ጥር 22፤2016 – በአዳማ ወረዳ ተሰርቆ የተፈታታ ተሽከርካሪን ጨምሮ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

 

በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ ተሰርቆ የተፍታታ ተሽከርካሪ ጨምሮ የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን የአዳማ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አስታወቀ።

የአዳማ ወረዳ  ፖሊስ ወንጀል መርማሪ ክፍል ኃላፊ ሳጅን በሻ ዱቤ ለብስራት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ  እንደገለፁት በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ መፈተሻ ኬላ ላይ በቁጥጥር ስር የዋለዉ ኮንትሮባንድ  ከ5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የተለያዩ እቃዎች ጨምሮ ተሰርቆ የተፈታታ ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መነሻቸዉ ከጅቡቲ እና ከጅግጅጋ ከተማ እንደሆኑ የገለፁት ኃላፊዉ የተሰረቀ የተሽከርካሪ  እቃዎች ጨምሮ ኮስሞቲክ የተለያዩ አልባሳት እና የአይን መነፀሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን ገልፀዋል።

እነዚህን የኮንትሮባንድ እቃዎችን ሲያጓጉዙ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዉለዉ  የምርመራ መዝገባቸዉ ተጣርቶ  ለአቃቢ ህግ መላኩን ዋና ሳጅን ጨምረዉ ለጣቢያችን ገልፀዋል።

በበቀለ ጌታሁን

ጥር 22፤2016 – በጋዛ ቢያንስ ግማሹ ህንፃዎች ተጎድተዋል ወይም ወድመዋል ሲል አንድ አዲስ መረጃ አመላከተ

 

እስራኤል ለጥቅምት ሰባቱ የሃማስ ጥቃት የአጸፋ ምላሽ መስጠት ከጀመረች ወዲህ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የጋዛ ህንጻዎች ተጎድተዋል ወይም ወድመዋል ሲል አንድ አዲስ ትንታኔ አመላክቷል። ከታህሳስ ወር መጀመሪያ አንስቶ በደቡባዊ እና መካከለኛው ጋዛ ላይ የሚካሄደው የቦምብ ጥቃት እንዴት እንደተጠናከረ እና የእስራኤልን ወታደራዊ እርምጃ የካን ዮኒስ ከተማ ክፉኛ ውድመት እንዳደረሰባት ተገልጿል።እስራኤል ለጋዛውያን ለደህንነታቸው ሲሉ ወደ ደቡብ እንዲሄዱ ደጋግማ አስጠንቅቃለች።

በጋዛ ዙሪያ፣ የመኖሪያ አካባቢዎች ፈርሰዋል፣ ቀደም ሲል ሥራ የሚበዛባቸው የገበያ ስፍራዎች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል፣ ዩኒቨርሲቲዎች ወድመዋል እንዲሁም የእርሻ መሬቶች ተቃጥለዋል። በደቡብ ድንበር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ቤት አልባ በመሆናቸው የድንኳን ቤቶች በስፋት ይታያሉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው ወደ 1.7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ወይም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የጋዛ ህዝብ ተፈናቅሏል ።

የእስራኤል መከላከያ ሃይል በሃማስ ተዋጊዎች እና “የሽብር መሰረተ ልማቶች” ላይ ጥቃቱ ያነጣጠረ ነው ሲል ለቀረበበት ክስ ማስተባበያ ሰጥተዋል። የተገኘው የሳተላይት መረጃ ትንተና የጥፋቱን ትክክለኛ መጠን ያሳያል። ትንታኔው በጋዛ ሰርጥ ከ144 ሺ እስከ 175 ሺ የሚደርሱ ሕንፃዎች ተጎድተዋል ወይም ወድመዋል። ይህም ከ50 እስከ 61 በመቶ የሚሆነው የጋዛ ህንፃዎች ወድመዋል። በኒውዮርክ ሲቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሪ ሼር እና በኦሪገን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጃሞን ቫን ዴን ሆክ የተደረገው ትንታኔ በህንፃዎች ቁመት ወይም መዋቅር ላይ ድንገተኛ ለውጦችን ያሳያል ይህም ጉዳቶችን ያመላክታል ብለዋል።

