የካቲት 21፤2016 – የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ባለፉት ስድስት ወራት  ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

 

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከ5ሚሊየን በላይ የትራፊክ ፍሰት በማስተናገድ ከክፍያ መንገድ አገልግሎት እና ከልዩ ልዩ ገቢዎች ከ514 ሚሊዮን 6 መቶ 2 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን አስታውቃል፡፡

በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከታክስ በፊት ከ271 ሚሊየን ብር በላይ ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን ከባለፈዉ አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 27 በመቶ የትርፍ እድገት ለማስመዝገብ መቻሉን የኢንተርፕራይዙ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ስንታየው መኮንን ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

የኢንተርፕራይዙ የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያዉ ስድስት ወራት የትርፍ አፈፃፀም ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር 111 በመቶኛ ማስመዝገብ መቻንም ገልጻል፡፡በመንገዶቹ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አገልግሎት እየሰጠ እና የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብ እየሰራ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ስንታየው ያሉትን ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ በማስቀጠል፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችና የሚስተዋሉ ድክመቶችን ለመቅረፍ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ያለውን የሰው ኃይል በዕውቀትና በክህሎት በማሳደግ፣ የአሰራር ስልቶችን በማሻሻል በስፋት እየተቀሳቀሱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡የመንገዱን ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ በተለያዩ ቦታዎች ሰፊ የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት በማስተማር እና በመንገዱ ክልል ውስጥ የ24 ሰዓት የመንገድ ላይ ቅኝታዊ ቁጥጥር ኢንተርፕራይዙ እያደረገ መሆኑንም ተገልጻል፡፡

ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የትራፊክ አደጋ በ15 በመቶ መቀነስ የተቻለ ሲሆን በትራፊክ አደጋ የሚደርስ የሞት መጠን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ25 በመቶ መቀነስ ተችላል ተብላል፡፡

በትግስት ላቀዉ

Screenshot 2024-02-26 202636

የካቲት 18፤2016 – አዛዉንቶቹ የደቡብ ኮሪያ ሴት ራፕሮች የህይወት ጉዞ አድናቆት ተችሮታል

 

ሱኒ እና ሰባቱ ልዕልቶች በ70ዎቹ እና 80 ዎቹ ውስጥ የእድሜ ክልል ዉስጥ በሚገኙ ደቡብ ኮሪያውያን አያቶች የተዋቀረ ታዋቂ የራፕ ቡድን ነው።

በደቡብ ኮሪያ ሰሜን ጂዮንግሳንግ ግዛት ውስጥ ከሚገኘው የቺልጎክ ገጠር መንደር የመጡ አረጋውያን ሴቶች የራፕ ቡድን እንደ እዉቅናቸዉ እየጨመረ በመምጣቱ ዓለም አቀፍ አርዕስተ ዜና እያደረጋቸዉ ይገኛል፡፡ ሱኒ እና ሰባቱ ልዕልቶች ባለፈው አመት ላይ ነሀሴ ወር ላይ የጀመሩት ነገር ግን ያልተለመደው የራፕ ቡድን አሁን በመላው አለም እየታወቀ ይገኛል፡፡

የሴት አያቶች ቡድኑ አባላት ሰፋፉ ሱሪና ሹራብ አንገታቸው ላይ ሰንሰለት በማድረግ ስለገጠር አኗኗራቸው በተለይም በደቡብ ኮሪያ ገጠራማ አካባቢ ስለሚሰዋለዉ ነገር በራፕ ያቀነቅናሉ፡፡ስምንቱ የቡድኑ አባላት ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚተዋወቁ ሲሆን ነገርግን የራፕ ቡድን ለመመስረት የወሰኑት ባለፈው አመት ነበር። በገጠር ውስጥ ማደጋቸዉ ትምህርት ለመከታተል እድል አልሰጣቸዉም ነበር፡፡

በ 2016 መጨረሻ የኮሪያ ፊደል የሆነዉን ሃንጉል ማንበብ እና መጻፍ ለመማር ወሰኑ፡፡አንድ ቀን የ 81 ዓመቷ የራፕ ቡድኑ መሪ ፓርክ ጆ ኦም ሰን በኢንተርኔት ላይ የራፕ ቪዲዮ ይመለከታሉ፡፡የሀንጉል መምህራቸውን አሳምነው እንዴት ራፕ ማድረግ እንደሚችሉ እንዲያስተምሯቸዉ አድርገዋል፡፡ሱኒ እና ሰባቱ ልዕልቶች ሐብሐብ መልቀም እና ሌሎች የገጠር አኗኗራቸውን የሚገልጹ ግጥሞችን መግጠም ጀመሩ፡፡

ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ የራፕ ትርኢትያቸውን በትምህርት ቤት ጨዋታ ላይ አሳይተዋል። ዘመናዊ አልባሳት እና የአንገት ጌጣጌጦችን እንደ ሰንሰለት ከመጠቀም ባለፈ እንደ ታዋቂ ራፐረፐች አስቂኝ የእጅ ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሱኒ እና ሰባቱ ልዕልቶች በደቡብ ኮሪያ መድረኮች እና በተለያዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በስፋት መታየት ጀመሩ፡፡

እርጅና ላይ ብሆንም እንኳን ደስ ብሎናል የምትለዉ የቡድኑ መሪ ሱኒ ወጣት እንደሆንን ይሰማናል ስትል ተናግራለች።ሱኒ እና ሰባቱ ልዕልቶች በእስያ ውስጥ አርዕስተ ዜና የሆኑ ሲሆን ዓመት፣ አባላቱ ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸውን ጂ-ፖፕ የተባለ የወንድ ባንድ ቡድን እዉቅና ማግኘቱ ይታወሳል፡፡

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-02-26_09-44-56

የካቲት 18፤2016 – ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ከከፈተችበት ጊዜ አንስቶ 31 ሺ የዩክሬን ወታደሮች መገደላቸው ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ተናገሩ

 

ፕሬዝዳንት ቮልዲሚር ዘለንስኪ ሩሲያ ባካሄደችው አጠቃላይ ወረራ 31 ሺ የዩክሬን ወታደሮች ተገድለዋል ሲሉ አስታውቀዋል። የዩክሬን ፕሬዝዳንት በውጊየው የቆሰሉትን ወታደሮች ቁጥር  ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል። የዩክሬን ባለስልጣናት የተጎጂዎችን ቁጥር በይፋ የማይናገሩ ሲሆን ሌሎች ግምቶች ግን የተጎጂዎች ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

የፕሬዝዳንቱ መረጃ የተሰማው የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትሩ ለዩክሬን ምዕራባውያኑ የሚሰጡት ዕርዳታ ግማሹ በመዘግየቱ የሕይወት ዋጋ እያስከፈለን ነው ካሉ በኋላ ነው።የዘሌንስኪ መግለጫ የተጋነነ የዩክሬን ወታደሮች ሞት በሩሲያ በኩል ለተሰጠው አሃዝ ምላሽ እንደሆነ ተሰምቷል። “በዚህ ጦርነት 31,000 የዩክሬን ወታደሮች ሞተዋል። ሩሲያ እንደምትለው 300 ሺ ወይም 150 ሺ አይደሉም ፑቲን የሚናገሩት ውሸት ነው” ሲሉ አክለዋል።

በጦርነቱ ውስጥ ስላለው ሰፊ ኪሳራ የተናገሩት ዘለንስኪ እንዳሉት በሩስያ በተያዙት የዩክሬን አካባቢዎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሀን ዜጎች ሞተዋል ነገር ግን ትክክለኛው ቁጥራቸው አይታወቅም ሲሉ አክለዋል። “ስንቶቹ እንደተገደሉ፣ ስንቶች እንደተሰቃዩ እና ስንቶቹ እንደተሰደዱ አላውቅም ብለዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት በነሀሴ ወር የተገደሉ የዩክሬን ወታደሮች ቁጥር ከ70 ሺ እስከ 120 ሺ ሊደርስ እንደሚችል ማሳወቁ ይታወሳል።

ዩክሬን ከደረሰባት ኪሳራ ሩሲያ የከፋ ነው ያሉት ዘሌንስኪ 180 ሺ የሩስያ ወታደሮች መሞታቸውን እና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ መቁሰላቸውን ተናግረዋል። የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር በበኩሉ 350 ሺ ወታደሮች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን አንስተዋል።ባለፈው ሳምንት የዩክሬን ወታደሮች ከምስራቃዊ ቁልፍ ከሆነችው አቪዲቪካ ከተማ ለቀው መውጣታቸው የሚታወስ ሲሆን ለሩሲያ በጦርነቱ ከወራት በኋላ የተመዘገበ ትልቁ ድል ነው።

ዘለንስኪ በከፊል የምዕራባውያን የጦር መሳሪያ አቅርቦትን በመዳከሙ የመጣ ሽንፈት ነው ሲሉ ወቅሰዋል። የባይደን አስተዳደር በበኩሉ ለዩክሬን የ 60 ቢሊዮን ዶላር የእርዳታ ፓኬጅ በኮንግረሱ መቆየቱ ለከተማይቱ በሩሲያ እጅ መያዝ አስተዋጽኦ አድርጓል ብሏል። ሩሲያ ሙሉ በሙሉ ወረራ ከጀመረች ሁለት ዓመታት ማስቆጠሯን ተከትሎ የምዕራባውያን ሀገራት መሪዎች ከዩክሬን ጋር ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ቅዳሜ ወደ ኪየቭ ተጉዘዋል። በዚህም መሰረት ጣሊያን እና ካናዳ ከዩክሬን ጋር የጸጥታ ስምምነት መፈራረማቸው ተነግሯል።

በስምኦን ደረጄ

Screenshot 2024-02-26 083127

የካቲት 18፤2016 – በጉራጌ ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የስድስት  ሰዎች ህይወት አለፈ

 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን በመስቃን ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ገልጿል።

በመስቃን ወረዳ  ጆሌ ቀበሌ ዲራማ ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ ትላንት እሁድ ከቀኑ 10 :00 ሰዓት ላይ አደጋ መድረሱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ መምሪያ የሚዲያ ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጅራ ይጓዝ የነበረ ተሳቢ ከባድ ተሽከርካሪ ሰባት ሰዎችን ካሳፈረ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ በተለምዶ ባጃጅ ታክሲ ጋር በመጋጨቱ የአምስት ሰዎች ህይወት ወዲያዉኑ  አልፏል።

ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዉ ወደ ወራቤ ሪፈራል ሆስፒታል ከተላኩ ሁለት ሰዎች መካከል ደግሞ  የአንዱ ህይወት በማለፉ በአደጋዉ በአጠቃላይ የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ገልፀዋል።

አንድ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ተጎጂ  በወራቤ ሪፈራል ሆስፒታል በህክምና እየተረዳ ይገኛል።በአደጋዉ ህይወታቸዉ ካለፈዉ ስድስቱ ሰዎች ሶስት ሴቶችና ሶስት ወንዶች  ናቸው። የአደጋዉ መንስኤ  እየተጣራ መሆኑን  ም/ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቭዥን ጨምረው ተናግረዋል።

በምህረት ታደሰ

photo_2024-02-23_10-09-04

የካቲት 15፤2016 -የአንጋፋው ድምጻዊ ጌታቸው ካሣ የቀብር ሥነ ስርዓት ዛሬ ከቀኑ በ 8 ሰዓት ላይ ይፈጸማል

 

የድምጻዊ ጌታቸው ካሣ የቀብር ሥነ ስርዓት በዛሬዉ እለት የካቲት 15 ቀን 2016 ከቀኑ በ8 ሰዓት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ይፈፀማል።

ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ አስቀድሞ ከቀኑ ስድስት ሰዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የስንበት መርሐ ግብር እንደሚካሄድ ተነግሯል። በስንበት መርሐ ግብሩ ላይ የአጋፋው ድምጻዊ ጌታቸው ካሣ የሕይወት ታሪክ ቀርቦ የሞያ አጋሮቹ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጥ ሥነ ስርዓት እንደሚካሄድም ታዉቋል።

የካቲት 12፤2016 –ወደ አሜሪካ ለመግባት ሲሉ ሜክሲኮ የሚመጡ አፍሪካውያን ቁጥር በዘጠኝ እጥፍ መጨመሩ ተሰማ

 

ባለፈው 2023 አመት ሜክሲኮ የደረሱት የአፍሪካ ስደተኞች ቁጥር ካለፈው 2022 ዓመት ጋር ሲነፃፀር በዘጠኝ እጥፍ ብልጫ እንዳለው ይፋ አኃዛዊ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሳምንቱ መጨረሻ የሜክሲኮ የሀገር ውስጥ ዲፓርትመንት ያወጣው አሃዝ እንደሚያሳየው እ.ኤ.አ. በ2023 ወደ 60,000 የሚጠጉ ስደተኞች ከአፍሪካ ወደ ሜክሲኮ መጥተዋል።ካለፈው 2022 አመት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ብልጫ ያለው ሲሆን በወቅቱ 6,500 አፍሪካውያን ወደ ሜክሲኮ መጥተው ነበር።

በሜክሲኮ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ራ አለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ተልዕኮ ኃላፊ ዳና ግራበር ላዴክ እንደተናገሩት ከእነዚህ ስደተኞች አብዛኞቹ ከጊኒ፣ አንጎላ፣ ሞሪታኒያ፣ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ እና ካሜሩን የመጡ ናቸው። ኃላፊዋ ዳና ግራበር አክላ እንደተናገረችው ሰዎች አገራቸውን የሚለቁት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ በማለት በሀገራት ከሚያጋጥሙ ከአጠቃላይ ሁከት እስከ አስከፊ ድህነት ብሎም ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና ውጣ ውረድ የበዛበት ውስብስብ ችግሮች ዋንኛ ተጠቃሽ ናቸው ብላለች።

በእርግጥ የአየር ንብረት ለውጥ እና የተፈጥሮ አደጋዎች የራሳቸው ተፅእኖ እንዳላቸው ሊታሰቡ እንደሚገባም ገልፃለች። እ.ኤ.አ በ2023 ሜክሲኮ የደረሱት አብዛኞቹ አፍሪካውያን ስደተኞች በሜክሲኮ ውስጥ ተረጋግተው ህይወት መመስረት እንደማይፈልጉ እና ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ድንበር ለመሻገር ዋንኛ ግባቸው እንደሆነ ወይዘሮ ግራበር ዳና ተናግረዋል።

በርካታ ስደተኞች ወደ ሜክሲኮ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲያመቻቹላቸው ለሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች የሚከፍሉ ሲሆን፥ ጉዞውም ከ10,000 እስከ 20,000 የአሜሪካን ዶላር አካባቢ እንደሚፈጅ መረጃዎች ያመላክታሉ።በ2023 የበጀት ዓመት ወደ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች የአሜሪካ-ሜክሲኮን ድንበር አቋርጠዋል።

ወደ 300 ሺ የሚጠጉ ስደተኞች ደግሞ በታህሳስ ወር ከየትኛውም ወር በላይ በዩናይትድ ስቴትስ ድንበር ጠባቂዎች ተይዘዋል። አብዛኛዎቹ ሰዎች ጥገኝነት የሚጠይቁ ሲሆን ይህም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንዲቆዩ የሚፈቅድላቸው ሁኔታ እስኪመቻች ድረስ ዓመታትን ሊስቆጠረ ይችላል።

በስምኦን ደረጄ

new_flyer_ev_bus_in_winnipeg_manitoba

የካቲት 12፤2016 – በአዲስ አበባ ከተማ በዛሬዉ እለት የኤሌክትሪክ ሚኒባሶች የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

 

በአዲስ አበባ ከተማ አዳዲስ የኤሌክትሪክ ሚኒባሶች የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡ቢሮው የሕዝብ ትራንስፖርት አቅርቦትን ለማሻሻልና ተደራሽ ለማድረግ የግል ባለሃብቱ ወደ ትራንስፖርት ዘርፉ እንዲቀላቀል እድል መፈጠሩን አስታውሷል፡፡

በዚህ መሰረትም ዛሬ 20 አዳዲስ የኤሌክትሪክ ሚኒባስ ታክሲዎች የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ነው የተገለጸው፡፡ታክሲዎቹ በነበረው የስምሪት መስመርና ታሪፍ ከቦሌ-በሚሊኒየም-በስቴድዮም-ሜክሲኮ (ቡናና ሻይ ) እና ከቦሌ-በሚሊኒየም-በጊዮን_ፒያሳ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተጠቅሷል፡፡

የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን በዘመናዊ የኤሌክትሪክ መኪናዎች መሰጠቱ የሕዝብ ትራንስፖርት አቅርቦቱን እንደሚያሻሽል የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡በተጨማሪም የበካይ ጋዝ ልቀት በመቀነስና ከተማዋን የሚመጥንና ውብ ገፅታ ከመገንባት አንፃር የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የካቲት 8፤2016 – ዳቦ ለመግዛት ሱቅ የተላከውን የ8 ዓመት ልጅ አግተው ቤተሰቦቹን 1ሚሊዮን ብር የጠየቁ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

 

በሸገር ከተማ አስተዳደር ሱሉልታ ክፍለ ከተማ ዳቦ ለመግዛት ሱቅ የተላከውን የ8 ዓመት ህፃን ልጅ አግተው በመውሰድ ወላጆቹን 1ሚሊየን ብር የጠየቁ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሱሉልታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የሱሉልታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ዋና ክፍል መርማሪ ም/ኢንስፔክተር ተርፌሳ ነጋሳ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት የወንጀል ድርጊቱ ጥር 8 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 1፡30 ላይ ተፈጽሟል፡፡ ዳቦ ለመግዛት ሱቅ የተላከው የ8 ዓመት ታዳጊ የእናቱ የቅርብ ዘመድ የሆነች ግለሰብ ችብስ እገዛልሀለው በማለት ወደ ጫንጮ ከተማ በድብቅ አንድ ቤት ውስጥ አግታ ወስዳዋለች፡፡

