በኢትስዊች እና በጀነሲስ አናሊቲክስ መካከል የ15 አመት እና የአምስት አመት መሪ እቅድ ለመቅረፅ ያለመ ስምምነት ተካሂዷል።
የኢትስዊች ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ይለበሰ አዲስ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት አንድ ተቋም ስራውን ለማከናወን የራሱ ስትራቴጂ፣ስልት እንዲሁም ፍኖተ ካርታ ያስፈልገዋል።
ኢትስዊች አ.ማ ከዚህ ቀደም የነበረውን የአምስት አመት ስትራቴጂ ማጠናቀቁን ገልፀው ቀጣዮን ስትራቴጂ ሊያዘጋጁለት የሚችሉ የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶችን አወዳድሯል ብለዋል።
በዘርፋ በቂ ልምድና ክህሎትን ካዳበረውና በበርካታ ሀገራት ላይ እንዲህ ያሉ ስራዎችን ከሚሰራው ከጀነሲስ አናሊቲክስ ተቋም ጋር ኢትስዊች ተፈራርሟል ሲሉ ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።
በሰው ሀይል፣በቴክኖሎጂ ረገድ አክሲዮን ማህበሩ በሚሰጣቸው መሰረተ ልማቶችን ታሳቢ ያደረገ አገልግሎት በብሄራዊ ስዊች ደረጃ ምን መሟላት አለባቸው የሚለውን ገምግሞ ስትራቴጂ እንዲያዘጋጅ ይህ ስምምነት ከተቋሙ ጋር ተከናውኗል።
ስምምነቱ በዲጂታል ስርአቱ በተለይም በፋይናንሱ አለም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው ደንበኞች ክፍያዎችን በቀላሉ መፈፀም እንዲችሉ ያግዛቸዋል በማለት አብራርተዋል።
ኢትስዊች አ.ማ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ በሁሉም የግል እና የመንግስት ባንኮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክን ጨምሮ የተቋቋመ ብሄራዊ ስዊች ነው።
በቅርቡ የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት፣የክፍያ ስርአት ኦፕሬተሮች እና የክፍያ መፈፀም ሰነድ አውጪዎች በባለቤትነት ተቀላቅለውታል።
በቅድስት ደጀኔ
