photo_2024-06-24_06-48-38

ሰኔ  17፤2016 – በሩሲያ በቤተክርስቲያን እና ምኩራብ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ የ15 ሰዎች ህይወት አለፈ

ጥቃቱን አይኤስ መፈፀሙ ተነግሯል

በሩሲያ ሰሜን ካውካሰስ ሪፐብሊክ ዳግስታን ውስጥ በፖሊስ መኮንኖች፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ምኩራቦች ላይ በደረሰ ጥቃት የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፏል። በጴንጤቆስጤ የሩሲያ ኦርቶዶክስ በዓል ላይ ታጣቂዎች በደርቤንት እና ማካችካላ ከተሞች ላይ ጥቃት አድርሰዋል። ከሟቾቹ መካከል ቢያንስ 15 የፖሊስ አባላት፣ ቄስ እና የጥበቃ ሰራተኛ ይገኙበታል። ከአጥቂዎቹ መካከል ስድስቱ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ፖሊስ ሌሎችን እያደነ ይገኛል።

የአጥቂዎቹ ማንነት ባይታወቅም በዳጌስታን ከዚህ ቀደም ተከታታይ ጥቃቶች ሲደርሱ ቆይቷል።በእሁዱ ጥቃት ሁለት አብያተ ክርስቲያናት እና ሁለት ምኩራቦች ኢላማ ተደርገዋል። የዳግስታን ትልቋ ከተማ በሆነችው በማካችካላ አንድ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ተገድለዋል።15 ፖሊሶች በጥቃቱ መገደላቸውን የዳግስታን ሪፐብሊክ መሪ ሰርጌ ሜሊኮቭ ተናግረዋል። በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተለጠፉት ምስሎች እንዳሳዩት የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪዎች  ወደ ስፍራው ከመድረሳቸው በፊት ጥቁር ልብስ የለበሱ ሰዎች በፖሊስ ተሽከርካሪ ላይ ሲተኩሱ ያሳያል።

በቴሌግራም የመልእክት መላላኪያ መተግበሪያ ላይ ያለ ይፋዊ ባልሆነ ገፅ ማሽ ታጣቂዎች በደርቤንት በሚገኝ ህንፃ ውስጥ እንደነበሩ ተነግሯል። በሰርጎካል መንደር የፖሊስ መኪና ጥቃት ደርሶበታል።ዳግስታን በጣም ድሃ ከሆኑት የሩስያ ክፍሎች አንዷ ስትሆን አናሳ ክርስቲያኖች መኖሪያ ነች። እ.ኤ.አ. ከ 2007 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት የካውካሰስ ኢሚሬትስ የተባለ ቡድን በዳግስታን እና በአጎራባች የሩሲያ ሪፑብሊኮች በቼችኒያ ፣ኢንጉሼቲያ እና ካባርዲኖ-ባልካሪያ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወሳል።

በመጋቢት ወር በሞስኮ አቅራቢያ በሚገኘው ክሮከስ ከተማ አዳራሽ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ፣ የአይኤስ ቡድን ድርጊቱን ስለ መፈፀሙ ኃላፊነቱን ቢወስድም የመንግስት ባለስልጣናት ግን ለጥቃቱ ጥፋተኛ ሲሉ ጣታቸውን በዩክሬን እና በምዕራቡ ዓለም ላይ ቀስረዋል። በወቅቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ሩሲያ በአክራሪ የአሸባሪዎች ጥቃት ዒላማ ልትሆን አትችልም” ምክንያቱም “በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ልዩነት እና በሃይማኖቶች እና በጎሳ መካከል ያለውን አንድነት የሚያሳይ ልዩ ተምሳሌት ነው” ብለው አጥብቀው ተናግረው ነበር። ከሶስት ወራት በፊት የሩሲያ የሀገር ውስጥ ደህንነት አገልግሎት ኤፍ.ኤስ.ቢ በሞስኮ ምኩራብ ላይ ጥቃት ለማድረስ የአይኤስ ሴራ ማክሸፉን ማስታወቁ ይታወሳል።

በስምኦን ደረጄ

Tags: No tags

2 Responses

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *