photo_2024-06-18_13-28-35

ሰኔ  11፤2016 – በ-#ቱርክ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን ለማጭበርበር አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የተጠቀመዉ ተማሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

አንድ የቱርክ ዩኒቨርሲቲ እጩ ተማሪ ለመግቢያ ፈተና በፍጥነት መልስ ለማግኘት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ  ሲጠቀም ከተያዘ በኋላ በቅርቡ በቁጥጥር ስር ውሏል።

በሰኔ 1 በሺዎች የሚቆጠሩ የሁለተኛ ደረጃ ምሩቃን በኢስፓርታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለፈተና ተቀምጠዋል፡፡ የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ የሆነውን መሰረታዊ የብቃት ፈተና ተሰጥቷል፡፡ነገር ግን አንድ ክስተት የአለም አቀፍ የዜና አርዕስተ ዜና ሆኗል። አንድ እጩ ተፈታኝ ተማሪ የኢንተርኔት ግንኙነትን በመጠቀም በድብቅ ካሜራ እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሃይል የሚሰራ ሶፍትዌር በመጠቀም በፈተና ላይ ያሉ ጥያቄዎችን በማንበብ እና በተጨባጭ ምላሽ የሚሰጥ ሶፍትዌር በመጠቀም ሲያጭበረብር መያዙን የቱርክ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ተማሪዉ በፈተናው ወቅት ያሳየው ባህሪ የተቆጣጣሪዎችን ትኩረት ስቧል፡፡ እናም ባደረጉበት ክትትል የፈተና የማታለል ዘዴው ተደርሰዎበታል።የቱርክ የዜና ወኪል ኤኤ እንደዘገበዉ በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ውስጥ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ዘግቧል። ምንም እንኳን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጥቅም ላይ የዋለው የስርዓቱ ሙሉ ዝርዝሮች እስካሁን ይፋ አለመደረጉን ፖሊስ አስታዉቋል፡፡ተማሪዉ በፈተና አዳራሹ መግቢያ ላይ ያለውን የመቆጣጠሪያ ነጥብ ለማለፍ በስኒከር ጫማው ውስጥ አነስተኛ ራውተር ደብቋል፡፡

አነስተኛ ስማርት ፎን እንደ ክሬዲት ካርድ በመያዝ፣ ባለከፍተኛ ጥራት ያለዉ ካሜራ በሸሚዝ ቁልፍ ተመስሎ ካሰራ በኃላ በጆሮ ማዳመጫ ወደ ጆሮው መልስ ማግኘት ችሏል፡፡ተቆጣጣሪዎች የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የኩረጃዉን ሁኔታ እንዴት እንደያዙት ግልጽ አይደለም፡፡ነገር ግን የቱርክ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት የፈተናዉ ፈታኞች ‘በጥርጣሬ’ ሳይዙት እንዳልቀረ ጽፈዋል፡፡ ለዚህምበ በጆሮው ውስጥ የጆሮ ማዳመጫ ሲያገኙ ተቆጣጣሪዎች ከፈተና አዳራሽ በማስወጣት ለፖሊስ አስረክበዉታል።

ጥልቅ ፍተሻ ሲደረግበት የጆሮ ማዳመጫው እና አነስተኛ ካሜራው ከስማርት ፎን ጋር የተገናኙ ሲሆን ይህም በሰዉ ሰራሽ አስተዉሎት ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሃይል የሚሰራ ሲስተም ጋር የተገናኘ መሆኑን ደርሰዉበታል፡፡ሲስተሙ በፈተናው ላይ ያሉትን ጥያቄዎች አንብቦ ትክክለኛውን መልስ በጆሮ ማዳመጫው በኩል መስጠት ይችላል።በፖሊስ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ባይሰጠም አንዳንድ የዜና ማሰራጫዎች በቻች ጂፒቲ የጎላበተ መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቱርክ የዩንቨርስቲ ፈተናዎች ላይ መኮረጅ እንደ ከባድ ወንጀል የሚቆጠር በመሆኑ ተማሪዉ የእስር ቅጣት ይጠብቀዋል።ሌላ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ለመፈተን ደግሞ ቢያንስ ለሁለት አመት እግድ ይጣልበታል። ተማሪዎች አስፈላጊ በሆኑ ፈተናዎች ላይ ለማጭበርበር ቴክኖሎጂን ሲጠቀ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሰዉ ሰራሽ አስተዉሎት ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለኩረጃ ጥቅም ላይ ሲዉል ይህ የመጀመሪያው ጉዳይ ነው፡፡

