photo_2024-06-19_09-02-04

ሰኔ  12፤2016 – ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን አቀባበል የፒዮንግያንግ ከተማ አደባባይ በፊኛዎች እና ባንዲራዎች ማጌጡ ተሰማ

ከተማዋ ፑቲንን ለመቀበል ባደረገችው ዝግጅት የፒዮንግያንግ ማዕከላዊ አደባባይ በሰዎች ተጨናንቋል። በሰሜን ኮሪያ መስራች በኪም ኢል ሱንግ ስም በተሰየመው አደባባይ ላይ ፑቲን ሲደርሱ ከፍተኛ አቀባባል ዛሬ ማለዳ ተደርጎላቸዋል። መደበኛ ልብስ የለበሱ ልጆች ትናንሽ ፊኛዎችን ይዘው ታይተዋል። አደባባዩ ዙሪያ ያሉ ህንጻዎች በሩሲያ እና በሰሜን ኮሪያ ባንዲራ ያጌጡ ሲሆን የሁለቱን ሀገራት መሪዎች ምስል ተሰቅሎባቸዋል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በታጠቁ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚፈልጉ ፍንጭ ሰጥተዋል። ፑቲን ፒዮንግያንግ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በቀይ ምንጣፍ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ፑቲን ዛሬ እሮብ ማለዳ ጎህ ሳይቀድ በሰሜን ኮሪያ ዋና ከተማ ደርሰዋል። ሁለቱ መሪዎች ሲጨባበጡ እና አንዲት ሴት ለፑቲን ቀይ አበባ ስትሰጥ የሚያሳይ መረጃን የሰሜን ኮርያ መገናኛ ብዙሃን አጋርተዋል። ከዛም መሪዎቹ ወደ ኩምሱሳን ግዛት እንግዳ ማረፊያ ቤት ሲያቀኑ ታይተዋል።

የመንግስት የዜና ወኪል ኬሲኤንኤ የሁለቱ መሪዎች ስብሰባ በሰሜን ኮሪያ እና በሩሲያ መካከል ያለውን ወዳጅነት እና አንድነት “የማይበገር እና ዘላቂነት” ያሳየ ታሪካዊ ክስተት ነው ብሏል። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት “ዓለም አቀፍ ፍትህን ፣ ሰላምን እና ደህንነትን ለመጠበቅ እንዲሁም ለአዲሱ የብዝሃ-ዋልታ ዓለም ግንባታን ለማፋጠን እንደ ጠንካራ ስትራቴጂካዊ ምሽግ ሆኗል” ብለዋል ። ፑቲን ከ 24 ዓመታት በኋላ ወደ ሰሜን ኮሪያ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን አድርገዋል።

በየካቲት 2022 ሙሉ በሙሉ በዩክሬን ላይ ሩሲያ ወረራ ከጀመረች በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል። ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ የጦር መሳሪያ ዝውውር በመካከላችን የለም ብለው ቢክዱም ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ ግን ቃል ገብተዋል። ፑቲን እና ኪም ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በምስራቅ ሩሲያ በመስከረም 2023 ነበር። ሰሜን ኮሪያ በኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቿ እና በሚሳኤል ፕሮግራሞቿ ምክንያት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጥብቅ ማዕቀብ ለዓመታት ተጥሎባታል። ሩሲያም በዩክሬን ወረራ ምክንያት በዩናይትድ ስቴትስ እና በምዕራባውያን በኩል የተጣለባትን ማዕቀብ እየታገለች ትገኛለች።

ከሩሲያ እና ከሰሜን ኮሪያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት ቻይና የፑቲን እና የኪም ግንኙነት እንዳስደሰታት ገልፃለች። ፑቲን ከአንድ ወር በፊት ቻይናን መጎብኘታቸው ይታወሳል። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊን ጂያን የፑቲንን የፒዮንግያንግ ጉብኝት አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቤጂንግ “ሩሲያን ከባህላዊ ወዳጆቿ ጋር ያላት ግንኙነት ማሳደጓን በደስታ ትቀበለዋለች ሲሉ ተናግረዋል።

በስምኦን ደረጄ

Tags: No tags

2 Responses

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *