ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ34 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል
ኢት ስዊች ይህን ያለው በዛሬው እለት 12ኛውን አመታዊ የባለአክሲዮኖች አጠቃላይ ስብሰባ ባካሄደበት ወቅት ላይ ነው።የኢትስዊች የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሰሎሞን ደስታ በመክፈቻ ንግግራቸው “ኢትስዊች ባለፈው የበጀት ዓመት ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የክፍያ ሥነ-ምህዳር እንዲኖር በማመቻቸት ረገድ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል” ብለዋል።
በተጨማሪም የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል እስከ ሰኔ 30 2025 ድረስ ወደ 2.56 ቢሊዮን ብር ማደጉን ጠቅሰዋል።ይህም ባለአክሲዮኖች የኩባንያውን የእድገት እና የዘመናዊነት ጥረቶችን ለመደገፍ ያላቸውን ጠንካራ ቁርጠኝነት ያሳያል ማለታቸውን ብስራት ሬዲዮ ሰምቷል።
አቶ ሰለሞን አክለውም የኩባንያው የፋይናንስ ሪፖርት እንደሚያሳየው 2.2 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ ማግኘቱን ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል።ከታክስ በፊት ያለው የኢትስዊች ትርፍ 1.42 ቢሊዮን ብር ገቢ አስመዝግቧል በማለት የቦርድ ሊቀመንበሩ ተናግረው ይህም ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ34 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል ።
ኢትስዊች በኢትዮጵያ ፈጣን እና አስተማማኝ የክፍያ ስርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣቱን ቀጥሏል። በተለይም እንደ ክፍያ ጥያቄ እና የQR ክፍያዎች ያሉ የአጠቃቀም ጉዳዮችን በማስቻል ኢትስዊች ሁሉንም የፋይናንስ ተቋማት ለመደገፍ አስፈላጊውን መሠረተ ልማት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ አቶ ሰለሞን ጨምረው ተናግረዋል።
ኢትስዊች በመጪው የበጀት ዓመት የአገልግሎት ጥራትንና መሠረተ ልማትን ማሻሻል፣ ቀጣይ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ፣ አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎቶችን ማስተዋወቅ እና ክልላዊ እና ድንበር ተሻጋሪ የክፍያ ዓለም አቀፍ ሽርክናዎችን ማጠናከርን ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።
በቅድስት ደጀኔ