ተጠርጣሪዋ ግለሰብ ከሌሎች አራት ግብራበሮቿ ጋር በመሆን ያገቱትን የ8ዓመት ልጅ ከጫንጮ ከተማ ወደ ምዕራፍ ሸዋ ዞን ኤጀርሳ ለፎ በተባለ ወረዳ በድብቅ እንዳስቀመጡት ታዉቋል፡፡አንደኛ ተጠርጣሪ እና የታገተው ልጅ የቅርብ ዘመድ የሆነችው በምስራቅ ሸዋ ዞን አጀርሳ ለፎ ወረዳ ለሁለተኛ ተጠርጣሪ አስረክባ ወደ ሱሉልታ በመመለስ ሁኔታውን ስትከታተል እንደነበር ታውቋል፡፡

ሌሎች አራቱ ተጠርጣሪዎችም በተለያዩ ጊዜያት ለ8 ዓመቱ ልጅ እናት በመደወል 1ሚሊየን ብር በአስቸኳይ ካላመጣሽ ልጅሽን በህይወት አታገኚውም ብለው በማስፈራራታቸው ጉዳዩን ለፖሊስ ማሳወቋንም ተናግረዋል፡፡ፖሊስ ባደረገው ክትትል አንደኛ ተጠርጣሪ በጫንጮ ከተማ በቁጥጥር ስር ውላ የጠቆመቻቸው አራቱ ተጠርጣሪዎችም ካገቱት የ8 ዓመት ታዳጊ ልጅ ጋር በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጀርሳ ለፎ ወረዳ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

የሱሉልታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ተጠርጣሪዎቹ ላይ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ ለዓቃቢ ህግ የላከ ሲሆን በቅርብ ጊዜያትም በ5 ተጠርጣሪዎች ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥ የሱሉልታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ዋና ክፍል መርማሪ ም/ኢንስፔክተር ተርፌሳ ነጋሳ ጨምረው ለብስራት ሬድዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በምህረት ታደሰ

Screenshot 2024-02-13 181417

የካቲት 5፤2016 – በፍቺ የተለያትን የቀድሞ ሚስቱን በቅናት በመነሳሳት የገደለው ተከሳሽ በእስራት ተቀጣ

 

በምስራቅ ቦረና ዞን መደወላቡ ወረዳ መደሃሊቦ ቀበሌ በፍቺ የተለያትን የቀድሞ ሚስቱን በስለት ወግቶ የገደለው ተከሳሽ በእስራት መቀጣቱ ተገልጿል፡፡

ተከሳሽ አብዱራህማን ሀሰን የሁለት ልጆቹ እናት  እና   ባለቤቱ የነበረቸው የቀድሞ ሚስቱ  ላይ ባደረበት የቅናት  ስሜት ተገፋፍቶ በስለት  ዘግናኝ በሆነ መልኩ ገድሎ ለማምለጥ የሞከረ መሆኑን  የምስራቅ ቦረና ዞን ፖሊስ መምሪያ ሴቶች እና ህጻናት ጉዳዮች ጽ/ ቤት  ወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ሶሶቤ ደጀኔ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

ተከሳሹ ለይላ መሃመድ  የተባለች  ሴት  ጋር ተጋብተው ሁለት ልጆችን ማፍራት ችለው የነበረ ቢሆንም ባለቤቷ ባደረበት የቅናት ስሜት  መግባባት ባለመቻላቸው  ልጆቿን ይዛ ወደ ቤተሰቦቿ ሄዳ የነበረ መሆኑም ተነግሯል፡፡ በዚህም ደስተኛ አለመሆኑን እና ሚስትም በፍርድ ቤት ፍቺ እንዲጸድቅ አድርጋ የፍቺ ሂደት እንዳጠናቀቁ ተረጋግጧል፡፡

ነገረ ግን በፍቺው ደስተኛ ያልነበረው አብዱራህማን ሀሰን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዋን መከታተልን ስራዉ ያደርጋል፡፡ ጥር 6 ቀን  2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት ላይ  ከሱቅ እቃ ገዝታ ስትመለስ እቤት  ውስጥ ማንም አለመኖሩን አረጋግጦ በአጥር ዘሎ በመግባት በግል ተበዳይ የቤተሰብ ቤት ዉስጥ ይደበቃል ፡፡

