የፍሎሪዳ ገዥ ሮን ዴሳንቲስ እ.ኤ.አ. ከ2024 ፕሬዚዳንታዊ ውድድር ራሳቸውን በማግለል ዶናልድ ትራምፕን ደግፈዋል። በኒው ሃምፕሻየር ከሚካሄደው የሪፐብሊካን ምርጫ አስቀድመው ይህንኑ ውሳኔ አሳልፈዋል። ዴሳንቲስ በአንድ ወቅት ለፓርቲው እጩ ጠንካራ ተፎካካሪ ተደርገው ይወሰድ የነበረ ቢሆንም በትላንትናው እለት ግን ይህ ፉክክራቸው እንዳበቃ እና ለሪፐብሊካን እጩነት የሚያበቃ ግልፅ የድል መንገድ የለም ብለዋል ።
የትራምፕ የመጨረሻ ቀሪ ተፎካካሪ የሆነችው ኒኪ ሃሌይ ስትሆን የወቅቱን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ማሸነፍ የምችለው እኔ ብቻ ነኝ ስትል ናግራለች። ኒኪ ሃሌይ በነገው እለት በኒው ሃምፕሻየር ከትራምፕ ጋር ፊት ለፊት ይፎክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህም በህዳር ወር አጠቃላይ ምርጫ የሪፐብሊካን እጩን ለመምረጥ በግዛት ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ ነው።እሁድ ከሰአት በኋላ በኤክስ ላክ በተለቀቀው አምስት ደቂቃ የሚጠጋ ቪዲዮ ላይ ዴሳንቲስ ዘመቻዬ አብቅቷል ብለዋል።
የፍሎሪዳ ገዥው በአዮዋ የመጀመሪያውን ውድድር 51 በመቶ ድምጽ በማሸነፍ ግንባር ቀደም የሆኑትን ትራምፕን እደግፋለሁ ብለዋል።ዴሳንቲስ አብዛኞቹ የሪፐብሊካን መራጮች “ለዶናልድ ትራምፕ ሌላ እድል መስጠት እንደሚፈልጉ” ግልጽ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል።ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ጋር አለመግባባቶችን እንደነበረ ግን ዴሳንቲስ አምነዋል ።ነገር ግን ትራምፕ በህዳር አጠቃላይ ምርጫ የዴሞክራቲክ እጩ ከሆኑት ባይደን በላይ ናቸው ብለዋል ።
ዴሳንቲስ “የሪፐብሊካንን እጩ ለመደገፍ ቃል ፈርሜያለሁ፣ እናም ይህን ቃል አከብራለሁ” ብለዋል። ትራምፕ እሁድ ከሰአት በኋላ በኒው ሃምፕሻየር ውስጥ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ስለ ዴሳንቲስ ከተፎካካሪነት ራሳቸውን ማግለል አስመልክቶ የመጀመሪያ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ከፍተኛ ደስታ ውስጥ ነበሩ። በድጋፍ ሰልፍ ላይ ለተገኙት ታዳሚዎች ንግግር ሲያደርጉ፣ የቀድሞ ተቀናቃኛቸውን “በጣም አስፈሪ ሰው” ሲሉ ገልጸዋል፣ በማከልም “በጣም ጥሩ ዘመቻ አካሂዷል፣ ቀላል አልነበረም” ብለዋል።
በቤዛዊት አራጌ
