photo_2024-01-20_13-35-11

ጥር 11፤2016 – አሽከርካሪውን ገድለው ሞተር ሳይክል የወሰዱ ተከሳሾች ከ24 ዓመት እስከ እድሜ ልክ እስራት ተቀጡ

 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በዳውሮ ዞን በሎማ ቦሣ ወረዳ ሻይቲ ፉላሳ ቀበሌ ተሳፋሪ መስለው ሞተር ሳይክል ለመቀማት አሽከርካሪውን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉ ተካሳሾች ከ24 ዓመት ፅኑ እስራት እስከ እድሜ ልክ እስራት መቀጣታቸው ተነግሯል ።

ተከሳሾች 1ኛ አረጋ አርጃ ፣ 2ኛ ካለብ ዲናቶ እና 3ኛ ሰውለሰው በቀለ ሲሆኑ  በረቀቀ መንገድ በምስጥር በመደራጀት ያልተገባ የንብረት ጥቅም ለማግኘት ሟች ጌታሁን ከንፈሻ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪ ላይ የግድያ ወንጀል መፈጸማቸው ተነግሯል ።

የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት ገደማ ከሚኖርበት ዲሣ ከተማ ተሳፋሪ በመምሰል በ3ኛ ተከሳሽ አቀናባሪነት ሟችን ጠርተው  በማስወጣት ወደ ገሣ ከተማ አስተዳደር አድርሰን በማለት በሟች ሞተር ሳይክል ተሳፍረው ለመሄድ እንደተስማሙ ተገልጿል ።

በዚህም መሠረት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በሟች ሞተር ሳይክል ተሳፍረው ወደ ሎማ ቦሣ ወረዳ ሻይቲ ፉላሳ ቀበሌ ኦቺ የሚባል ቦታ ሲደርሱ ሟችን ሽንት እንሸናለን በማለት ወርደው በቦታው በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለው አስክሬኑን ከእንጨት ጋር አስረው በማስቀመጥ የሟች ሞተር ሳይክል ይዘው እንደተሰወሩ ተጠቅሷል ።

ተከሳሾቹ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ከተሻገሩ እና ከአከባቢው ከተሰወሩ በኃላ የዞኑ ፓሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላትና ከህብረተሰብ ጋር ባደረገው ብርቱ ክትትል እንደተያዙ የዳውሮ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አ/ቶ ፍቃዱ ደምሴ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ። የዞኑ ፍትህ መምሪያ ልዩ ልዩ ወንጀሎች ዐቃቤ ህግ በሶስቱም ተከሳሾች ላይ ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መመሰረቱ ተገልጿል።

ተከሳሾች ችሎት ቀርበው የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም በማለት ክደው ቢከራከሩም በዐቃቤ ህግ የቀረበው ማስረጃ ተከሳሾች ወንጀል መፈጸማቸውን  የሚያስረዳ በመሆኑ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን እንደተሰጣቸውም ተነግሯል።  ነገር ግን ተከሳሾች አቅርበው ባሰሙት መከላከያ ማስረጃ የዐቃቤ ህግን ክስና ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተልፏል ።

ስለሆነም የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት አንደኛ ተከሳሽ አ/ቶ አረጋ አርጃ እና 2ኛ ተከሳሽ አ/ቶ ካለብ ዲናቶ በ24 አመት ጽኑ እስራት እና 3ኛ ተከሳሽ አ/ቶ ሰውለሰው በቀለ በዕድሜ ልክ እስራት እንድቀጡ ወስኗል።

በአበረ ስሜነህ

photo_2024-01-19_12-32-09

ጥር 10፤2016 – በአሜሪካ አንድ ግለሰብ 27 ሴቶች ከእኔ ጋር በነበራቸውን የፍቅር ግንኙነት ላይ አሉታዊ አስተያየትን በፌስቡክ ሰጥተዋል ሲል ክስ መሰረተ

 

በቺካጎ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ በፌስቡክ የፍቅር ጓደኝነት ቡድን ላይ ስለ እኔ አሉታዊ አስተያየቶችን ሰጥተዋል በማለት 27 ሴቶችን በመክሰስ 75 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ጠይቋል።

ግለሰቡ እነዚሁ ሴቶች እኔ በጣም ተንኮለኛ እና ከመናፍስታዊ አሰራር ጋር ትስስር ያለኝ በማስመሰል ጠርተውኛል ብሏል።የ32 አመቱ ኒኮ ዲ አምብሮሲዮ ከእርሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው በርካታ ሴቶች አሉታዊ ቆይታ ነበር ሲል በፌስቡክ ላይ የጋራ መድረክ በሆነው ‘ከተመሳሳይ ሰው ጋር በፍቅት ተጣምረን ይሆን’ በሚለው ግፅ ላይ ሴቶቹ ታሪካቸውን ካጋሩ በኋላ ስሜ ጠፍቷል ብሏል።