ከዛም ሟች ለይላ ወደ መጸዳጃ ቤት ስታመራ  ከተደበቀበት ወጥቶ በያዘው ስለታም ቢላዋ አንገቷን ወግቶ  ህይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል።  ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ  ለመሰወር የሞከረ ቢሆንም  በሞተር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ  በቁጥጥር  ስር ውሏል፡፡

ድርጊቱን ሲከታተል የቆየው ፖሊስ ተከሳሽ የ35 ዓመቷን ተበዳይ እና የሁለት ልጆቹን እናት መግደሉን በህክምና እና በሰው ማስረጃ ያሟላ በመሆኑ  የምስራቅ ቦረና ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት  ጥር 28 ቀን 2016 ዓ. በዋለው ችሎት በተከሳሽ አብዱራህማን ሃሰን ላይ በ23 ዓመት እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ማሳለፉን ረዳት ኢንስፔክተር ሶሶቤ ደጀኔ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጨምረዉ ተናግረዋል ።

በኤደን ሽመልስ

Screenshot 2024-02-12 185954

የካቲት 4፤2016 – የግል ተበዳይ ላይ ጉዳት በማድርስ ሞባይል ስልክና 4ሺ ብር የቀሙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ዋሉ

 

ብሩክ አበበ ፣ ሙሉጌታ ሀይሉ እና መኳንንት የኔዓለም የተባሉ ሦስት ወንጀል ፈፃሚዎች ጥር 17 ቀን 2016 ዓ/ም ምሽት 12 ሠዓት  በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው ካራቆሬ መድሃኒያለም ቤተ ክርስቲያን ጀርባ አካባቢ የግል ተበዳይ አቶ ተስፋዬ ግርማን በማስፋራራት እና ጭንቅላታቸው ላይ ጉዳት በማድርስ ግምቱ 27 ሺ ብር የሚያወጣ ሳምሰንግ ሞባይል ስልክና 4ሺብር ቀምተው ለማምለጥ ሲሞክሩ በስራ ላይ በነበሩ የፖሊስ የክትትል አባላት አማካኝነት ብሩክ አበበ የተባለው እጅ ከፍንጅ መያዝ ተችሏል፡፡

ከወንጀል ፈፃሚው እጅ የግል ተበዳይ ስልክና መንጃ ፈቃድ መገኘቱን በኮልፌ ቀራኒዩ ክፍለ ከተማ ፖሊስ የካራ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ም/ኢ/ር ተመኙ ያለ ገልፀዋል፡፡ሙሉጌታ ሀይሌ እና መኳንንት የኔዓለም የተባሉት ወንጀል ፈፃሚዎች ወደ ገደል ዘለው በመግባት ያመለጡ ቢሆንም ሲዘሉ ጉዳት የደረሰባቸው በመሆኑ  ህክምና ለማግኘት ጥረት እያደረጉ መሆኑን  ፖሊስ በደረሰው መረጃ መሰረት ወንጀል ፈፃሚዎቹ አለርት ሆስፒታል ሲታከሙ በቁጥጥር ውለዋል። ከግለሰቡ ላይ የተሰረቀው 4ሺ ብር በኤግዚቢትነት መያዙን ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ፖሊስ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ወንጀሉን በፈፀሙ በሰዓት እድሜ ውስጥ በቁጥጥር አውሎ እና ንብረታቸው በማስመለሱ የተሰማቸውን ደስታ የገለፁት አቶ ተስፋዬ ግርማ ፖሊስ በሥውር የሚያደርገው ጥበቃ ለዚህ ውጤት እንዳበቃው መገንዘባቸውን ጠቁመው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ፖሊስ ጣቢው ባከናወነው ምርመራ የማስፋት ስራ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ/ም ወረዳ 2 ልዩ ስፍራው  ቻይና የድንጋይ ጠጠር መፍጫ አካባቢ  እና ጥር 12 ቀን 2016 ዓ/ም በተመሳሰይ ስፍራ ወንጀል ፈፃሚዎቹ  ከሁለት ግለሰቦች የቀሙትን ሁለት ስልኮች አስመልሷል።

ፖሊስ ግለሰቦቹ  ላይ ክስ እንዲመሰረት ምርመራውን አጠናቆ መዝገቡን ለአቃቢ ህግ መላኩን ከኃላፊው ገለፃ መረዳት ተችሏል፡፡