ጥር 29፤2016 – በስልጤ ዞን ወደ ሳዑዲ አረቢያ እወስዳችኋለው በማለት የማታለል ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን በሁልባረግ ወረዳ በህገወጥ የሰዎች ዝዉዉር ወንጀል የተከሰሰዉ ግለሰብ በእስራት መቀጣቱን የክልሉ ፖሊስ ገልጿል።የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ የሚዲያ ክፍል ኃላፊ ም/ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ግለሰቡ ያታለላቸው ተበዳዮች 1ኛ. ሁልፈሞ ናስር 2ኛ. ማሬ ሡልጣን 3ኛ. መሐመድ ከይሬ ሲሆኑ በሁልባረግ ወረዳ ቶዴ ጠመዳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ዲጆ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በጥር ወር 2015 ዓ.ም ድርጊቱ ተፈፅሟል።

ተከሳሽ አክመል ሞሳ ኢብሮ ሶስቱን ግለሰቦች በህገወጥ መንገድ ድንበር ለማሻገር በማሰብ እስከመኖሪያ ሠፈራቸው ድረስ በመሄድ ሳዑዲ አረቢያ ልላካችሁ ምንም ገንዘብ አያስፈልግም ብሎ በማሳመን ወደ አዲስ አበባ በመዉሰድ ለሌላ ደላላ እንዳስረከባቸው ገልፀዋል።

ወጣቶቹ ተታለዉ መወሰዳቸዉን የተረዱት ቤተሰቦችም ልጆቻቸዉን ለማስመለስ እግር በእግር ተከታትለዉ ወደ አዲስ አበባ ያቀናሉ።የግል ተበዳይ ወላጆች የልጆቻቸዉን ዱካ ተከታትለው አዲስ አበባ ሲገቡ ልጃቸውን ለማስለቀቅም 15ሺ ብር ይጠየቃሉ።

ይህ መረጃ የደረሰው የሁልባራግ ወረዳ ፖሊስ ተከሳሹን በቁጥጥር ስር አዉሎ ምርመራ አጣርቶ የምርመራ መዝገቡን አደራጅቶ ለዐቃቤ ህግ መላኩ ተገልጿል።በተከሳሹ ላይ የተጣራዉ የምርመራ መዝገብ ከፖሊስ የተረከበዉ የዞኑ ዐቃቤ ህግ ክስ ይመሰርታል።ዓቃቤህግ የመሰረተዉን ክስ የተመለከተዉ የስልጤ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት በቀረበለት ማስረጃ የተከሳሹ ድርጊት ወንጀል መሆኑ በማረጋገጡ ጥፋተኛ ሲል ብይን ሰጥቷል።

ተከሳሹን ያርማል ሌላውን ማህበረሰብ ያስተምራል በሚል በተከሳሽ አክመል ሞሳ ኢብሮ ላይ በ11 ዓመት ጽኑ እስራትና አምስት መቶ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ እንደወሰነበት ም/ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ጨምረው ለብስራት ሬድዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በምህረት ታደሰ

ጥር 29፤2016 – በጋና ጋዜጠኛን በጥፊ የመቱት የምክር ቤት አባል በጋዜጠኞች ማህበር ላይ ስማቸው በጥቁር መዝገብ ሰፈረ

 

የጋና የፓርላማ አባል የሆኑት ፋሩክ አሊዩ ማሃማ ጋዜጠኛ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በሚል በጋና ጋዜጠኞች ማህበር (ጂጄኤ) ጥቁር መዝገብ ውስጥ ስማቸው ሰፍሯል።

እየጨመረ የመጣውን ጥቃቶች ተከትሎ በሀገሪቱ ውስጥ ጋዜጠኞችን ለመጠበቅ በማህበሩ የተሰጠው ጠንካራ መግለጫ ሆኗል። የምክር ቤቱ አባል ማሃማ እና አጃቢዎቻቸው በሰሜናዊ ጋና የአዲስ አርበኞች ፓርቲን (የኤንፒፒ) የፖለቲካ ዝግጅት ሲዘግብ የነበረውን የሲቲ ቲቪ ጋዜጠኛ መሀመድ አሚኑ ኤም አላባራ ላይ ጥቃት እንደሰነዘሩ ተዘግቧል።