በተለይ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የደቡባዊዋ ካን ዮኒስ ከተማ ክፉኛ ተመታለች፣ ከ38,000 በላይ ወይም ከ46 በመቶ በላይ ህንፃዎቿ ወድመዋል ወይም ተጎድተዋል ሲል ትንታኔው አመልክቷል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በካን ዮኒስ ከ1,500 በላይ ሕንፃዎች ወድመዋል ወይም ተጎድተዋል።

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-01-30_20-25-54

ጥር 21፤2016- የናይጄሪያ እዉቋ ተዋናይት ቪክቶሪያ ኢንያማ ባሏ ማንችስተር ዩናይትድ በተሸነፈ ቁጥር ይደበድባት እንደነበር ተናገረች

 

የናይጄሪያ እዉቋ ተዋናይት ቪክቶሪያ ኢንያማ ከቀድሞ ባለቤቷ ጋር በተፋታችበትን ምክኒያት ዙሪያ ቃለምልልስ ሰጥታለች።

ተዋናይቷ ፤ ባለቤቷ የሚደግፈዉ የእንግሊዙ ማንችስተር ዩናይትድ ሽንፈት ባጋጠመዉ ቁጥር አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጥቃት ሲፈጽምባት እንደነበር ተናግራለች። ይህንኑ ተከትሎም ከባለቤቷ ጋር ፍቺ መፈጸሟን አስረድታለች።

ባለቤቷ ቡድኑ ሽንፈት በገጠመዉ ወቅት ቴሌቪዥናቸዉን ይደበድብ እንደበር ገልጿለች። ከፍቺያቸዉ በኋላም ማንችስተር ዩናይትድ ሽንፈት ሲያጋጥመዉ ደስታ እንደሚሰማት እና ፈጣሪን እንደምታመሰግን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ከዘገባዉ ተመልክቷል። በትዳር ያፈራችዉ ልጇም ቡድኑ ሲሸነፍ በእናቱ ላይ የሚደርሰዉን ጥቃት ተከትሎ እርሱም ደስተኛ እንደሚሆን ተናግራለች።

ባለቤቷ እርሷን በትዳር ዉስጥ ለማቆየት እዉቅናዋን እንደማስፈራሪያነት ሲጠቀመዉ እንደነበርም ገልጻለች። በ 2013 ትዳራቸዉ በፍቺ የተጠናቀቀ ሲሆን በወቅቱ ማንችስተር ዩናይትድ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን ዋንጫ አንስቷል። ከተከታይኛዉ አመት ጀምሮ ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን መልቀቅ በኋላ ማንችስተር ዩናይትድ በዉጤት ቀዉስ ዉስጥ ይገኛል።

ተዋናይቷ ከፍቺያቸዉ በኋላም በ 2019 ልጃቸዉን የማሳደግ ሙሉ መብቱን ወስዳ ከእርሷ ጋር እንደሚገኝ ተናግራለች። ተዋናይቷ በትዳሯ ሁለት ልጆችን ያፈራች ሲሆን አሁን ላይ ኑሮዋን በእንግሊዝ አድርጋለች።

ተዋናይቷ ሲደርስባት ለነበረዉ ጥቃት አሁን ላይ የስነልቦና ባለሙያን ክትትል እያደረገች ሲሆን አንዳንድ አጋጣሚዎች ግን በዉስጧ እንደቀሩ በቃለምልልሱ ገልጻለች።

በበረከት ሞገስ

ጥር 21፤2016 – የወንድሜ  ሚስት መርዝ አብልታኛለች በማለት የግድያ ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

 

በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ዳሮለቡ ወረዳ ዳዳታ ሮታ ቀበሌ በወንድሙ ትዳር  ደስተኛ ያልሆነው እና መርዝ ልትሰጠኝ ሞክራለች በማለት በሜንጫ የግድያ ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በእስራት መቀጣቱ  የምዕራብ ሀረርጌ ዞን  ፖሊስ መምሪያ ገልጿል ፡፡

