በ2016 ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ 239 ድንገተኛ አደጋዎች መድረሳቸውን የአዲስ አበባ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ ኮሚሽን አስታውቋል ።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት ባጋጠሙት 239 አደጋዎች ከ475 ሚሊየን ብር በላይ ንብረት ሲወድም የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ባደረጉት ጥረት 7.8 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን ተችሏል፡፡
ከደረሱት አደጋዎች መካከል 208 አደጋዎች በአዲስ አበባ ያጋጠሙ ሲሆን 33 አደጋዎች ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የደረሱ መሆናቸውንን ተነግሯል፡፡በስድስት ወራቱ ካጋጠሙት ከአደጋዎቹ ዉስጥ 150 የሚሆኑት የእሳት አደጋዎች ሲሆኑ 89 አደጋዎች ከእሳት ዉጪ ያጋጠሙ አደጋዎች ናቸው ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል 31 ሰዎች ከእሳት ዉጪ ባጋጠሙ ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ህይወታቸዉ አልፎ የተገኙ ሲሆን አስከሬናቸው የኮሚሽኑ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አንስተዉና አዉጥተዉ ለፖሊስ አስረክበዋል ያሉን አቶ ንጋቱ የደረሱትን አደጋዎች ለመቆጣጠር በተደረገ ጥረት ቁጥራቸዉ 25 የሆኑ ሰዎችን ከአደጋዎቹ ህይወታቸውን መታደግ ተችሏል ።
አደጋዎቹ የደረሱት ወንዝ ዉስጥ፣ተቆፍረዉ ክፍቱን በተተዉ ጉድጓዶች ፣በኤሌክትሪክና በመሳሰሉት ናቸዉ፡፡ ከነዚህ ዉስጥም ፖሊስ ምርመራ እያደረገባቸዉ የሚገኙ አንዳሉበት ተመላክቷል፡፡
በትግስት ላቀዉ