በስምኦን ደረጄ

Capture

ሰኔ  11፤2016 – ከሰው መቃብር ሐውልት ላይ ብረቶችን እየቆረጠ ሲሰርቅ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

 

በሐረር ከተማ ከሚገኙ የመቃብር ስፍራ ላይ ለሐውልት ተብለው የሟችን ማንነት የሚገልፅ ፅሁፍ ከያዙት ብረቶች ላይ በተለያዩ ጊዜያት እየቆረጠ በኪሎ ሲሸጥ የነበረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።

ግለሠቡ ከተለያዩ መቃብሮች ላይ የቆረጠውን ብረቶች ለመሸጥ ሲል በአካባቢው ህብረተሰብ ለአቦከር ወረዳ ፖሊስ መረጃ በመስጠቱ ወዲያውኑ ከነ እግዚቢቱ መያዙን የአቦከር ወረዳ ፖሊስ ሃላፊ ኮማንደር ዘይዳን ቶፊቅ አስታውቀዋል ሲል የዘገበው የሐረር ፖሊስ ኮሚሽን ነው።

 

photo_2024-06-18_09-45-07

ሰኔ  11፤2016 – ፑቲን ከ24 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዛሬው እለት ሰሜን ኮሪያን ይጎበኛሉ

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከ24 ዓመታት በኋላ ወደ ፒዮንግያንግ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ከማድረጋቸው በፊት ሰሜን ኮሪያ በዩክሬን ጦርነት ሞስኮብ በጽኑ ስለደገፈች አወድሰዋል። ፑቲን በዛሬው እለት ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ለመገናኘት በዋና ከተማው ፒዮንግያንግ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሁለቱ መሪዎች ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በመስከረም ወር ላይ በሩሲያ ሩቅ ምስራቅ በሚገኘው ቮስቴክኒ ኮስሞድሮም ነው።

ነገር ግን ፑቲን ከ 2000 ጀምሮ ፒዮንግያንግ ሲጎበኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው። በሰሜን ኮሪያ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ላይ በወጣ መረጃ መሰረት ሞስኮ ከፒዮንግያንግ ጋር የንግድ እና የደህንነት ስርዓቶችን ከምዕራቡ ዓለም ቁጥጥር ውጪ አድርገው እንደሚገነቡ ቃል ገብተዋል ። ፕሬዝዳንት ፑቲን በሰሜን ኮሪያ የገዥው ፓርቲ ቃል አቀባይ በሆነው በሮዶንግ ሲሙን ላይ በታተመው መልዕክታቸው “የአሜሪካ ጫና፣ ጥቃት እና ወታደራዊ ዛቻ” በመከላከል ፒዮንግያንግ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ቃል ገብተዋል።

ሁለቱ ሀገራት በፍትህ መከባበር ላይ የተመሰረተ ሁለገብ የአለም ስርአት መመስረትን ለማደናቀፍ የምዕራባውያን ምኞት በማለት የገለፁትን “በቆራጥነት መቃወማቸውን” እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል። ዩናይትድ ስቴትስ “በእነዚህ ሁለት ሀገራት መካከል ያለው ጥልቅ ግንኙነት” እንዳሳሰባት ተናግራለች። ክርምሊን የመሪዎቹን ቆይታ “የወዳጅነት ጉብኝት” ሲል ገልጿል። ፑቲን እና ኪም የደህንነት ጉዳዮችን ጨምሮ የሽርክና ስምምነት ሊፈራረሙ እንደሚችሉ እና ለመገናኛ ብዙሃን የጋራ መግለጫዎችን እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

በተጨማሪም በኪም ኢል ሱንግ አደባባይ ህዝባዊ ሰልፍ ይኖራል። ፑቲን በሰሜን ኮሪያ ብቸኛዋ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በሆነችው በፒዮንግያንግ የምትገኘውን የኦርቶዶክስ ህይወት ሰጭ ስላሴ ቤተክርስቲያንን ኮንሰርት ይመለከታሉ ተብሎ ይጠበቃል። የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ እ.ኤ.አ. በ2019 በሰሜን ኮሪያ ባደረጉት ጉብኝታቸው ለመጨረሻ ጊዜ በቆዩበት ፒዮንግያንግ በሚገኘው የኩምሱሳን የእንግዳ ማረፊያ ቤት ፑቲን እንደሚቆዩ ዘገባዎች አመላክተዋል።

