የሶማሊያ ታጣቂ ቡድን አልሸባብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሄሊኮፕተርን ከስምንት የሚጠጉ ተሳፋሪዎች እና የበረራ ሰራተኞች ጋር መያዙን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ሄሊኮፕተሩ በማዕከላዊ ሶማሊያ በቡድኑ እጅ ስር በሚገኝ ስፍራ ላይ አርፏል። በሶማሊያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮ (ኡንሶም) ሄሊኮፕተሩ የህክምና አቅርቦት ላይ እንደነበር በመግለፅ ክስተቱ መፈጠሩን አረጋግጧል።
አልሸባብን ተልዕኮው ባይጠቅስም ለማስለቀቅ ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው ብሏል። በኤኤፍፒ የዜና ወኪል የታየውን ክስተት አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳለው ሄሊኮፕተሯ ከዱሳማሬብ በስተደቡብ ምስራቅ 70 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ያረፈ ሲሆን በአውሮፕላኑ ውስጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኛ አለመኖራቸውን ገልጿል።በውስጡ የነበሩ ሰዎች የሶስተኛ ወገን የስራ ተቋረጮች መሆናቸውን ዘገባው አመላክቷል።
በሄሊኮፕተሩ ውስጥ የተሳፈሩት ሰዎች ዜግነት እና ብዛታቸው በትክክል አልተገለፀም። አንድ ተሳፋሪ ሲሞት ሁለት ሌሎች ደግሞ መሸሻቸው ተዘግቧል። አልሸባብ በደቡብ እና መካከለኛው ሶማሊያ ሰፊ ግዛቶችን አሁንም ተቆጣጥሮ ይገኛል። ቡድኑ ከአልቃይዳ ጋር የተቆራኘ ሲሆን ለ20 አመታት ያህል የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ ቆይቷል።ሄሊኮፕተሯን በቁጥጥር ስር በአልሻባብ መዋሏን የጋልጉዱግ ክልል የጸጥታ ሚኒስትር መሀመድ አብዲ አዳን አረጋግጠዋል።
በሄሊኮፕተሩ ላይ በርካታ የውጭ ሀገራት ዜጎች እና ሁለት የሀገር ውስጥ ተወላጆች እንደነበሩ የሶማሊያ ወታደራዊ ባለስልጣን ሻለቃ ሀሰን አሊ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል። “በተጨማሪም የህክምና ቁሳቁስ ጭኖ የነበረ ሲሆን የተጎዱ ወታደሮችን ከጋልጉዱድ ክልል ማጓጓዝ ነበረበት” ሲሉ ተናግረዋል። ሄሊኮፕተሩ በአልሸባብ ላይ የመንግስት ሃይሎች ባደረገው ጥቃት በግንባሩ አቅራቢያ ወደሚገኘው ዊሲል ከተማ በማቅናት ላይ ነበር።
በስምኦን ደረጄ