ሊና የተባለችው ወጣት ኮሎምቢያዊት ሴት ስትሆን ከሰባት ጡረተኞች ጋር ፍቅር የሚመስል ግንኙነት ውስጥ የገባች ሲሆን አዛውንቶቹን ለገንዘብ ፍላጎቷ ስትል ስትጠቀምባቸው እንደነበር ተሰምቷል።
በባራንኪላ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ሊና ያልተለመደ ታሪኳ በማህበራዊ ድረ ገፅ ላይ መሰራጨቱን ተከትሎ በመላው ሀገሪቱ መነጋገሪያ ሆናለች። በራሷ ዕድሜ ክልል ከሚገኙ ከወንዶች ጋር ብዙ አሳዛኝ የፍቅር ግንኙነቶችን ካደረገች በኋላ ወጣቷ ሴት በምትኩ ጡረተኞችን ዒላማ በማድረግ የስሜት አለመረጋጋቷን ለመቅረፍ እና የገንዘብ ድጋፍ በቀላሉ ማግኘት እንደምትችል ትገነዘባለች።
ያልተሳካ የፍቅር ግንኙነቷን ወደ ተሻለ ህይወት ለመለወጥ በማሰላሰል ሊና ጎረቤቷ ከሆኑ አዛውንት ጋር ቅርርብ መፍጠር ትጀምራለች። እኚህ አዛውንት ከዚህ ቀደም ከእርሷ ጋር ለመሆን ፍላጎት እንዳላቸውም ታስታውሳለች። በተጨማሪም በእድሜ ከሚበልጧት አዛውንት ወንዶች ዘንድ በጣም ተፈላጊ እንደሆነች ተረድታለች። እናም በህዝብ ፓርኮች እና ሌሎች በብቸኝነት የሚያሳልፉ አዛውንቶች የሚዝናኑባቸው ቦታዎች የማጥመጃ መረቧ ማድረግ ጀመረች። እናም በአሁኑ ወቅት በገንዘብ ከሚደግፏት ከሰባት ጡረተኞች ጋር የጠበቀ ግንኙነት መመስረት ችላለች።
ከእድሜ እኩዮቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነቶቼን ከመረመርኩ በኋላ ማሰብ ጀመርኩ። አዛውንቶቹ ለሚያስፈልግህ ነገር ምንም መጠየቅ የለብህም ፣ ሁሉንም ነገር ይሰጣሉ ምክንያቱም በእድሜያቸው እንደ እኔ ያለች ሴት አያገኙም። ለዛም ነው ጡረተኞችን ለመፈለግ የወሰንኩት ስትል ሊና ለኡልቲማ ሆራ ቫሌ የተሰኘ ጋዜጣ ተናግራለች። ሁልጊዜ ደስተኛ እንድሆን ያደርጉኛል በማለት አክላለች።የሊና ሰባት አረጋውያን የወንድ ጓደኞቿ ካርሎስ፣ ሲሞን፣ ጄሱስ፣ ፓብሎ፣ ማኑዌል እና ሌሎች ሁለት ስማቸውን ያልተገለፁ ወንዶች ናቸው።
ሁሉም አዛውንቶች እርስ በእርስ የሚተዋወቁ ሲሆን በወጣቷ ዘንድ ይበልጥ ለመወደድ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል። ወንዶቹ የሊናን ወጪዎች ለመሸፈን እና የቤት ውስጥ ስራዎችን እንደ ጽዳት፣ ልብስ ማጠብ እና ምግብ ማብሰልን ጨምሮ እርሷን የመርዳት ኃላፊነት አለባቸው። በዚህም የተነሳ በእርሷ ዘንድ ይበልጥ ለመወደድ ይወዳደራሉ። ሊና ከአዛውንቶቹ ጋር የመሰረተችው ግንኙነት ከፍቅር ይልቅ እንደ ንግድ ስራ ትገልፀዋለች። በየወሩ ብዙ ገንዘብ ለሚሰጧት ለጋስ አዛውንት የበለጠ አብሮ የማሳለፍ እድል እንደምትሰጠውም ትገልጻለች።
የሊና ታሪክ በቅርቡ ከኮሎምቢያ በተጨማሪ በደቡብ አሜሪካ ሀገራት ውስጥ በስፋት ተሰራጭቷል። አንዳንዶች በእድሜ የገፉ ሰዎችን በመጠቀሟ በቁጥጥር ስር መዋል እንዳለባት አስተያየት ሰጥተዋል። ሌሎች ደግሞ ተንኮለኛ ናት የገንዘብ ፍላጎቷን ለመሙላት ስትል የሄደችበት ርቀት አስገራሚ ነው ብለዋል። ሊና ከአዛውንቶቹ ጋር ስላላት ግንኙነት እንጂ ማንም ሰው ስለሚያስበው ነገር ግድ አይሰጠኝም ስትል ትደመጣለች።
በስምኦን ደረጄ

2 Responses