የ 16 ዓመቷ ታዳጊ ማህሌት ተክላይ መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ከመኖርያ ቤቷ ወደ ትምህርት በወጣችበት መታገቷን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን መዘገቡ አይዘነጋም።
ታዳጊዋ ከሶስት ወራት ፍለጋ በኋላ በዛሬው እለት ህይወቷ አልፎ መገኘቷን የአድዋ ከተማ ፖሊስ አዛዥ አቶ ተስፋዬ አማረ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን አረጋግጠዋል።
አቶ ተስፋዬ የታዳጊዋን ህልፈት ከማረጋገጣቸው ዉጪ ገዳይ ናቸዉ ተብለዉ የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉንም ለብስራት ተናግረዋል። ሆኖም ምን ያህል ሰዎች በቁጥጥር ስር ስለማዋላቸዉ ያሉት ነገር የለም።
ታዳጊዋ ማህሌት ተክላይ በእለቱ ከቀኑ 11 ሰዓት ከ 30 አካባቢ ነበር የቋንቋ ትምህርቷን ለመከታተል በወጣችበት የጠፋችዉ። ማህሌት ምሽቱን በተንቀሳቃሽ ስልኳ ወደ አባቷ በመደወል መታገቷን የሚያመላክት መረጃ ሰጥታ አጋቾቿም 3 ሚሊዮን ብር ጠይቀዉ እንደነበር ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን መዘገቡ አይዘነጋም።
የታዳጊዋ ማህሌት ተክላይ አስክሬን በእዛዉ አድዋ ከተማ ጭላ በተሰኘ አካባቢ መገኘቱንም ጣቢያችን ሰምቷል። ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያደርግም የአድዋ ከተማ ፖሊስ አዛዥ አቶ ተስፋዬ አማረ ጨምረው ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
በበረከት ሞገስ

2 Responses