በስምኦን ደረጄ

Capttttttttttttttttttture

ሰኔ  10፤2016 – በ2017 የትምህርት ዘመን የትምህርት አገልግሎት መስጠት የተከለከሉ የ41 ትምህርት ተቋማት ዝርዝር ይፋ ሆነ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በ2017 የትምህርት ዘመን የትምህርት አገልግሎት መስጠት የተከለከሉ የትምህርት ተቋማትን ዝርዝር በዛሬው እለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ አድርጋል።

የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኛው ገብሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በ2017 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን መዝግበው የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች 1332 መሆናቸዉንና የማስተማር ፈቃድ የተሰጣቸው እንደሆነ እንዲሁም 43 ት/ቤቶች በራሳቸው ጊዜ መቀጠል ስላልቻሉ ፈቃዳቸው መሰረዙን አሳውቀዋል፡፡

ሀላፊው አክለውም የ150 ት/ቤቶች ጉዳይ በሂደት ላይ እንደሆነና ወደፊት የሚገለጽ መሆኑን ፤ 41 ትምህርት ቤቶች በዋናነት በትምህርት ፖሊሲ ጥሰት ፣ በትምህርት ስታንዳርዱ መሰረት ከ 75% በታች ያመጡ እንዲሁም የትምህርት ጊዜ ሰሌዳን በአግባቡ አለመጠቀም የታየባቸው ሲሆኑ በልጆች አስተዳደግ ላይ ተፅእኖ የሚፈጥርና ብቁ ትውልድ በማፍራት ሒደታችን እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑ ትምህርት ቤቶቹ እንዲዘጉ ባለስልጣኑ ውሳኔ ላይ መድረሱን አብራርተዋል::

መስፈርቱን ባለማሟላታቸው በተዘጉ ትምህርት ቤቶች ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች ያለምንም ዋጋና መሰል ልዩነቶች ምርጫቸው ተጠብቆ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እንደሚደረግም አሳውቀዋል

photo_2024-06-17_13-34-03 (2)

ሰኔ  10፤2016 – በትግራይ ክልል ወረርሽኝ በሆነ መልኩ በተከሰተ ከእንስሳት ወደ ሰዎች የሚተላለፍ በሽታ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ

በደቡብ ምስራቅ ትግራይ በተለይም ህንጣሎ ዋጀራት በተሰኘዉ ወረዳ ከእንስሳት ወደ ሰዉ በሚተላለፍ በሽታ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል።

በትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የጤና ኤክስቴንሽን እና የጤና ማስተዋወቅ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሚካኤል ሃጎስ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት በሽታዉ ጦርነቱ ካስከተለዉ ቀዉስ መካከል አንዱ ነዉ ብለዋል። በበሽታዉ ከተያዘ እንሰሳ ጋር በሚኖር ንክኪ እና ስጋዉን በመብላት በሚተላለፈዉ በሽታው በወረዳዉ በወረርሽኝ መልክ መከሰቱን ተናግረዋል።

በዚህ በሽታ ቁጥራቸዉ በዉል ያልታወቀ ሰዎች መጠቃታቸዉን የተናገሩት አቶ ሚካኤል ፤ እስከሞት ሊያደርስ እንደሚችልም ገልጸዋል። በዚህ በሽታ የተነሳ የአራት ሰዎች ህይወት ሲቀጠፍ በርካቶች በአዲ ጉደም ሆስፒታል እንዲሁም ከፍ ባለ አስጊ ሁኔታ ዉስጥ ያሉት ደግሞ በዓይደር ሪፈራል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና ክትትል ላይ ናቸዉ ብለዉናል።

በሽታዉ በሁሉም የትግራይ ዞኖች ይታይ ነበር ያሉት አቶ ሚካኤል አሁን ግን በወረርሽኝ መልክ በደቡብ ምስራቅ ትግራይ አንድ ወረዳ ላይ መከሰቱን አስረድተዋል።

