላ ስራ አስኪያጁም 15ሺህ ብሩን አስይዘው ቴሌቪዥኑን የሚያመጣ ሰው አብረው መላካቸውን ኢንስፔክተር ታዲዮስ አስረድተዋል፡፡
ተጠርጣሪው በባንኩ ማናጀር የተላከውን ሰው በር ላይ ቆሞ ይጠብቀው በነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B48631 አ.አ በሆነ የወንጀል ግብራበሩ በሚያሽከረክረው መኪና ውስጥ እንዲገባ አድርጎ ጥቂት ከተጓዙ በኋላ 6 ኪሎ ዩኒቪርሲቲ አንደኛ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ 15ሺህ ብሩን ስጠኝ ብሎ ከተቀበለው በኋላ ሾፌሩ የመኪናውን ፍጥነት ሲያቀዘቅዝለት በሩን በመክፈት ቴሌቪዥኑን እንዲያመጣ የተላከውን ሰው ገፍትሮ በመጣል በፍጥነት ለማምለጥ ሞክረዋል፡፡
ነገር ግን በወቅቱ በተሽከርካሪ በመንቀሳቀስ የወንጀል መከላከል ስራ ሲሰሩ የነበሩ የፖሊስ አባላት በደረሳቸው ጥቆማ ወንጀሉን ፈፅሟል የተባለውን ግለሰብ ከነ ግብራበሩ እና ሲጠቀሙበት ከነበረው መኪና ጋር ተከታትለው በቁጥጥር ስር ሊያውሏቸው መቻላቸውን የምርመራ ሃላፊው ገልፀዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በተያዙበት ወቅት ሶስት ሞባይል ስልኮች እጃቸው ላይ እንደተገኘ እና ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛን።
ምርመራ እየተካሄደባቸው ከሚገኙት ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ጥቆማ እና መረጃ አለኝ የሚል ማንኛውም ሰው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ መነን አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በአካል ቀርቦ ማነጋገር እንደሚችል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