photo_2025-12-19_15-50-10

ታህሳስ 10፤2018 – ኢትስዊች “ኢትዮ ፔይ” የተሰኘ አዲስ ብራንድ አስተዋወቀ

ታህሳስ 10፤2018 – ኢትስዊች “ኢትዮ ፔይ” የተሰኘ አዲስ ብራንድ አስተዋወቀ

ኢትስዊች አክሲዮን ማህበር የሀገሪቱን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችል “ኢትዮ ፔይ” (EthioPay) የተሰኘ አዲስ ብራንድ አስተዋውቋል::

የኢትስዊች አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አሥፈጻሚ የሆኑት አቶ ይለበስ አዲስ እንደተናገሩት ይህ ኢትዮ-ፔይ የተሰኘ የክፍያ መተግበሪያ የዲጂታል ግብይቶችን በአንድ መለያ (ብራንድ) እንዲከናወኑ የሚያደርግ ነው።

ኢትስዊች በፋይናንስ ዘርፉ የዲጂታል ክፍያ ሥነ-ምህዳር ተናባቢ እንዲሆን በማድረግ ታላቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ ተቋም መሆኑን አቶ ይለበስ ገልፀው ይፋ የሆነው ብራንድ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ስርአት በራስ አቅም መምራት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ኢትስዊች አ.ማ. ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ በሁሉም የግል እና የመንግስት ባንኮች እንዲሁም የአትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ የተቋቋመ ብሔራዊ ስዊች ነው።

በቅርቡም የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት፣ የክፍያ ስርዓት አፕሬተሮች እና የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድ አውጪዎች በባለቤትነት መቀላቀላቸው ተነግሯል።

ዋና አላማውም በፋይናንስ ተቋማት መካክል በዲጂታል አማካኝነት የሚደረጉ ግብይቶችን ተናባቢ ማድረግ፣ የሀገር ውስጥ የክፍያ ስርዓትን ማቅረብ፣ የብሔራዊ ክፍያ ጌትዌይ አገልግሎትን መስጠት፣ ለፋይናንስ ተቋማት የጋራ መሠረተ ልማት እና ሲስተሞችን መዘርጋትን ጨምሮ ሌሎችንም ያካትታል።

“ኢትዮ ፔይ” በየትኛውም የፋይናንስ ተቋም የታቀፉ ደምበኞች ከየትኛውም የፋይናንስ ተቋም ወደ ሌላ የፋይናንስ ተቋም ገንዘብ በቀላሉ እንዲልኩ እና እንዲቀበሉ የሚያችል ሀገር አቀፍ ብራንድ መሆኑ ተመላክቷል።

ቅድስት ደጀኔ

ህዳር 19፤2018 – ኢትስዊች የ15 አመት እና የአምስት አመት መሪ እቅድ ለመቅረፅ የሚያስችለውን ሰምምነት ከጀነሲስ አናሊቲክስ ጋር ተፈራረመ።

በኢትስዊች እና በጀነሲስ አናሊቲክስ መካከል የ15 አመት እና የአምስት አመት መሪ እቅድ ለመቅረፅ ያለመ ስምምነት ተካሂዷል።

የኢትስዊች ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ይለበሰ አዲስ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት አንድ ተቋም ስራውን ለማከናወን የራሱ ስትራቴጂ፣ስልት እንዲሁም ፍኖተ ካርታ ያስፈልገዋል።

ኢትስዊች አ.ማ ከዚህ ቀደም የነበረውን የአምስት አመት ስትራቴጂ ማጠናቀቁን ገልፀው ቀጣዮን ስትራቴጂ ሊያዘጋጁለት የሚችሉ የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶችን አወዳድሯል ብለዋል።

በዘርፋ በቂ ልምድና ክህሎትን ካዳበረውና በበርካታ ሀገራት ላይ እንዲህ ያሉ ስራዎችን ከሚሰራው ከጀነሲስ አናሊቲክስ ተቋም ጋር ኢትስዊች ተፈራርሟል ሲሉ ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።