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ዋና ክፍል ኃላፊ ኮማንደር  ቱራ ለታ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን አንደተናገሩት ዘኮ አብዱላሂ የተባለው ተከሳሽ ከቤተሰቦቹ ሁሉ በተለየ ሁኔታ በሚቀርበው ወንድሙ ትዳር ደስተኛ እንዳልነበር እና በተደጋጋሚም በትዳራቸው ጣልቃ ይገባ የነበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወንድሙ ቀሽርቱ ይስባህ የተባለች ወጣት በአካባቢ ባህል መሰረት ሽማግሌ ልኮ ትዳር ቢመሰርትም ተከሳሽ ዘኮ በወንድሙ ትዳር  ጣልቃ ይገባ ነበር።በዚህም ሚስት ቀሽርቱ ደስተኛ እንዳልነበረች እና ለባለቤቷም ለምን በእኛ ትዳር ጣልቃ ይገባል በእኔ እና በአንተ መካካል ችግር ካለ እኛ ራሳችን ነን መፍታት ያለብን እሱ አንተን አልፎ እንዴት ይናገረኛል ብትልም ምንም አይነት መፍትሄ ማግኘት አለመቻሏ ተጠቁሟል፡፡

ይህ ችግር ሳይፈታ ተከሳሽ ዘኮ አብዱላሂ በድንገት የጤና ችግር ይገጥመዋል። ነገር ግን ወደ ህክምና አልሄድም የወንድሜ ሚስት መርዝ አብልታኛለች ለዛ ነው የታመምኩት በሚል ቂም ይይዛል። ተከሳሽ ታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም  የወንድሙን  ሚስት መንገድ  ላይ ጠብቆ በሜንጫ በመምታት  ህይወቷ እንዲያልፍ በማድረግ ከአከባቢው ለመሰወር ይሞክራል።

ፖሊስ ተከሳሹ ድርጊቱን ከፈፀመ በኃላ ብዙም ሳይርቅ በቁጥጥር ስር አውሎት ምርመራ ማድረግ ይጀምራል።አስከሬኑ ለምርመራ  ወደ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ተልኮ ከተጣራ በኋላ ዓቃቢ ህግ ክስ ይመሰርታል፡፡

የክስ መዝገቡን የተመለከተው የምዕራብ ሀረርጌ  ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምንም ማስረጃ ባልተረጋገጠበት መርዝ ያበላችኝ የወንድሜ ሚስት ናት በሚል የወንድሙን ሚስት መግደሉን ያረጋግጣል።

ተከሳሽ ጥፋተኛ መሆኑ በሰው እና በህክምና ማስረጃ በመረጋገጡ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ. ም በዋለው ችሎት በ16 ዓመት ከ6 ወር እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ያስተላለፈበት መሆኑን ኮማንደር  ቱራ ለታ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በኤደን ሽመልስ

photo_2024-01-30_10-06-19

ጥር 21፤2016 – የአሶሳ ከተማ  ነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት እንዳማረራቸዉ ገለፁ

 

የአሶሳ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አልበሽር መሀመድ ከበጋ ወቅቱ  ጋር ተያይዞ የውሃ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ እና የከተማው ስፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት መጨመሩ ችግሩን እንዳስከተለው ተናግረዋል።

ስማቸዉ እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንዳንድ  የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎቹ  መንግስት  አንድ ሊለን ይገባል ዉሃ የምናገኘዉ በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ነዉ ሲሉ ሃሳባቸዉን ለብስራት ቴሌቪዥንና ራዲዮ ገልፀዋል ።

በዚህም ምክንያት ዉሃ ለማግኘት እስከ 4 ስዓት ወረፋ እንደሚጠብቁ ሃሳባቸዉን ገልፀዉ ፣የዉሃ ስርጭቱ ፍትሐዊነት እንዳልሆነ ተናግረዋል።የእለት ከዕለት ኑሯቸዉን ለማስኬድ እጅግ እንደተቸገሩ ጨምረዉ ለጣቢያችን ገልፀዋል።

የአሶሳ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ዋና ሥራ አስኪያጅ  ከበጋ ወቅቱ  ጋር ተያይዞ የውሃ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ እና የከተማው ስፋት ጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ ለሁሉም  የከተማው ህዝብ ንፁህ የመጠጥ ውሀን ተደራሽ ማድረግ እንዳልተቻለ ጠቁመዋል። በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ለተከታታይ ሁለት ቀናት ተደራሽ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።

አቶ አልበሽር አክለው ዘላቂ የሆነ መፍትሔ እስከሚገኝ  ያለውን የውሃ ምርት በአግባቡ በመጠቀም ለሁሉም የከተማው ነዋሪ ማህበረሰብ በፍትሐዊነት ተደራሽ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ችግሩ እንዳለ አምኖ የአሶሳ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረትን በዘላቂነት ለመፍታት የሁሉም ባለድርሻ አካላት እገዛ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል ።

በበቀለ ጌታሁን

photo_2024-01-29_16-53-23

ጥር 20፤2016 – የውቅሮ ከተማ ምክር ቤት ከመጠን በላይ ድግስ ደጋሾችን ለመቅጣት የሚያስችል ህግ አፀደቀ

 

የውቅሮ ከተማ ም/ቤት የ4ኛ ዓመት 37ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ይህንኑ ህግ ማፅደቁን ብስራት ሬዲዮና ቴሌቨዥን ከትግራይ ምስራቃዊ ዞን ኮሚኒኬሽን ፅህፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያመላክታል።

ምክርቤቱ በመደበኛ ጉባኤው የፀጥታ ጉዳዮች፣ስራ አጥነት፣ድርቅና የንፁሕ መጠጥ ዉሀ እጥረት የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል። ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ ድግስ በሚል ሰበብ ከፍተኛ የሆነ ብክነት እየተስተዋለ ነው የተባለ ሲሆን እነዚህን ችግሮችን ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ እንደሚሰራየውቅሮ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉ ማሩ ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ህዝብ ከፍተኛ በሆነ ችግር ውስጥ እያለና  በድርቅ ወቅት ከመጠን ያለፈ ድግስ የሚደግሱ ሰዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ የውቅሮ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈትለወርቅ አበበ ገልፀዋል።

ነገር ግን ቅጣቱ ምንድን ነው ስለሚለው ጉዳይ የተገለፀ ነገር የለም።

በሚሊዮን ሙሴ

ጥር 20፤2016 – እኔ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ብሆን ኖሮ ወታደሮቻችን አይገደሉም ነበር ሲሉ ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ

 

በያዝነው አመት መጨረሻ ለሚካሄደው ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ ለመሆን የሚወዳደሩት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥቃቱ “ እኔ ፕሬዝዳንት ብሆን በጭራሽ አይከሰትም ነበር” ብለዋል።ትራምፕ ይህንን ይበሉ እንጂ በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸዉ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው ውጥረት ከባድ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከ2016 እስከ 2020 በነበራዉ የትራምፕ አገዛዝ በሶሪያ የሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎች አራት ወታደሮችን የገደለውን ጨምሮ ብዙ ጊዜ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

ኢራን በሶሪያ ዮርዳኖስ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ በተፈጸመዉ ጥቃት ሶስት የአሜሪካ ወታደሮችን ተገድለዉ 34ቱን ለቆሰሉበት የሰው አልባ አውሮፕላኖች ድብደባ እጄ የለበትም ስትል አስታዉቃለች።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥቃቱን የፈጸሙት በሶሪያ እና ኢራቅ በሚንቀሳቀሱት በኢራን የሚደገፉ ታጣቂ ቡድኖች ነው ብለዋል። “መልስ እንሰጣለን” ሲሉም ዝተዋል፡፡

