በምስራቅ ሀረርጌ ዞን በደኖ ወረዳ ዋሬ ቀበሌ ከጫት ማሳ ውስጥ ጫት እየወሰደ ይሸጥብናል በማለት የተጠረጠረን ግለሰብ ላይ የግድያ ወንጀል የፈፀመው ተከሳሽ በእስራት መቀጣቱን የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል፡፡
የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ሳሊም ሙፍቲሀል ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደገለፁት ተከሳሽ ጁነዲን ኢብራሂም የተባለው ግለሰብ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም ሌሎች ስድስት ሰዎችን በማስተባበር ነው ወንጀሉን የፈፀመው፡፡
ከጫት ማሳ ውስጥ ጫት እየወሰደ የሚሸጠው አህመድ ሹሙሚ የተባለው ግለሰብ ነው በማለት ወደ መኖሪያው አካባቢ በመሄድ አህመድን ሹሙሚ ከተኛበት ቀስቅሰው በመውሰድ በጥይት ተኩሰው መግደላቸው ዓቃቢ ህግ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በከፈተው የክስ መዝገብ ላይ መጥቀሱን ተናግረዋል ፡፡
አቃቢ ህግ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 5391 መሰረት በሰባት ሰዎች ላይ በግድያ ወንጀል የመሰረተው ክስን ሲከታተል የነበረ የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቢህግ ያቀረበው ማስረጃ በስድስቱ ተከሳሾች ላይ ጥፋታቸው በበቂ ሁኔታ ባለመረጋገጡ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 141 መሰረት በነፃ እንዲለቀቁ ወስኗል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ ጁነዲን ኢብራሂም ደግሞ በአቃቢ ህግ ማስረጃ ጥፋተኛ መሆኑ በመረጋገጡ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን አቶ ሳሊም ሙፍቲሀል ጨምረው ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ፡፡
በምህረት ታደሰ

2 Responses