በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን በሁልባረግ ወረዳ በህገወጥ የሰዎች ዝዉዉር ወንጀል የተከሰሰዉ ግለሰብ በእስራት መቀጣቱን የክልሉ ፖሊስ ገልጿል።የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ የሚዲያ ክፍል ኃላፊ ም/ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ግለሰቡ ያታለላቸው ተበዳዮች 1ኛ. ሁልፈሞ ናስር 2ኛ. ማሬ ሡልጣን 3ኛ. መሐመድ ከይሬ ሲሆኑ በሁልባረግ ወረዳ ቶዴ ጠመዳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ዲጆ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በጥር ወር 2015 ዓ.ም ድርጊቱ ተፈፅሟል።
ተከሳሽ አክመል ሞሳ ኢብሮ ሶስቱን ግለሰቦች በህገወጥ መንገድ ድንበር ለማሻገር በማሰብ እስከመኖሪያ ሠፈራቸው ድረስ በመሄድ ሳዑዲ አረቢያ ልላካችሁ ምንም ገንዘብ አያስፈልግም ብሎ በማሳመን ወደ አዲስ አበባ በመዉሰድ ለሌላ ደላላ እንዳስረከባቸው ገልፀዋል።
ወጣቶቹ ተታለዉ መወሰዳቸዉን የተረዱት ቤተሰቦችም ልጆቻቸዉን ለማስመለስ እግር በእግር ተከታትለዉ ወደ አዲስ አበባ ያቀናሉ።የግል ተበዳይ ወላጆች የልጆቻቸዉን ዱካ ተከታትለው አዲስ አበባ ሲገቡ ልጃቸውን ለማስለቀቅም 15ሺ ብር ይጠየቃሉ።
ይህ መረጃ የደረሰው የሁልባራግ ወረዳ ፖሊስ ተከሳሹን በቁጥጥር ስር አዉሎ ምርመራ አጣርቶ የምርመራ መዝገቡን አደራጅቶ ለዐቃቤ ህግ መላኩ ተገልጿል።በተከሳሹ ላይ የተጣራዉ የምርመራ መዝገብ ከፖሊስ የተረከበዉ የዞኑ ዐቃቤ ህግ ክስ ይመሰርታል።ዓቃቤህግ የመሰረተዉን ክስ የተመለከተዉ የስልጤ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት በቀረበለት ማስረጃ የተከሳሹ ድርጊት ወንጀል መሆኑ በማረጋገጡ ጥፋተኛ ሲል ብይን ሰጥቷል።
ተከሳሹን ያርማል ሌላውን ማህበረሰብ ያስተምራል በሚል በተከሳሽ አክመል ሞሳ ኢብሮ ላይ በ11 ዓመት ጽኑ እስራትና አምስት መቶ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ እንደወሰነበት ም/ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ጨምረው ለብስራት ሬድዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
በምህረት ታደሰ
2 Responses