በሰው ሀይል፣በቴክኖሎጂ ረገድ አክሲዮን ማህበሩ በሚሰጣቸው መሰረተ ልማቶችን ታሳቢ ያደረገ አገልግሎት በብሄራዊ ስዊች ደረጃ ምን መሟላት አለባቸው የሚለውን ገምግሞ ስትራቴጂ እንዲያዘጋጅ ይህ ስምምነት ከተቋሙ ጋር ተከናውኗል።

ስምምነቱ በዲጂታል ስርአቱ በተለይም በፋይናንሱ አለም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው ደንበኞች ክፍያዎችን በቀላሉ መፈፀም እንዲችሉ ያግዛቸዋል በማለት አብራርተዋል።

ኢትስዊች አ.ማ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ በሁሉም የግል እና የመንግስት ባንኮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክን ጨምሮ የተቋቋመ ብሄራዊ ስዊች ነው።

በቅርቡ የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት፣የክፍያ ስርአት ኦፕሬተሮች እና የክፍያ መፈፀም ሰነድ አውጪዎች በባለቤትነት ተቀላቅለውታል።

በቅድስት ደጀኔ

photo_2025-11-25_09-49-51

ህዳር 15፤2018 – ኢትስዊች እና ማስተርካርድ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የክፍያ አቅምን ለማስፋት ያለመ ስምምነት ተፈራረሙ

ኢትስዊች እና ማስተርካርድ የኢትዮጵያን ዲጂታል የክፍያ ሥነ-ምህዳር ለማሳደግ እና ሀገሪቱ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ አውታረ መረብ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ አዲስ የንግድ ስምምነት በዛሬው እለት ተፈራርመዋል።የኢትስዊች ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ይለበሰ አዲስ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት ይህ ሽርክና በኢትዮጵያ ዲጂታል ለውጥ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን የቀጣይ ትውልድ የክፍያ መፍትሄዎችን ያስተዋውቃል ሲሉ የተናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው የፋይናንስ ሥነ-ምህዳራችንን ደህንነት እና የመቋቋም አቅም በእጅጉ ያጠናክራል ብለዋል። ስምምነቱ በመላ አገሪቱ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማትን፣ ንግዶችን እና ሸማቾችን የሚጠቅሙ ፈጠራ ያላቸው፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው የክፍያ መፍትሄዎችን ለማስተዋወቅ የጋራ ቁርጠኝነትን ያንፀባርቃል።

በዚህ አጋርነት ስር ማስተርካርድ እና ኢትስዊች የተለያዩ ዓለም አቀፍ የክፍያ ችሎታዎችን ለማሰስ እና ተግባራዊ ለማድረግ አብረው ይሰራሉ።ሽርክናው ኢትስዊች በማስተርካርድ ኔትወርክ እና በማስተርካርድ ዓለም አቀፍ የክፍያ መግቢያ አገልግሎቶች በኩል በቀጥታ ግንኙነት እንዲኖረው ያደርጋል የተባለ ሲሆን ይህም በማስተርካርድ የምክር አገልግሎቶች የተደገፈ መሆኑ ተገልጿል።ይህም የኢትዮጵያ ንግዶች ዓለም አቀፍ ክፍያዎችን እንዲቀበሉ እና ለድንበር ተሻጋሪ ንግድ እድሎችን እንዲያሰፉ ያስችላቸዋል ተብሏል።

በተጨማሪም በዚህ ትብብር የኢትዮጵያ ባንኮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለምንም እንከን የሚሰሩ እና በኤቲኤሞች፣ በፖስ ተርሚናሎች እና በኦንላይን ነጋዴዎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን የሚያቀርቡ የጋራ ብራንድ ያላቸው የቅድመ ክፍያ የጠንካራ ምንዛሬ ካርዶችን እንዲያወጡ ይፈቀድላቸዋል።

