ዘመናት ያስቆጠሩ ከአድማጭ ጆሮ ርቀው የኖሩና በስፋት ያልተደመጡ የዘመን ቃናዎች በተሰኘ መጠሪያ ድምፃዊ ዳዊት ጽጌ ሙሉ አልበም ለአድማጭ ሊያደርስ መሆኑን ብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ሰምቷል።
ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ ቀደም ያሉ ሙዚቃዎች ከትውልድ ትውልድ ሳይሸጋገሩ ተረስተው መቅረታቸው ለዚህ ስራ መነሳሳት ምክንያት እንደሆነው ተናግሯል።
ቀደም ያሉት ሙዚቃዎች በሬዲዮ ጣቢያዎች ብቻ ተገድበው መቀመጣቸው፣ የተቀረጹበት ቴክኖሎጂ ረጅም ዓመት ለመዝለቅ የማያስችል መሆኑ እንዳይደመጡ ከሚያደርጋቸው ምክንያቶች አንዱ ነው ተብሏል።
ድምፃዊ ዳዊት ጽጌ ቆየት ያሉ የሙዚቃ ስራዎችን ከያሉበት አፈላልጎ በዘመናዊ የድምጽና የምስል ቴክኖሎጂ ተገልብጠው በዘመኑ የድምፅ ቀረጻ ፣ የቅንብር ና የሚክሲንግ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ወደ አድማጭ እንደሚደረስም ተናግሯል።
በአዲስ መልክ ወደ አድማጭ የሚደርሱት ሙዚቃዎች አንጋፋ ድምፃዊያን ከሆኑት መካካል የአሰፋ አባተ (ፊርማና ወረቀት) ፣ ጥላሁን ገሰሰ(የግሌ ነሽ)፣ እና እሳቱ ተሰማ(ድማማ) የተሰኙ ሙዚቃዎች እንደሚገኙበት የሙዚቃ አቀናባሪ አበጋዝ ክብረወርቅ ተናግሯል። ከ ዘመን ቃናዎች አልበም ላይ ሶስት ሙዚቃዎችም እንዳቀናበረ ገልጿል።
የሙዚቃ ቪዲዮው ከአርብ ምሽት ጀምሮ በድምፃዊ ዳዊት ጽጌ የዩቲውብ ቻናል ወደ አድማጭ ይደርሳል ተብሏል ። ድምፃዊ ዳዊት ጽጌ ወጣት የሙዚቃ ባለሙያዎችን ያሳተፈውን ሁለተኛ የሙዚቃ አልበሙን እያዘጋጀ እንደሆነ እና በቅርቡም ለአድማጭ እንደሚደርስ ብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ሰምቷል።
በኤደን ሽመልስ

2 Responses