አንትራክስ የተሰሰነዉ በሽታ በባክቴሪያ የሚመጣ ሲሆን የተጠቃዉ ሰዉ ፤ ከእንስሳት ጋር በሚኖረዉ ንክኪ የቆዳ ላይ ህመም ፣ በበሽታዉ የተጠቃ እና ያልተመረመረ ከብትን የተመገቡ ሰዎች ደግሞ ከአንጀት ጋር የተታያዘ ከፍተኛ ህመምን እንዲሁም የእንሰሳዉ ቆዳ በፋብሪካዎች ከተቀነባበረ ደግሞ በሳንባ ላይ ከፍተኛ ህመምን የሚያስከትል እና በ 24 ሰዓታት ዉስጥ ሊገድል የሚችል ነዉ ብለዉናል።

በአሁኑ ወቅትም በትግራይ ከእንስሳቱ ጋር በሚኖር ንክኪ በቆዳ ላይ የሚከሰተዉ የበሽታ አይነት በስፋት መታየቱን ጠቅሰዉ ያልተመረመረ ስጋን የተመገቡ ሰዎችም በበሽታዉ መጠቃታቸዉን አክለዋል። በሽታዉ ከሰዉ ወደሰዉ አይተላለፍም የተባለ ሲሆን ከእንስሳት ጋር የሚኖር ንክኪን ግን መገደብ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከ 20 አመታት በፊትም በሽታዉ ተከስቶ ነበር የተባለ ሲሆን በወቅቱ በቁጥጥር ስር የነበረ ቢሆንም ከጦርነቱ በኋላ በተፈጠረዉ የጤና አገልግሎት ስርዓት መጓደል የተከሰተ መሆኑን አመላክተዋል።

በበሽታዉ የተያዙ ሰዎች በቆዳ ላይ የማሳከክ እና አብጦ የመፈንዳት እንዲሁም የእንስሳት ስጋን ተመግበዉ የታመሙትን ሰዎች ደግሞ እንደማንኛዉም የሆድ ህመም የቁርጠት እና የህመም ምልክት ያለዉ ሲሆን በአንጀት ላይ ግን ቁስለትን የሚያስከትል መሆኑንም ተናግረዋል።

በሽታው በቶሎ የህክምና ክትትል ከተደረገለት የሚድን እንደሆነም በትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የጤና ኤክስቴንሽን እና የጤና ማስተዋወቅ ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሚካኤል ሃጎስ ጨምረዉ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በበረከት ሞገስ

photo_2024-06-17_12-28-46

ሰኔ  10፤2016 – በሸካ ዞን የአራት አመት ህፃን በንብ መንጋ ተነድፎ ህይወቱ አለፈ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሸካ ዞን የማሻ ወረዳ ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 11ሰዓት በወረዳዉ ኡዋ ቀበሌ ልዩ ስፍራ ይጎ ቁጥር አንድ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የአራት አመት ህፃን በንብ መንጋ ተነድፎ ህይወቱ ማለፋ ተገልጿል።

የክልሉ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ምክትል ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደገጹት በእለቱ ንፋስ ቀላቅሎ በጣለዉ  ከባድ ዝናብ ምክንያት በመኖሪያ ቤት አከባቢ ዘመናዊ የንብ እርባታ ቀፎ በንፋስ በመዉደቁ ምክንያት ንቦቹ ከቀፎዉ ወጥተዉ በመጫወት ላይ የነበሩ ሶስት ህፃናትን ለመዉረር ሞክረዋል።  ሁለቱ ህፃናት ሮጠዉ ሲያመልጡ የአራት አመቱ ህፃን ማምለጥ ባለመቻሉ በንቦች መንጋ ተነድፎ ህይወቱ እንደላፈ አስረድተዋል።

መሰል የንብ መንጋ አደጋ በሌሎች አከባቢዎች እንዳይከሰት ንብ የማነብ ስራ የሚያከናዉኑ ግለሰቦች ዘመናዊ ቀፎዎችን በንፋስ እንዳይወድቁ እና  ከለላ አጥር ማበጀት እንደሚኖርባቸዉ  ምክትል ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በሳምራዊት ስዩም

photo_2024-06-17_12-06-00

ሰኔ  10፤2016 – በኮሎምቢያ አንዲት ሴት ከሰባት ጡረተኛ ወንዶች ጋር ለጥቅሟ ስትል የፍቅር ግንኙነት በመመስረቷ መነጋገሪያ ሆናለች