በቅድስት ደጀኔ

photo_2025-10-29_11-01-12

ጥቅምት 19፤2018 – ኢትስዊች ከታክስ በፊት 1.42 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ

ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ34 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል

ኢት ስዊች ይህን ያለው በዛሬው እለት 12ኛውን አመታዊ የባለአክሲዮኖች አጠቃላይ ስብሰባ ባካሄደበት ወቅት ላይ ነው።የኢትስዊች የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሰሎሞን ደስታ በመክፈቻ ንግግራቸው “ኢትስዊች ባለፈው የበጀት ዓመት ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የክፍያ ሥነ-ምህዳር እንዲኖር በማመቻቸት ረገድ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል” ብለዋል።

በተጨማሪም የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል እስከ ሰኔ 30 2025 ድረስ ወደ 2.56 ቢሊዮን ብር ማደጉን ጠቅሰዋል።ይህም ባለአክሲዮኖች የኩባንያውን የእድገት እና የዘመናዊነት ጥረቶችን ለመደገፍ ያላቸውን ጠንካራ ቁርጠኝነት ያሳያል ማለታቸውን ብስራት ሬዲዮ ሰምቷል።

አቶ ሰለሞን አክለውም የኩባንያው  የፋይናንስ ሪፖርት እንደሚያሳየው  2.2 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ  ማግኘቱን ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል።ከታክስ በፊት ያለው  የኢትስዊች ትርፍ  1.42 ቢሊዮን ብር ገቢ አስመዝግቧል በማለት የቦርድ ሊቀመንበሩ ተናግረው  ይህም ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ34 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል ።

ኢትስዊች በኢትዮጵያ ፈጣን እና አስተማማኝ የክፍያ ስርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣቱን ቀጥሏል።  በተለይም  እንደ ክፍያ ጥያቄ  እና የQR ክፍያዎች ያሉ የአጠቃቀም ጉዳዮችን በማስቻል ኢትስዊች ሁሉንም የፋይናንስ ተቋማት ለመደገፍ አስፈላጊውን መሠረተ ልማት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ አቶ ሰለሞን ጨምረው  ተናግረዋል።

ኢትስዊች በመጪው የበጀት ዓመት የአገልግሎት ጥራትንና መሠረተ ልማትን ማሻሻል፣ ቀጣይ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ፣ አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎቶችን ማስተዋወቅ እና ክልላዊ እና ድንበር ተሻጋሪ የክፍያ ዓለም አቀፍ ሽርክናዎችን ማጠናከርን ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።

በቅድስት ደጀኔ

photo_2024-07-02_15-23-49

ሰኔ 25፤2016 – ለጥበቃ በተሰጠዉ የጦር መሳሪያ የስራ ባልደረባዉን የገደለዉ ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

የኢሉባቡር ዞን ፖሊስ መምሪያ ፤ ታረቀኝ አለማየሁ የተባለዉ ግለሰብ በያዩ ወረዳ የያዩ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጥበቃ ሰራተኛ ሆኖ እያገለገለ እያለ በስራዬ ጣልቃ እየገባ ነዉ በሚል የስራ ባልደረባዉን መግደሉን ፖሊስ መምሪያዉ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን የላከዉ መረጃ ያመላክታል።

ግለሰቡ ህዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት አስቦና አቅዶ የስራ ባልደረባዉን ለመግደል ተዘጋጅቶ ተኩሶ መግደሉን በማስረጃ መረጋገጡን ያገኘነዉ መረጃ ጠቁሟል።

ፖሊስ ምርመራዉን አጠናቅቆ ፤ ዐቃቢ ህግ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 32 ንዑስ በአንቀጽ 1 እና 540 መሰረት በግድያ ወንጀል ክስ የመሰረተበት መሆኑም ተገልጿል።

