በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ህገ-ወጥ እንቅስቃሴን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተደረገ ስምሪት በዘረፋ ወንጀል የተሰማሩ 27 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል ።
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 17 ግለሰቦች ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም ለስርቆት ሲንቀሳቀሱባቸው ከነበሩ 8 ባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪ እና አንድ ሞተር ሳይክል ጋር እንደተያዙ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ክፍል ሃላፊ ምክትል ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ።
ሌሎች 10 ተጠርጣሪዎች ቀደም ሲል የተያዙ ሲሆን ምርመራ ተጣርቶ ክስ እንደተመሠረተባቸው አክለዋል ። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ ከሌሎች አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የገቡ ግለሰቦች ይገኙበታል ተብሏል ።
ማህበረሰቡ በግብይት ፣ በንግድና በሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ስልክ ገንዘብና ሌሎች ንብረቶችን በጥንቃቄ እንዲይዝ እና ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
በአበረ ስሜነህ