በየመን የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ጄራልድ ፌየርስቴይን ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን ተጨማሪ ዉጥረት ከሚያባብስ ድርጊት እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል፡፡ የአሜሪካ አስተዳደር በአካባቢው በሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ እንዲያጠናክር ከፍተኛ ጫና እንደሚደርስበት ተናግሯል።ነገር ግን ፌይርስታይን አንዳንድ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ጥሪ እንዳደረጉት ፕሬዝዳንት ባይደን በኢራን ላይ ቀጥተኛ ጥቃት እስከማድረግ ድረስ መሄድ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የየመኑ አማፂ ቡድን የሁቲ ንቅናቄ እሁድ አመሻሹ ላይ በኤደን ባህረ ሰላጤ በሚገኝ የአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሙን አስታዉቋል።የወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪያ በሰጡት መግለጫ፥ በኢራን የሚደገፈው ቡድን የባህር ሃይል ኢላማ ያደረገ ጥቃትን አድርሷል፡፡

በስምኦን ደረጄ

Screenshot 2024-01-29 154404

ጥር 20፤2016 – በተለምዶ”ሿሿ” የተባለውን ወንጀል  ሲፈጽሙ የነበሩ ሦስት ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ ሲያዙ አንደኛዋ ወንጀል ፈፃሚ በክትትል መያዟን አዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ

ተጠርጣሪዎች ወንጀሉን የፈጸሙት ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 በተለምዶ ወሎ ሰፈር ሸዋ ሱፐር ማርኬት አካባቢ ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ ነው። ወንጀል ፈፃሚዎቹ  ኮድ 1- 09609 ትግ በሆነ ሚኒባስ ሁለቱ ሴቶች ተሳፋሪ አንደኛው ረዳት በመምሰል የግል ተበዳይ የሆነቸውን ወ/ት ሌሊሴ ያደታን ካሳፈሩ በኋላ አንደኛዋ ወንጀል ፈፃሚ ያመማት በመስመሰል  የግል ተበዳይ ላይ ምራቅ በመትፋት ሌሎቹ ደግሞ የሚጠርጉ መስለው ግምቱ 40ሺ ብር የሚያወጣ የእጅ ስልኳን ከሰረቁ በኋላ  ከመኪናው ላይ ገፍትረው በማስወረድ ያመልጣሉ፡፡

የግል ተበዳይ ያሰማችውን የድረሱልኝ ጥሪ የሰሙ በወንጀል መከላካል ስራ ላይ የነበሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት እና በአካባቢው በነበሩ ግለሰቦች ትብብር ሦስቱ ወንጀል ፈፃሚዎች ከግል ተበዳይ ከሰረቁት ሞባይል ስልክ እንዲሁም አንድ ሌላ ተጨማሪ ስልክ  እጅ ከፍንጅ እንደተያዙ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የላንቻ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አስታውቋል፡፡

ፖሊስ ባደረገው ክትትል እንደኛዋን ወንጀል ፈፃሚ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ መቀጠሉ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ደጋጋሚ መሆናቸውን መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ፖሊስ አስታውቋል።

ተመሳሳይ ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመከላከል ህብረተሠቡ ትራንስፖርት ሲጠቀም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው እና አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙ ለፀጥታ አካላት ማሳወቅ እንዳለበት ፖሊስ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

photo_2024-01-29_14-46-04

ጥር 20፤2016 – በደቡብ ሱዳን ወሬ ያበዛሉ በሚል በሀገሪቱ ሚኒስትር ስም የተሰየመው የጂን መጠጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል ተከለከለ

 

በደቡብ ሱዳን የመካከለኛው ኢኳቶሪያ ግዛት ባለስልጣናት በአካባቢው ለመጠጥነት የሚቀርበውን ጂን በርካቶች ከጠጡ በኃል ህይወታቻው በማለፉ ምርቱ እንዳይሸጥ አገዱ።