በዐቃቢ ህግ የተመሰረተዉን ክስ ሲመለከት የቆየዉ የኢሉባቡር ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ፤ ተከሳሽ ታረቀኝ አለማየሁ የቀረበበት ክስ በማስረጃ በመረጋገጡ እና መከላከል ባለመቻሉ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለዉ ችሎት በ 10 አመት እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የኢሉባቡር ዞን ፖሊስ መምሪያ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን የላከዉ መረጃ ያመላክታል።

በበረከት ሞገስ

photo_2024-07-01_10-48-38

ሰኔ  24፤2016 – በ-#ናይጄሪያ ሴት አጥፍቶ ጠፊዎች ባደረሱት ጥቃት 18 ሰዎች ተገደሉ

በናይጄሪያ ሰሜናዊ ምስራቅ ክልል ውስጥ አጥፍቶ ጠፊዎች ቅዳሜ እለት በፈፀሙት በርካታ ፍንዳታዎች ቢያንስ 18 ሰዎች መገደላቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

በሰሜናዊ ምስራቅ ቦርኖ ግዛት በጉዎዛ ከተማ በቀብር ሥነ ሥርዓት እና በጋብቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ የአጥፍቶ ጠፊዎች የቦምብ  ፈንጂዎ ጥቃት መድረሱን የቦርኖ ግዛት የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኤጀንሲ ኃላፊ ባርኪንዶ ሳኢዱ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ሦስተኛው ፍንዳታ በናይጄሪያ-ካሜሩን ድንበር ላይ በምትገኘው ከተማ ውስጥ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ፍንዳታ ከደረሰ ከደቂቃዎች በኋላ በመንግስት ሆስፒታል አካባቢ መከሰቱን አስረድተዋል።

እስካሁን ድረስ ህጻናት፣ አዋቂ ወንድ፣ ሴት እና ነፍሰ ጡር ሴትን ጨምሮ  18 ሰዎች እስከ ሰኞ ረፋድ ድረስ ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል ሲሉ ሰኢዱ ተናግረዋል። በከባድ ጉዳት የደረሰባቸው 19 ሰዎች በግዛቱ ዋና ከተማ ማይዱጉሪ ወደሚገኝ የህዝብ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ገልፀዋል።በድምሩ 23 ሰዎች ቆስለዋል። ቦኮ ሃራም እና የአይኤስ ታጣቂ የሽብር ቡድኖች ከአስር አመታት በላይ የፈፀሙትን የሽብር ጥቃቶች በመጋፈጥ ላይ የቆየችው ናይጄሪያ በዚህ አመት እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት በአንድ ቀን ሲፈፀም የመጀመሪያው ነው።

ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኒዩ ጥቃቱን “ተስፋ የቆረጡ ኃይሎች የሽብር ድርጊቶች” ሲሉ አውግዘዋል።በግዎዛ ከተማ ለተፈፀመው ግድያ ተጠያቂ በሆኑ አካላት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀው ይህ ጥቃት በቅርብ ጊዜ በታጣቂዎች ላይ የናይጄሪያ ጦር ያገኘውን ስኬት የሚያደናቅፍ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ የግፍ ጥቃት ፈጣሪዎች ለወሰዱት እርምጃ መንግስታቸው የናይጄሪያ ህዝብ ወደ ፍርሀት፣ እንባ፣ እና ሀዘን ውስጥ እንዲገባ ስለማይፈቅድ የአፀፋ ምላሽ ይሰጣል ሲሉ አረጋግጠዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በናይጄሪያ ቦርኖ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲያቆም አሳስቧል።እነዚህ አሰቃቂ ጥቃቶች ለሰው ልጅ ህይወት ያላቸውን ንቀት ያሳያል ሲል ቡድኑ ኮንኗል። በናይጄሪያ የሚገኘው የአሜሪካ ተልዕኮ ጥቃቱን “አሰቃቂ” ሲል ገልጿል። “እነዚህ አስጸያፊ የጥቃት ድርጊቶች ጨካኝ እና ምህረት የለሽ ለሰው ሕይወት ግድየለሽነትን ያሳያሉ። እነዚህ አስጸያፊ ጥቃቶች በክልሉ ውስጥ የሽብርተኝነትን ቀጣይነት ያለው ስጋት የሚያስታውሱ ናቸው በማለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ጎዛ በ2014 በቦኮ ሃራም ቁጥጥር ስር የነበረች ሲሆን በ2015 የናይጄሪያ ጦር ድል አድርጎ ቡድኑን አባሯል። ነገር ግን ቦኮሀራም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በከተማዋ አቅራቢያ ጥቃቶችን እና አፈናዎችን ማድረጉን ቀጥሏል። በግዎዛ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች ታጣቂዎች እራሳቸውን ለማደስ እና አሁንም ጉዳት የማድረስ አቅም እንዳላቸው ለማሳየት እየሞከሩ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬን አንግቧል። ባለፈው ህዳር 20 ሰዎች በአጎራባች ዮቤ ግዛት የቀብር ስነስርዓት ጨርሰው ሲመለሱ በቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ተገድለዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው ታጣቂዎች በጉሮካያ መንደር ባደረጉት ወረራ 17 ሰዎችን ከገደሉ ከአንድ ቀን በኋላ የመንደሩ ነዋሪዎች የመኸር ግብር የተባለውን ግብር ለመክፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው ሲል ፖሊስ አስታውቋል።ቦኮ ሃራም በታሪክ ከነበሩት ታጣቂ ቡድኖች በበለጠ በርካታ ሴቶችን ለአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ይጠቀም እንደነበር አንድ ጥናት አመልክቷል። የቅርብ ጊዜ ቁጥሮች እንደሚጠቁሙት ቦኮ ሃራም ከሚጠቀምባቸው አጥፍቶ ጠፊዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ብዙዎች እንደሚጠቁሙት የሴቶች የአለባበስ ሁኔታ ፈንጂዎችን ለመደበቅ ቡድኑ ይጠቀምበታል።

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-06-28_16-29-46

ሰኔ  21፤2016 – በዩኒቨርስቲ ተማሪዋ ግድያ  ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በይግባኝ በእድሜ ልክ እስራት መቅጣቱን ፖሊስ አስታወቀ

የአሶሳ ዩንቨርሲቲ ተማሪ የሆነችውን ግለሰብ በጩቤ ሶስት ቦታ በጀርባዋ በመውጋት የግድያ ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣቱ ይታወሳል።

ሆኖም በይግባኝ በእድሜ ልክ እስራት መቅጣቱን በአሶሳ ከተማ አስተዳደር የወረዳ አንድ ፖሊስ አስታውቋል ።ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በግምቱ ከጧቱ 2፡45 ሰዓት አከባቢ ተከሳሽ አ/ቶ ዩሀንስ መርጋ ኢተቻ የተባለው ግለሰብ የሴት ጓደኛው የሆነችው ተማሪ ደራርቱ ለሜሳ የተባለችው ላይ ጭካኔ በተሞላበት የግድያ ወንጀል ፈፅሟል።

ተከሳሽ በፈፀመው ሰው መግደል  ወንጀል ተከሶ ከዚህ በፊት የ18 ዓመት እስራት ውሳኔ ተላልፎበት ነበር ።ይሁን እንጅ በውሳኔው ቅር የተሰኘው  የአሶሳ ከተማ አስተዳደር አቃቤ ህግ ይግባኝ በመጠየቅ የእስራቱ ውሳኔ እንዲሻሻልላቸው በጠየቀው መሠረት ጉዳዩን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሲመለከተው ቆይቷል ።

ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ሲመርምር ከቆየ በኃላ የኢ/ፌ /ድ/ሪ የወንጀል ህግ  አንቀጽ 539 /1ሀ ስር የተመለከተው  መተላለፉ ካረጋገጠ በኃላ ተከሳሹ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ በመሆኑ በይግባኝ ችሎት ሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት እሱንም ያርማል ማህበረሰቡንም ያስተምራል በማለት በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንድቀጣ ወስኗል ።