ሊና የተባለችው ወጣት ኮሎምቢያዊት ሴት ስትሆን ከሰባት ጡረተኞች ጋር ፍቅር የሚመስል ግንኙነት ውስጥ የገባች ሲሆን አዛውንቶቹን ለገንዘብ ፍላጎቷ ስትል ስትጠቀምባቸው እንደነበር ተሰምቷል።

በባራንኪላ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ሊና ያልተለመደ ታሪኳ በማህበራዊ ድረ ገፅ ላይ መሰራጨቱን ተከትሎ በመላው ሀገሪቱ መነጋገሪያ ሆናለች። በራሷ ዕድሜ ክልል ከሚገኙ ከወንዶች ጋር ብዙ አሳዛኝ የፍቅር ግንኙነቶችን ካደረገች በኋላ ወጣቷ ሴት በምትኩ ጡረተኞችን ዒላማ በማድረግ የስሜት አለመረጋጋቷን ለመቅረፍ እና የገንዘብ ድጋፍ በቀላሉ ማግኘት እንደምትችል ትገነዘባለች።

ያልተሳካ የፍቅር ግንኙነቷን ወደ ተሻለ ህይወት ለመለወጥ በማሰላሰል ሊና ጎረቤቷ ከሆኑ አዛውንት ጋር ቅርርብ መፍጠር ትጀምራለች። እኚህ አዛውንት ከዚህ ቀደም ከእርሷ ጋር ለመሆን ፍላጎት እንዳላቸውም ታስታውሳለች። በተጨማሪም በእድሜ ከሚበልጧት አዛውንት ወንዶች ዘንድ በጣም ተፈላጊ እንደሆነች ተረድታለች። እናም በህዝብ ፓርኮች እና ሌሎች በብቸኝነት የሚያሳልፉ አዛውንቶች የሚዝናኑባቸው ቦታዎች የማጥመጃ መረቧ ማድረግ ጀመረች። እናም በአሁኑ ወቅት በገንዘብ ከሚደግፏት ከሰባት ጡረተኞች ጋር የጠበቀ ግንኙነት መመስረት ችላለች።

ከእድሜ እኩዮቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነቶቼን ከመረመርኩ በኋላ ማሰብ ጀመርኩ። አዛውንቶቹ ለሚያስፈልግህ ነገር ምንም መጠየቅ የለብህም ፣ ሁሉንም ነገር ይሰጣሉ ምክንያቱም በእድሜያቸው እንደ እኔ ያለች ሴት አያገኙም። ለዛም ነው ጡረተኞችን ለመፈለግ የወሰንኩት ስትል ሊና ለኡልቲማ ሆራ ቫሌ የተሰኘ ጋዜጣ ተናግራለች። ሁልጊዜ ደስተኛ እንድሆን ያደርጉኛል በማለት አክላለች።የሊና ሰባት አረጋውያን የወንድ ጓደኞቿ ካርሎስ፣ ሲሞን፣ ጄሱስ፣ ፓብሎ፣ ማኑዌል እና ሌሎች ሁለት ስማቸውን ያልተገለፁ ወንዶች ናቸው።

ሁሉም አዛውንቶች እርስ በእርስ የሚተዋወቁ ሲሆን በወጣቷ ዘንድ ይበልጥ ለመወደድ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል። ወንዶቹ የሊናን ወጪዎች ለመሸፈን እና የቤት ውስጥ ስራዎችን እንደ ጽዳት፣ ልብስ ማጠብ እና ምግብ ማብሰልን ጨምሮ እርሷን የመርዳት ኃላፊነት አለባቸው። በዚህም የተነሳ በእርሷ ዘንድ ይበልጥ ለመወደድ ይወዳደራሉ። ሊና ከአዛውንቶቹ ጋር የመሰረተችው ግንኙነት ከፍቅር ይልቅ እንደ ንግድ ስራ ትገልፀዋለች። በየወሩ ብዙ ገንዘብ ለሚሰጧት ለጋስ አዛውንት የበለጠ አብሮ የማሳለፍ እድል እንደምትሰጠውም ትገልጻለች።

