በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ሀረማያ ወረዳ ውስጥ በቧንቧ ውሃ ወረፋ ላይ በተፈጠረ ጸብ በድንጋይ የአንዲትን ግለሰብን አራት ጥርስ ላይ ጉዳት ያደረሰችው ተከሳሽ በእስራት መቀጣቷን የሀረማያ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ ኢንስፔክተር ተስፋዬ አየለ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
ተከሳሽ ናሂ አህመድ የውሃ ቧንቧ ወረፋ ይዘው ሲቀዱ ከነበሩ ሶስት ግለሰቦች ውስጥ ዘሃራ በከር ጋር በወረፋ ምክንያት በመጣላታቸው ጉዳት ልታደርስባት መቻሏ ተረጋግጧል ።መጠኑ ትልቅ የሆነ ድንጋይ በመወርወር አራት ጥርሶቿ ላይ ጉዳት ያደረሰች ሲሆን አንደኛው ጥርስ በመውለቁም በአካል ማጉደል በቁጥጥር ስር ውላለች።
በወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረትም ክስ ተመስርቶባታል ። የክስ መዝገቡ በሰው እና በሰነድ ማስረጃ ተረጋግጦ ጥፋተኛ መሆኗን የሀረማያ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አረጋግጧል ። በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በተከሳሿ ላይ የሁለት ዓመት እስራት እንድትቀጣ የወሰነባት መሆኑን ኢንስፔክተር ተስፋዬ አየለ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
በኤደን ሽመልስ