በአበረ ስሜነህ

photo_2024-06-28_16-18-00

ሰኔ  21፤2016 – በህንድ ዴሊ አየር ማረፊያ በጣለዉ ከባድ ዝናብ በጣሪያ መደርመስ የተነሳ የሰዉ ህይወት አለፈ

በዴሊ አየር ማረፊያ የጣለውን ከባድ ተከትሎ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ አራት ሰዎች ቆስለዋል።በአውሮፕላን ማረፊያው ተርሚናል 1 ላይ በቆሙ መኪኖች ላይ ጣሪያው ሲደረመስና ግዙፍ ምሰሶዎች ሲወድቅ የተሰራጩ ምስሎች አመላክተዋል፡፡ከተርሚናሉ የሚመጡ ሁሉም በረራዎች ለጊዜው ታግደው መግቢያ በሮች ተዘግተዋል።በአውሮፕላን ማረፊያው የነፍስ አድን ስራ ለተጎጂዎች የተሰራ ሲሆን ወደ ሆስፒታል ለተጨማሪ ህክምና መላካቸዉ ተሰምቷል፡፡የሕንድ አቪዬሽን ተቆጣጣሪ አየር መንገዶች ተሳፋሪዎችን በተለዋጭ በረራዎች እንዲያስተናግዱ ወይም ተመላሽ እንዲያደርጉ መክሯል።

አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ በረራዎች ከተርሚናል 1 የሚነሱ በመሆናቸው አደጋው በሺዎች በሚቆጠሩ የጉዞ እቅዶች ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል።አንዳንድ አየር መንገዶች የበረራ ስራዎችን ወደ ቀሪዎቹ ሁለት ተርሚናል ኤርፖርት ቀይረዋል።የፌደራል አቪዬሽን ሚኒስትር ራም ሞሃን ናይዱ ኪንጃራፑ ለሟች ቤተሰብ የ2 ሚሊየን ሩፒ ወይም 24 ሺ የአሜሪካን ዶላር ካሳ እንደሚከፍሉ እና ለተጎዱ ሰዎች ደግሞ 300,000 ሩፒዎች ማካካሻ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።ለጋዜጠኞችም እንደተናገሩት ሁኔታው በቁጥጥር ስር እንደሆነ እና ምንም አይነት ችግር እንዳይፈጠር የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመላዉ ሀገሪቱ ተመሳሳይ መዋቅር ያላቸው ኤርፖርቶች ላይ ፍተሻ እንደሚደረግላቸው አክለዋል።ክስተቱ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ትችት ሲሰነዘርበት የነበረ ሲሆን በርካታ ተጠቃሚዎች የአየር ማረፊያዉ ተርሚናል በቢሊዮኖች ሩፒ ወጪ ከፍተኛ እድሳት ከተደረገለት በኃላ በመጋቢት ወር በጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ተመርቋ፡፡ የቅርብ ጊዜ አጠቃላይ ምርጫ ከመጀመሩ ከአንድ ወር በፊት ምርቃት ተደርጎለታል፡፡ሆኖም ሚኒስትሩ ኪንጃራፑ የተደረመዉ የኤርፖርቱ ክፍል የታደሰው አይደለም ብለዋል፡፡በጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የተመረቀው ሕንፃ በሌላ በኩል እንደሆነ እና የፈረሰው ሕንፃ አሮጌ ሕንፃ መሆኑን እና ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡

ከትላንት ሃሙስ እለት ጀምሮ ከባድ ዝናብ በደልሂ ከተማ እየጣለ ይገኛል፡፡ የህንድ ዋና ከተማ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በከባድ የሙቀት መጠን ዉስጥ የቆየች በመሆኑ ዝናቡ እንደ ፋታ ተወስዷል፡፡ነገር ግን ዝናቡ ከተማዋን ትርምስ ውስጥ ከቶታል ምክንያቱ ደግሞ በርካታ መንገዶች በውሃ የተሞሉ በመሆናቸው የትራፊክ መጨናነቅን አስከትሏል።የሕንድ ሜትሮሎጂ ዲፓርትመንት እንዳስታወቀዉ በሳምንቱ መጨረሻ ከባድ ዝናብ መጣሉን እንደሚቀጥል ተንብዮአል።

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-06-28_13-31-48

ሰኔ  21፤2016 – በቦንጋ ከተማ ከተወለደች ሰባት ቀን የሞላት ህፃን ተጥላ በህይወት ተገኘች

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ አስተዳደር 01 ቀበሌ ማሪያም ቤተክርስቲያን አከባቢ ከተወለደች ሰባት ቀናት የሚሆናት ጨቅላ ህፃን ተጥላ መገኘቱን የቦንጋ ከተማ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ምክትል ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን  እንደገለፁት የአከባቢው ህብረተሰብ አመሻሽ ላይ የህፃን ድምፅ ሰምተው፤ ህፃኗን በህይወት መኖሯን ሲያረጋግጡ ለፖሊስ በማሳወቅ ወደ ህክምና ወስደዋል። የህፃኗ ጤንነት ተረጋግጦ ለቦንጋ ከተማ ሴቶችና ህፃናት የስራ ሂደት ዳይሬክቶሬት እንደተሰጠች ገልፀዋል፡፡

በከተማዉ በተደጋጋሚ ጊዜ ተወልደዉ የሚጣሉ ህፃናት እየተበራከቱ በመምጣቱ ተወልደው የሚጣሉ ህፃናት ማቆያ አለመኖሩ ችግር እንደሆነ ተገልፆል።

ከዚህ ቀደም በከተማ ዉስጥ ተወልደዉ የተጣሉ ሁለት ወንድና ሁለት ሴት ህፃናት መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን በቦንጋ ገብረፃዲቅ ሆስፒታል ትብብር በማድረግ በጊዜያዊነት እንዲቆዩ ተደርጓል።በጉድፈቻ ለማሳደግ የሚፈልግ ሰዉ ቦንጋ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት በአካል ቀርቦ በሕጋዊ መንገድ መውሰድ ይችላል ተብሏል፡፡

የሰባት ቀን ጨቅላ  ህፃን ልጆን  ወልዳ የጣለችዉን እናት ፖሊስ እያፈላለገ እንደሚገኝ ምክትል ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በሳምራዊት ስዩም

Capture

ሰኔ  21፤2016 – በአሜሪካ በግድያ እና የ18 ዓመቷን ግለሰብ አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ በኬሚካል መርፌ በሞት ተቀጣ

በቴክሳስ የሞት ፍርድ የተፈረደበት እስረኛ ራሚሮ ጎንዛሌስ እ.ኤ.አ በ2001 በአንዲት ወጣት ግድያ እና አስገድዶ መድፈር ወንጀል ለአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢልም በስተመጨረሻ በሞት ተቀጥቷል።

ጎንዛሌስ እሮብ እለት መሞቱ ተነግሯል። በሃንትስቪል በሚገኘው የመንግስት ማረሚያ ቤት የኬሚካል መርፌ የሞት ቅጣቱ ተፈፅሞበታል። በወንጀል ድርጊቱ የተገደለችው የ18 ዓመቷ ብሪጅት ታውንሴንድ የተባለች በደቡብ ምዕራብ ቴክሳስ የምትኖረውን ሴት አስክሬኗ በ2001 ከጠፋ ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ የተገኘ ሲሆን ተከሳሹ ተኮሶ መግደሉን አምኗል።በቴክሳስ የወንጀል ፍትህ ዲፓርትመንት በተለቀቀው መግለጫ ጎንዛሌስ ለተጎጂዋ ቤተሰብ ግድያው ከሚፈፀምበት ክፍል በመሆን ደጋግሞ ይቅርታ ጠይቋል።

