በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በዳውሮ ዞን በሎማ ቦሣ ወረዳ ሻይቲ ፉላሳ ቀበሌ ተሳፋሪ መስለው ሞተር ሳይክል ለመቀማት አሽከርካሪውን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉ ተካሳሾች ከ24 ዓመት ፅኑ እስራት እስከ እድሜ ልክ እስራት መቀጣታቸው ተነግሯል ።
ተከሳሾች 1ኛ አረጋ አርጃ ፣ 2ኛ ካለብ ዲናቶ እና 3ኛ ሰውለሰው በቀለ ሲሆኑ በረቀቀ መንገድ በምስጥር በመደራጀት ያልተገባ የንብረት ጥቅም ለማግኘት ሟች ጌታሁን ከንፈሻ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪ ላይ የግድያ ወንጀል መፈጸማቸው ተነግሯል ።
የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት ገደማ ከሚኖርበት ዲሣ ከተማ ተሳፋሪ በመምሰል በ3ኛ ተከሳሽ አቀናባሪነት ሟችን ጠርተው በማስወጣት ወደ ገሣ ከተማ አስተዳደር አድርሰን በማለት በሟች ሞተር ሳይክል ተሳፍረው ለመሄድ እንደተስማሙ ተገልጿል ።
በዚህም መሠረት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በሟች ሞተር ሳይክል ተሳፍረው ወደ ሎማ ቦሣ ወረዳ ሻይቲ ፉላሳ ቀበሌ ኦቺ የሚባል ቦታ ሲደርሱ ሟችን ሽንት እንሸናለን በማለት ወርደው በቦታው በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለው አስክሬኑን ከእንጨት ጋር አስረው በማስቀመጥ የሟች ሞተር ሳይክል ይዘው እንደተሰወሩ ተጠቅሷል ።
ተከሳሾቹ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ከተሻገሩ እና ከአከባቢው ከተሰወሩ በኃላ የዞኑ ፓሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላትና ከህብረተሰብ ጋር ባደረገው ብርቱ ክትትል እንደተያዙ የዳውሮ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አ/ቶ ፍቃዱ ደምሴ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ። የዞኑ ፍትህ መምሪያ ልዩ ልዩ ወንጀሎች ዐቃቤ ህግ በሶስቱም ተከሳሾች ላይ ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መመሰረቱ ተገልጿል።
ተከሳሾች ችሎት ቀርበው የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም በማለት ክደው ቢከራከሩም በዐቃቤ ህግ የቀረበው ማስረጃ ተከሳሾች ወንጀል መፈጸማቸውን የሚያስረዳ በመሆኑ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን እንደተሰጣቸውም ተነግሯል። ነገር ግን ተከሳሾች አቅርበው ባሰሙት መከላከያ ማስረጃ የዐቃቤ ህግን ክስና ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተልፏል ።
ስለሆነም የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት አንደኛ ተከሳሽ አ/ቶ አረጋ አርጃ እና 2ኛ ተከሳሽ አ/ቶ ካለብ ዲናቶ በ24 አመት ጽኑ እስራት እና 3ኛ ተከሳሽ አ/ቶ ሰውለሰው በቀለ በዕድሜ ልክ እስራት እንድቀጡ ወስኗል።
በአበረ ስሜነህ