“ማኩኢ ጂን” በመባል የሚታወቀው ሮያል ጂን በአብዛኛው ወጣቶች ዘንድ ሱስ የሚያስይዝ ነው ተብሎ ተለይቷል። የገና እና የዘመን መለወጫ በዓላት ላይ የፍጆታ መጠኑ እየጨመረ በመምጣቱ ቁጥራቸው ላልተገለጸ ሰዎች የሞት ምክንያት ሆኗል ተብሏል።

ይህንኑ ተከትሎ ባለስልጣናት “ማኩኢ” የሚባለውን ሮያል ጂን የተባለውን ቀይ ቢራ ጥቅን ላይ እንዳይውል ከልክለዋል። የማዕከላዊ ኢኳቶሪያ ግዛት አስተዳዳሪ ኢማኑኤል አዲል አንቶኒ እንደተናገሩት ማንም ሰው መጠጡን መሸጥም ሆነ መጠጣት የለበትም ምክንያቱም ብዙ ወጣቶችን እየገደለ ነው ብለዋል።
በርካታ ወጣቶች ሲሰክሩ እናቶቻቸውን በገጀራ ይመታሉ ሲሉም አክለዋል። በዋና ከተማዋ ጁባ የሚገኘው የአንግሊካን ቤተክርስቲያን እገዳው ተግባራዊ ስለመሆኑ መንግስት እንዲያረጋግጥ አሳስቧል። ይህው ጂን በ 2019 ዓመት በማስታወቂያ ሚኒስትሩ ሚካኤል ማኩኢ ቅጽል ስም ተሰጥቶታል።

እኚህ ሚኒስትር በደቡብ ሱዳን ከሚገኙ ፖለቲከኞች በጣም ተናጋሪ ሚኒስትር በመሆናቸው ህዝቡ የጂን መጠጡን በእርሳቸው ስም ሰይሞታል። ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት ጂን ከገበያ እንዲታገድ ጠይቀው የሚያመርተው ፋብሪካ እንዲዘጋ ጥሪ አቅርበው ነበር።

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-01-29_15-31-16

ጥር 20፤2016 – በመኮሮኒ ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ ደብቆ ተጠርጣሪ ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሄደው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

 

ግለሰቡ ከናቢስ የተባለውን አደንዛዥ ዕፅ ይዞ በወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረ ጓደኛውን ለመጠየቅ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ያቀናል፡፡

ከክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረ ጓደኛውን ለመጠየቅ ምግብ ይዞለት የሄደው ይኸው ተጠርጣሪ ይህንኑ ተግባር ፈፅሟል፡፡

በወቅቱ በሳህን የተቋጠረው ምግብ እንጀራ ፍርፍር በማካሮኒ ነበር፡፡ በእነዚያ የማካሮኒ ቀዳዳዎች ውስጥ የሚያብለጨልጩ ነገሮች ተወታትፈዋል፡፡

ምግቡን ፈትሸው የሚያስገቡት የፖሊስ አባላት ባዩት ነገር ይጠራጠራሉ። ምግቡ ተዘርግፎ ሲፈተሽ ብዛቱ 51 የማካሮኒ ፍሬዎች በተጠቀለሉ የአልሙኒየም ወረቀቶች አባብጠዋል፡፡

ወረቀቶቹን በመፍታት ለማየት ሲሞከርም ካናቢስ የተባለው አደንዛዥ ዕፅ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ግለሰቡ ከዚህ በፊት በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ በዚያው ፖሊስ መምሪያ ታስሮ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ድፍረት በተቀላቀለበት ሁኔታ አደንዛዥ ዕፁን በምግብ ውስጥ ደብቆ ወደ ተጠርጣሪ ማቆያ ቤት ለማስገባት የሞከረው ጠያቂ ሰዎች የሚበዙበትን ሠዓት በማጥናትና የፖሊስ አባላት በዚያ ሰዓት ሊዘናጉ ይችላሉ ብሎ በማሰብ መሆኑም ታውቋል፡፡

በፈፀመው ወንጀል የምርመራ መዝገብ ተደራጅቶበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል፡፡