እኔ በራሴ ላይ ያመጣሁት ህመም፣ የተጎዳሁት ጉዳት ከፍተኛ ነው ከምንም በላይ የነጠቅኩትን ህይወት መመለስ አልችልን የተቀበልኩት ቅጣት በቃላት መግለጽ የማልችለው ነው ብላል። ይህ ይቅርታ በቂ እንዳልሆነ ተስፋ አደርጋለሁ ሲል አክሏል። ይቅር እንድትለኝ መጸለይን አላቆምኩም እናም አንድም ቀን ይቅርታ ለመጠየቅ እድሉን አግኝቼ አላውቅም። ግን አንድ ቀን ይቅር እንደምትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ ሲል ተናግሯል።ሟች ታውንሴንድ በህይወት ብትኖር በዚህ አመት 41 ዓመቷን ትይዝ ነበር።እኤአ በጥር 2001 ከቤቷ ታፍና በጎንዛሌዝ የፆታ ጥቃት ተፈፅሞባት ተገድላለች።

ጎንዛሌዝ ሌላን ሴት በማፈን እና አስገድዶ በመድፈር በእድሜ ልክ እንዲቀጣ ከተፈረደበት በኋላ በታውንሴንድ ግድያ ወንጀለኛ መሆኑ ተደርሶበታል። የሟቿ ታውንሴንድ ወንድም ዴቪድ የጎንዛሌዝን በሞት መቀጣት ከተመለከተ በኋላ በመጨረሻ ፍትህ ሲሰጥ አይተናል ብሏል። ይህ ቀን ለቤተሰባችን ረዥሙ የስቃይ ጉዞ ያበቃበት ቀን ነው ሲል ተደምጧል። ከሁለት አስርት አመታት በላይ፣ ሊታሰብ በማይቻል ስቃይ እና የልብ ህመም አሳልፈናል ሲል ተናግሯል።ዴቪድ የጎንዛሌስ ሞት ትንሽ ሰላም ይሰጠናል ሲል ግን ደስተኛ እንዳልሆንን መናገር እፈልጋለሁ ብሏል።

የጎንዛሌስ ጠበቆች፣ ቦርዱ የሞት ፍርድን ወደ እስር ቅጣት እንዲቀይር ጠይቀው ነበር። እራሱን ለማሻሻል፣ ለማሰላሰል እና ለጸሎት በትጋት ሲደክም ነበር ፤እናም ወደ ጎልማሳ፣ ሰላማዊ፣ ደግ፣ አፍቃሪ እና ጥልቅ ሀይማኖተኛ ተቀይሬ ሲሉ ለዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥያቄ ቢያቀርቡም ውድቅ ሆኗል።በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከቴክሳስ እና ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ 11 የሀይማኖት መሪዎች ቡድን የይቅርታ ቦርዱን እና የቴክሳስ ገዥውን ግሬግ አቦትን ግድያው ውድቅ እንዲያደርጉ እና ምህረት እንዲደረግለት ጠይቀዋል።

ሆኖም የምህረት ቦርዱ የጎንዛሌስን የሞት ፍርድ ወደ እስር ለመቀየር 7 ለ 0  ድምፅ በመስጠቱ የሞት ፍርዱ ተግባራዊ ሆናል። የጎንዛሌስ ግድያ በዚህ ዓመት በቴክሳስ ሁለተኛው ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ደግሞ ስምንተኛው የሞት ቅጣት ተደርጎ ተመዝግቧል። በተመሳሳይ ሐሙስ እለት ኦክላሆማ እኤእይ በ1984 የ 7 ዓመቷን ህጻን ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈር እና ግድያ የፈፀመው ሪቻርድ ሮጀም በሞት እንዲቀጣ ቀጠሮ ተይዞለታል።

በስምኦን ደረጄ