በፓርቲው የመጀመሪያ ደረጃ ምርጫ ወቅት የተፈጠረውን ትርምስ ሲዘግብ ጋዜጠኛው አንዳች ጥፋት ባልፈፀመበት ሁኔታ የፓርላማው አባል በጥፊ መምታታቸው ተሰምቷል። አንድ የፖሊስ አባል እና የምርጫ አስፈፃሚም ጥቃት ደርሶባቸዋል ነገር ግን ወደ ስፍራው በመጡ ወታደራዊ አባላት የምክር ቤቱ አባል እና ጠባቂዎቻቸው ገለል እንዲሉ አድርገዋል።

የጋና የጋዜጠኞች ማህበር እና ሌሎች ሶስት ማህበራት የፓርላማ አባሉ የመገናኛ ብዙሃን መድረኮችን እንዳይጠቀሙ ለመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች አሳስበዋል። ገዥው ፓርቲ ኤንፒፒ እና ፖሊስ ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል እና ለፍርድ እንዲቀርቡ የ10 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምርመራ መጀመሩን ተናግሯል። በጋና ውስጥ በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሁንም የተስፋፋ ቢሆንም ብዙ ጊዜ አጥፊዎች ሲቀጡ አይታይም። እ.ኤ.አ. በ2019 አህመድ ሁሴን-ሱአሌ የተባለው የምርመራ ጋዜጠኛ በአክራ በቤተሰቡ መኖሪያ ቤት አቅራቢያ ባልታወቁ ታጣቂዎች በጥይት ተገድሏል።

በኤደን ሽመልስ

ጥር 28፤2016 – የፋሲለደስ ቤተመንግሥትን ፤ ለማደስ መንግስት ቢንቀሳቀስም በተለያዩ ሴራዎች ሊከዉነዉ አልቻለም ሲሉ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ

 

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ በዛሬው ዕለት ጥር 28 ቀን ፣ 2016 ዓ.ም ተካሂዷል። ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ከተለያዩ የም/ቤቱ አባላት ጥያቄ የቀረበላቸዉ ሲሆን ምላሽና ማብራሪያም ሰጥተዋል።

መንግስት በአማራ ክልል እያከናወነ ካላቸዉ ስራዎች ዉስጥ ለቱሪዝም ምቹ የሆኑ ቦታዎችን በማዘመን እና በማደስ ተጨማሪ ገቢ እና የስራ እድል የሚገኝበትን አማራጭ አይቶ እንደነበር ገልጸዋል።

የፋሲለደስ ቤተመንግሥት በእርጅና ያጋጠመዉን ጉዳት ለማደስ መንግስት እቅድ እንደነበረዉም ጠ/ሚኒስትሩ በዛሬዉ የም/ቤት ዉሎ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ይህ በጎንደር የሚገኘዉን የፋሲለደስ ቤተመንግሥትን ፤ መንግስት ለማደስ ቢንቀሳቀስም በተለያዩ ሴራዎች እና አሉባልታዎች መስራት አለመቻሉን ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ መናገራቸውን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል።

ለዚህም ከመጽሐፍት ሽያጭ እድሳቱን ለመስራት ቢታቀድም መከወን ግን አልተቻለም ሲሉ ተናግረዋል። ሆኖም ጠ/ሚኒስትሩ መንግስት ያጋጠመዉን ችግር ያልገለፁ ሲሆን ሴራ እና አሉባልታ ያሏቸዉንም ጉዳዮች ከማብራራት ተቆጥበዋል።