ታዋቂው ይህ የፌስቡክ ገፅ መነሻውን በኒውዮርክ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ ሌሎች ዋና ዋና የአሜሪካ ከተሞች ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል። የፌስቡክ ገፁ ዋና ተጠቃሚ ሴቶች ሲሆን ከፍቅረኛቸው ጋር የነበራቸውን ልማድ እርስ በእርስ ከመለዋወጣቸው ባለፈ ተመሳሳይ ወንድ ግን በተለያየ በአንድ አጋጣሚ ፍቅር ውስጥ ከነበሩ ያ ሰው ምን ዓይነት ባህሪና ድክመት እንዳለበት መረጃ የሚለዋወጡበት ስርዓት ነው።

የዚሁ ገፅ ሰለባ የሆነው ዲ አምብሮሲዮ በደርዘን የሚቆጠሩ ሴቶች ተንኮለኛ የፈለገውን ካገስኘ በኋላ የሚሰወር ሰው በማለት የገለፁት ሲሆን በአብዛኛው እርሱን የሚያንቋሽሹ አስተያየቶችን ጽፈዋል።ይህው የቺካጎው ሰው ታዲያ ሴቶቹ ላይ ፣የፌስቡክ ገፁን መስራች እና የፌስቡክ ወላጅ ኩባንያ ሜታ ለጠፋው ስሜ 75 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ክፈሉኝ ብሏል።

የሰውዬው ጠበቆች በተከሳሾቹ ድርጊት የተነሳ የስም ማጥፋት፣የማስፈራራት እና የግላዊ መብትን የሚጥስ ወረራ እንደተፈጸመበት እና ካሳ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል።ዲ አምብሮሲዮ ፎቶዎቼ በፌስቡክ ላይ መሰራጨቱ የበዛ አሉታዊ አስተያየቶች ዒላማ ሆኛለሁ “በግል ውርደት፣ አእምሮአዊ ስቃይ ፣የስሜት ጭንቀት፣ እንዲሁም የገቢ ማጣት” እንዳስከተለበት ተናግሯል።

በስምኦን ደረጄ

ጥር 10፤2016 – በበቆሎ እርሻ ዉስጥ ከማሳ ጋር የተዘራ አደንዛዥ እፅ እንዲወገድ ተደረገ

 

በምዕራብ አርሲ ዞን ወንዶ ወረዳ ከበቆሎ እርሻ ዉስጥ ከበቆሎ ጋር የተዘራ አደንዛዥ እፅ እንዲወገድ መደረጉን የወንዶ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ገለፀ።

የወንዶ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ኑሩ ጃርሶ ለብስራት ቴሌቬዥንና ራዲዮ እንደገለፁት በበቆሎ እርሻ ዉስጥ ከበቆሎ ጋር ተደባልቆ የተዘራ አደንዛዥ እፅ እንዲወገድ የተደረገዉ ህብረተሰቡ ለፖሊስ በሰጠዉ ጥቆማ መሆኑን ገልፀዋል።

በሻሸመኔ ዙሪያ በሻላና በወንዶ ገነት አካባቢ አርሶ አደሩ ከሰብል ምርቶች ጋራ በመቀላቀል ሀሽሽን በድብቅ ዘርቶ እንዲያበቅል የተደረገ በመሆኑ ማህበረሰቡ እራሱ ባደረገዉ ዉይይት ሀሽሽን ከአዝዕርት ጋራ ቀላቅሎ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ከበድ ያለ ዉሳኔ እዲተላለፍባቸዉ መወሰኑን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም አንዳንድ አርሶ አደርች ሀሽሽን ከሚያዘዋዉሩ ነጋዴዎችና ደላሎች በመታለል ከዲርጊቱ ያልተቆጠቡ በመሆናቸዉ ስር ነቀል ልዉጥ ለማምጣት ሰፊ እርምጃና የማነቃቂያ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ምክትል ኢንስፔክተር ኑሩ ጃርሶ ጨምረዉ ተናግረዋል።

በበቀለ ጌታሁን

ጥር 10፤2016 – በሰሜን ኮርያ የደቡብ ኮርያን ተከታታይ ድራማ ሲከታተሉ የተገኙ ታዳጊዎች የ12 ዓመታት ቅጣት ተጣለባቸው

 

በሰሜን ኮሪያ ሁለት ታዳጊ ወንድ ልጆች የደቡብ ኮርየን ድራማ በመመልከታቸው ለ12 ዓመታት ከባድ የጉልበት ሥራ በአደባባይ ተፈርዶባቸዋል። እ.ኤ.አ. በ2022 የተቀረፀ በሚመስል ቪዲዮ ላይ እንደተመላከተው ሁለት የ16 አመት ወንድ ልጆች በመቶዎች በሚቆጠሩ ተማሪዎች ፊት እጃቸውን በካቴና ታስረው በስታዲየም ውስጥ ይታያሉ።