የሊና ታሪክ በቅርቡ ከኮሎምቢያ በተጨማሪ በደቡብ አሜሪካ ሀገራት ውስጥ በስፋት ተሰራጭቷል። አንዳንዶች በእድሜ የገፉ ሰዎችን በመጠቀሟ በቁጥጥር ስር መዋል እንዳለባት አስተያየት ሰጥተዋል። ሌሎች ደግሞ ተንኮለኛ ናት የገንዘብ ፍላጎቷን ለመሙላት ስትል የሄደችበት ርቀት አስገራሚ ነው ብለዋል። ሊና ከአዛውንቶቹ ጋር ስላላት ግንኙነት እንጂ ማንም ሰው ስለሚያስበው ነገር ግድ አይሰጠኝም ስትል ትደመጣለች።

በስምኦን ደረጄ

Capture

ሰኔ  10፤2016 – በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የስድስት ሰዎች ህይወት አለፈ

በ14 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል

ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በሰደን ሶዶ ወረዳ ሀርቡ ኩሉሌ ከተማ ልዩ ቦታዉ ላጋ ጉንጋ በተሰኘዉ ቦታ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የስድስት ሰዎች ህይወት እንዳለፈ ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል።

ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ የደረሰዉ የትራፊክ አደጋ መነሻዉን ከቱሉ ቦሎ ያደረገዉ የህዝብ ማመላለሻ አይሱዙ ተሽከርካሪ ወደ አጨበር ከተማ በመጓዝ ላይ የነበረ ሲሆን በአደጋዉ ሌሎች 14 ሰዎችም ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ነዉ የተባለዉ።

ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በቱሉ ቦሎ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን በዚህ አደጋም ከ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት ወድሟል ተብሏል።

ኮድ 3 49391 ኦሮ የሆነዉ ተሽከርካሪ በምን ምክኒያት አደጋዉ እንዳጋጠመዉ እየተጣራ መሆኑንም የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ፖሊስ ያስታወቀዉ። በዚህ አደጋም የስድስት ሰዎች ህይወት ወዲያዉኑ አልፏል።

በበረከት ሞገስ

photo_2024-06-13_20-22-51

ሰኔ 6፤2016 – ለዓረፋ በዓል ወደ ወራቤ የሚያቀኑ መንገደኞች እስከ አምስት እጥፍ የደረሰ ጭማሪ የተደረገበት ታሪፍ እንዲከፍሉ መገደዳቸዉን ተናገሩ

የስልጤ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ በበኩሉ ተሽከርካሪዎቹ ወራቤ ሲደርሱ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ብሏል

የፊታችን እሁድ ለሚከበረዉ የዓረፋ በዓል በርካታ ዜጎች ወደ ወራቤ እና ስልጦ ዞኖች የሚጓዙ መንገደኞች ከታሪፍ በላይ እንዲከፍሉ እየተጠየቁ መሆኑን ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ቅሬታቸዉን ለጣቢያችን የተናገሩት አንድ መንገደኛ ከአዲስአበባ ወራቤ እስከ 1 ሺህ 500 ብር እንዲከፍሉ እየተጠየቁ መሆኑን ገልፀዋል። በህጋዊ ታሪፉ መሰረት 350 ብር ገደማ ለሚጠይቀዉ መንገድ እስከ አምስት እጥፍ ጭማሪ የታየበትን ገንዘብ እንዲከፍሉ መገደዳቸዉን ገልጸዋል። ተሽከርካሪዎቹ ከመናህሪያ ዉጪ ጫኝ መሆናቸዉንም ተጓዡ ተናግረዋል።

ብስራት የስልጤ ዞን የትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ አቶ ሱልጣን ራህመቶን የጠየቀ ሲሆን ፤ መምሪያዉ ጣልቃ መግባት የማይችል ቢሆንም ተሽከርካሪዎቹ ወደ ዞኑ እና ወደ ወራቤ ከተማ ሲደርሱ ግን ግጣት እንደሚጠብቃቸው ገልጸዋል። “መንገደኞች ጥቆማ መስጠት አለባቸዉ” ያሉት አቶ ሱልጣን ፤ ከታሪፍ በላይ የከፈሉትን ገንዘብ እስከማስመለስ የደረሰ አገልግሎት እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