በበረከት ሞገስ

Screenshot 2024-02-03 232622

ጥር 25፤2016 – በዛሬው እለት ፒያሳ አካባቢ ባጋጠመ የእሳት አደጋ ሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ አምስት የንግድ መደብር ወድሙ

 

በአዲስ አበባ ከተማ በዛሬው እለት በደረሰ የእሳት አደጋ የጄኔሬተር እና የተለያዩ የእሳት ማጥፊያ መሳሪዎች መሸጫ የሆኑ አምስት ሱቆች መውደማቸውን የአዲስ አበባ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ ኮሚሽን አስታውቋል።

ዛሬ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም  ከቀኑ 7:14  ሰዓት ላይ በአራዳ ክፍለ-ከተማ ወረዳ አንድ ሸዋ ዳቦ እየተበላ በሚጠራዉ አካባቢ በተነሳ የእሳት አደጋ አምስት የንግድ ሱቆች የተቃጠሉ ሲሆን በሁለት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መደረሱን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

የንግድ ሱቆቹ  የህንጻ መሳሪያዎች የጀኔሬተር እና የእሳት ማጥፊይ መሸጫዎች ሲሆኑ ከንግድ  ሱቆቹ ዉስጥ በርካታ ንብረት ማዉጣት መቻሉም ተነግሯል ።

የእሳት አደጋዉን ለመቆጣጠር ዘጠኝ የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪ ከሀምሳ ሰባት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጋር የተሰማራ ሲሆን እሳቱን ለማጥፋት በተደረገ ርብርብ ወደሌሎች የንግድ ቤቶች ሳይዛመት መቆጣጠር ተችሏል።

የእሳት አደጋዉን ለመቆጣጠር ሁለት ሰዓት ፈጅቷል።

በትግስት ላቀው

ጥር 23፤2016 – የኢትዮጵያ አሌክትሪክ አገልግሎት የስነ ምግባር ጥሰት በፈፀሙ 23 አመራርና ሰራተኞች ላይ እርምጃ ወሰደ

 

የኢትዮጵያ አሌክትሪክ አገልግሎት በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ የተጠያቂነት ስርዓትን ለማስፈን ባከናወነው ስራ በ23 አመራርና ሰራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መውሰዱን አስታወቀ።

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ ከደንበኞች ከቀረቡለት 63 ጥቆማዎች ውስጥ ተገቢውን የማጣርት ስራ በማከናወን በ23 አመራርና ሰራተኞች ላይ ከጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ስንብት የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እንደወሰደ ነው ያስታወቀው ፡፡

በተጨማሪም የዲሲፕሊን ችግር በታየባቸው 409 ሠራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን የወሰደ ሲሆን በ106 ሠራተኞች ላይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ በ282 ሠራተኞች ላይ የደመወዝ ቅጣት፣ በ11 ሠራተኞች ላይ ስንብት እና በ10 ሠራተኞች ላይ ባደረገው ማጣራት ነጻ ብሏቸዋል፡፡

ተቋሙ ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችና ጥቆማዎችን ለመቀበል ከተዘረጉ የ905 እና 904 ነጻ የጥሪ ማዕከላት በተጨማሪ ደንበኞች ቅሬታቸውን ቀላልና ምቹ በሆነ መንገድ ማቅረብ የሚችሉበት ዘመናዊ የሙስና ጥቆማ መቀበያ ስርዓት ለመዘርጋት በሂደት ላይ መሆኑን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ከአገንግሎቱ ያገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

Screenshot 2024-02-01 140854

ጥር 23፤2016 – ድምፃዊ ዳዊት ጽጌ የዘመናት ቃናዎች የተሰኘ ቆየት ያሉ ዜማዎችን በአዲስ መልኩ ወደ አድማጭ ሊያደረስ መሆኑን አስታወቀ

 

ዘመናት ያስቆጠሩ  ከአድማጭ ጆሮ ርቀው  የኖሩና  በስፋት  ያልተደመጡ የዘመን ቃናዎች በተሰኘ መጠሪያ ድምፃዊ ዳዊት ጽጌ ሙሉ አልበም ለአድማጭ ሊያደርስ መሆኑን  ብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ሰምቷል።

ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ ቀደም ያሉ ሙዚቃዎች ከትውልድ ትውልድ ሳይሸጋገሩ  ተረስተው መቅረታቸው ለዚህ ስራ መነሳሳት  ምክንያት እንደሆነው ተናግሯል።

ቀደም ያሉት ሙዚቃዎች በሬዲዮ  ጣቢያዎች  ብቻ ተገድበው  መቀመጣቸው፣ የተቀረጹበት ቴክኖሎጂ ረጅም ዓመት  ለመዝለቅ የማያስችል   መሆኑ እንዳይደመጡ  ከሚያደርጋቸው ምክንያቶች አንዱ ነው ተብሏል።

ድምፃዊ ዳዊት  ጽጌ ቆየት ያሉ  የሙዚቃ ስራዎችን ከያሉበት አፈላልጎ  በዘመናዊ  የድምጽና  የምስል  ቴክኖሎጂ  ተገልብጠው   በዘመኑ የድምፅ  ቀረጻ  ፣ የቅንብር ና የሚክሲንግ  ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ወደ አድማጭ እንደሚደረስም ተናግሯል።

በአዲስ መልክ ወደ አድማጭ የሚደርሱት ሙዚቃዎች  አንጋፋ ድምፃዊያን ከሆኑት   መካካል የአሰፋ አባተ (ፊርማና ወረቀት) ፣ ጥላሁን ገሰሰ(የግሌ ነሽ)፣ እና እሳቱ ተሰማ(ድማማ) የተሰኙ ሙዚቃዎች  እንደሚገኙበት የሙዚቃ አቀናባሪ አበጋዝ ክብረወርቅ ተናግሯል።  ከ ዘመን ቃናዎች አልበም  ላይ ሶስት   ሙዚቃዎችም እንዳቀናበረ ገልጿል።

የሙዚቃ  ቪዲዮው  ከአርብ ምሽት ጀምሮ  በድምፃዊ  ዳዊት ጽጌ  የዩቲውብ ቻናል ወደ አድማጭ ይደርሳል ተብሏል ። ድምፃዊ  ዳዊት ጽጌ  ወጣት የሙዚቃ  ባለሙያዎችን ያሳተፈውን  ሁለተኛ የሙዚቃ አልበሙን እያዘጋጀ  እንደሆነ እና  በቅርቡም  ለአድማጭ እንደሚደርስ  ብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ሰምቷል።

በኤደን ሽመልስ

photo_2024-02-01_13-57-16

ጥር 23፤2016 – ከ1.1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ውጪ የተገነባው ሀይሌ ሆቴል ወላይታ ሶዶ በዛሬው እለት ስራ ጀመረ

 

ሆቴሎን ሰርቶ ለማጠናቅ 4 ዓመታት የፈጀ ሲሆን የሆቴሉን ስራ ለማጠናቀቅ በአንድ ወር ውስጥ አንድ መቶ ሚሊየን ብር ወጪ  ተደርጓል። ሀይሌ ሪዞርቶች ግሩፕ ዛሬ በይፍ ስራ የጀመረው ሀይሌ ሆቴል ወላይታ 9ኛ እንደሆነ ተነግራል።

ሀይሌ ሪዞርቶች ግሩፕ ባለቤት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ በቀጣይ አንድ አመት 3 ሆቴሎችን የመክፈት እቅድ እንዳለው ያስታወቀ ሲሆን ቦታዎቹም ጅማ ፣ ሻሸመኔ እና ደብረብርሃን ከተሞች መሆናቸውን ገልፃል።