አንድ አሽከርካሪ ከታሪፍ በላይ ጭኖ የተገኘ እንደሆነ የ 500 ብር ቅጣት የሚጣልበት ሲሆን ይህ ደግሞ እንደክልል ደንቡ ያለዉን ክፍተት የሚያሳይ ነዉ ብለዋል። በቅርቡ ግን ክልሉ ተግባራዊ አድርጎታል ያሉት ሌላ የቅጣት ደንብ ግን ከታሪፍ በላይ ያስከፈለን አሽከርካሪ የራስ ጥቅምን በማስቀደም በሚል 2 ሺህ 500 ብር እንደሚቀጣ ደንግጓል ብለዋል። በዚህ መሰረትም አሽከርካሪዎች ፤ ተጓዦች ከታሪፍ በላይ የከፈሉትን ገንዘብ ከማስመለስ ጀምሮ ቅጣቱ እንደሚጣልባቸው አስጠንቅቀዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ተሽከርካሪ ወደ ዞኑ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት ሃላፊዉ የመንገድ መጨናነቅ እንዳይከሰትም በቂ  ዝግጅት አድርገናል ባይ ናቸዉ። መምሪያ የመጣለትን ጥቆማ ተከትሎ በአዲስአበባ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አንስተዉ ከመነሻዉ ማስተካከል የሚቻልበት አማራጭ እንዳለም የስልጤ ዞን የትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ አቶ ሱልጣን ራህመቶ ጨምረዉ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በበረከት ሞገስ

photo_2024-06-13_20-17-41

ሰኔ 6፤2016 – እስራኤል ከ2024ቱ ኦሎምፒክ እንድትታገድ ተጠየቀ

 

በሲዊዘርላድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች እስራኤል በ2024 የኦሎምፒክ ጨዋታዎች እንዳትሳተፍ እገዳ እንዲጣልባት ጠይቀዋል።

የፍልስጤም ባንዲራ የያዙ ተቃዋሚዎች እስራኤል ከፓሪሱ የ2024 ኦሊምፒክ እንድትታገድ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በላውዛን ስዊዘርላንድ በሚገኘው የአለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፅሕፈት ቤት ፊት ለፊት አካሂደዋል።

በፍልስጤም ግዛት ለደረሰው የንፁሃን ጥቃት ትኩረት ለማሰጠት በላውዛን በሚገኘው የአለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፊት ለፊት ሰልፈኞች ተሰብስበው የነበረ ሲሆን፤ ኮሚቴው በእስራኤል ላይ እርምጃ እንዲወስድ ለማሳመን ሲሉ መገኘታቸው ተገልፆል።

ከሩሲያ እና ቤላሩስ የመጡ አትሌቶች በዚህ አመት ኦሎምፒክ ውድድሮች በገለልተኝነት እንዲሳተፉ ይፈቀድላቸዋል ሲል ኮሚቴው ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን ከሀምሌ 26 እስከ ነሐሴ 11 ባለው ጊዜ ውስጥ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ላይ ከሁለቱም ሀገራት የሚመጡ የመንግስት ባለስልጣናት በመክፈቻው ላይ እንዲሳተፉ አይፈቀድላቸውም፣የሀገራቱን ባንዲራ ፣ አርማም ወይም ብሄራዊ መዝሙሮችም እንዲጠቀሙም አይፈቀድላቸውም።

ተቃዋሚዎቹ የእስራኤልን “ዘር ማጥፋት” በመቃወም የፍልስጤም ባንዲራዎችን እና ባነሮችን በመያዝ “እስራኤል የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅማለች”፣ “ሰብአዊነት ወድቋል” እና “ፍልስጤም ነፃ ትሁን” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል። ሰላማዊ ሰልፉም ከሁለት ሰአት በላይ የፈጀ ሲሆን ያለ ፖሊስ ጣልቃ ገብነት በሰላም ተጠናቋል ተብሏል።

እ.ኤ.አ. ጥቅምት 7 2023 በሐማስ ከደረሰው ጥቃት በኋላ እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን ጥቃት በቀጠለችበት ወቅት አለም አቀፍ ውግዘት ገጥሟታል፣የተመድ የፀጥታው ምክር ቤትም አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈፀምም ጠይቋል።

በሚሊዮን ሙሴ