የመጀመሪያ የሀይሌ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች በ2002 ዓ.ም በሀዋሳ የከፈተ ሲሆን በ14 ዓመት ውስጥ መዳረሻውን ዘጠኝ ማድረሱን አስታውቋል።እንደሀገር ያሉትን የሆቴል መዳረሻዎችን እጥረት በከፍተኛ ደረጃ እና ፍጥነት እየቀረፈ መሆኑን  የሀይሌ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች ግረፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ጋዲሳ ግርማ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

አሁን ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ሀይሌ ሆቴል ወላይታ ሶዶ 107 የመኝታ ክፍሎችን የያዘ ሲሆን ከ15 እስከ 600 ሰዎችን የሚይዙ የስብሰባ አዳራሾች እንዳላቸውም ተነግሯል።ሀይሌ ሆቴል ወላይታ አገልግሎት ለመስጠት 160 ሰራተኞችን መቅጠሩን የገለፁት አቶ ጋዲሳ ሆቴሉ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ከ300 በላይ ሰራተኞችን እንደሚቀጥር ይጠበቃል።

ሆቴሉ ደረጃውን የጠበቀ የዋና የጅምናዚየም እና የተለያዩ የውበት እና የጤና መጠበቂያ ማአከሎች በስሩ እንዳሉትም የተገለፀ ሲሆን በሆቴሉ ሜኑም የወላይታ ባህላዊ ምግቦች እንደሚካተቱ ተነግሯል።

በቀጣይ በምስራቅ አፍሪካ የመክፈት እቅድ እንዳለው ያስታወቀው ሆቴሉ በአንድ አመት ውስጥ እከፍታቸዋለው ካሉት ሆቴሎች በተጨማሪም ኮንሶ እና ወልቂጤ ላይ የሀይሌ ሆቴል ግንባታ እየተፍጠነ መሆኑ ተገልፃል።

ሀይሌ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች ግሩፕ እስካሁን ከ1ሺ800 በላይ ለሚሆኑ ሰዎችን ቋሚ የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን በቀጣይ የሆቴሎቹ ቁጥር ሲጨምር ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን የስራ እድል እንደሚከፍት አስታውቋል።

በሆቴሉ የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል አስተዳደር አቶ ተስፍዬ ይገዙ፤ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ እና ሌሎች የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል።

ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ እስካሁን ከገነባው ሆቴሎች አሁን ላይ እየተገነቡ ያሉ ሆቴሎች በግንባታ እቃ እጥረት እና መወደድ ፈተና እየሆነባቸው እንደሆነ የተናገረ ሲሆን አሁንም ግን እየተፈተነም ስራውን በስፍት እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በትግስት ላቀው

i

ጥር 23፤2016 – የዎልቭስ እና ማንቸስተር የዩናይትድን ጨዋታ ፉትቦል ባንድ ይዘውላችሁ ይቀርባሉ።

ጥር 23፤2016 – ውድ የብስራት ሬዲዮ አድማጮች የ facebook ገጻችን like, share እና Comment በማድረግ ሃሳብ አስተያየታችሁን አካፍሉን።

በ-#እንግሊዝ_ፕሪምየር_ሊግ የ-#ዎልቭስ እና #ማንቸስተር_ዩናይትድ-ን ጨዋታ #ፉትቦል_ባንድ ይዘውላችሁ ይቀርባሉ።

ማነኛውንም ሃሳብ አስተያየት አድርሱን። መልሰን ወደ እናንተ አናደርሳለን።

ምሽት ከ4:00-7:00 ሰዓት ይጠብቁን!

የብስራትን የተለያዩ ማህበራዊ ገጾች በመቀላቀል፤ ወቅታዊ መረጃዎችን እና ፕሮግራሞችን ይከታተሉ…

Facebook: https://bit.ly/3Hng6Qt

Website: https://www.bisrattv.com/

Telegram: https://t.me/Bisrat101fm

YouTube: https://bit.ly/3zAAOrB

Twitter: https://twitter.com/Bisrat101fm

Twitter: https://twitter.com/Bisrat101fm

TikTok: https://bit.ly/48DoztJ