በተጨማሪም የደንብ ልብስ የለበሱ የፖሊስ መኮንኖች ስህተታቸው በጥልቀት እንዲያሰላስሉ ሲገሰጹ ያሳያል። የቲቪ ድራማን ጨምሮ የደቡብ ኮሪያ የመዝናኛ ፕሮግረሞች በሰሜን ኮርያ መከታተል ክልክል ነው። ያም ሆኖ ግን፣ አንዳንዶች ዓለም አቀፋዊ ተመልካቾች ያላቸውን ያላቸውን የደቡብ ኮርያ ድራማዎች መከታተል ከባድ ቅጣት ሊያስጥል የሚችል ቢሆንም ይህንን ቅጣት ለመቀበል ሲደፍሩ ይታያል።

በ2020 ፒዮንግያንግ የደቡብ ኮሪያን መዝናኛ መመልከት ሆነ ማሰራጨት በሞት የሚያስቀጣ ህግ አውጥታ ነበር። የደቡብ ኮሪያ ፊልሞች በቻይና በኩል ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚገቡ ሲሆን ለሰሜን ኮርያ ወጣቶች ከመዝናኛነት ባለፈ ችግርና ጭንቀትን ለመርሳት እንደሚረዱ ይታመናል። የአሜሪካን ድራማ ስትመለከት ከተያዝክ ጉቦ ሰጥተህ ማምለጥ ትችላለህ ነገር ግን የኮሪያ ድራማ ከተመለከትክ ጥይት ይተኮስብኃል ሲል አንድ የሰሜን ኮርያ ተወላጅ ተናግሯል።

በስምኦን ደረጄ

ጥር 8፤2016 – ኢራን በፓኪስታን የሚገኙ ታጣቂዎች ላይ ኢላማ ያደረገ ጥቃት ፈጸመች

 

ኢራን በምእራብ ፓኪስታን የሚገኘውን ታጣቂ ቡድን መምታቷን አስታዉቃለች፣ይህም ባለፈው ሳምንት ኢራን በኢራቅ እና ሶሪያ ላይ ጥቃት ከተሰነዘረች በኋላ የአሁኑ ሶስተኛው የአየር ጥቃት ነው።የኢራን መንግስት ቲቪ እንዳስታወቀው ድርጊቱ በባሎቺስታን በሚገኘዉ ታጣቂው ጃኢሽ አል-አድል ጋር የተገናኙ ሁለት ቦታዎች ላይ ኢላማ ያደረገ ነዉ፡፡

የፓኪስታን ባለስልጣናት ሁለት ህጻናት ሲገደሉ ሌሎች ሶስት ደግሞ ቆስለዋል።ኢስላማባድ የአየር ድብደባው “ህገወጥ ድርጊት” መሆኑን ገልጾ “ከባድ መዘዞችን” ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል::ይህዉ ጥቃት ከ100 ቀናት በላይ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በእስራኤል እና በፍልስጤም ቡድን ሃማስ መካከል የዘለቀዉ ግጭት የወለደዉ ነዉ፡፡ ዩናይትድ ስቴትስና ዩናይትድ ኪንግደም በኢራን በሚደገፉት የየመን የሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር ውስጥ የንግድ መርከቦችን ማጥቃት መጀመራቸዉን ተከትሎ ግጭቱ ተስፋፍቷል።

በፓኪስታን ኢራን የፈጸመችዉ ጥቃት በሰፊው ደቡብ ምዕራብ ባሎቺስታን ድንበር ግዛት ውስጥ ያለች መንደርን መቷል።ሰኞ ረፋድ ላይ ኢራን በሰሜናዊ ኢራቅ ኢርቢል ከተማ የባሊስቲክ ሚሳኤሎችን በመተኮሷ በአሜሪካ ውግዘት አስከትሎባታል።የኢራን አብዮታዊ ጥበቃዎች የኢራቅ ከፊል ራስ ገዝ በሆነው የኩርዲስታን ክልል የእስራኤል “የስለላ ዋና መሥሪያ ቤት” ናቸው ያላቸውን ስፍራዎች መምታቱን አስታዉቋል።

ኢራን በሶሪያ ሰሜናዊ ምዕራብ ኢድሊብ ግዛት ኢላማዎችን በመምታቱ ከሶሪያ መንግስት ቁጥጥር ውጪ በሆነዉና በሀገሪቱ የተቃዋሚዎች ምሽግ ነዉ በተባለ ስፍራ ጥቃት አድርሳለች፡፡በግዛቷ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ፓኪስታን “ኢራን የአየር ክልሌን ያለምክንያት ጥሳለች” ስትል ከሳለች፡፡

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-01-17_14-05-36

ጥር 8፤2016 – የግብረ-ስጋ ግንኙነት እንዲፈፅሙ ጠይቋት ፈቃደኛ ባለመሆኗ ሟችን በቢላዋ  ወግቶ የገደለው ተከሳሽ በ23 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ

 

ዳንኤል በርሄ ስዩም የተባለ ተከሳሽ ሀምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ በግምት 3፡30 ሲሆን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ሳሪስ አደይ አበባ መኪና መሻገሪያ ድልድይ አካባቢ በሚገኘው ፍሬሕይወት ህንፃ ውስጥ ሟችን የሽንት ቤት ቁልፍ ክፈችልኝ ብሏት ስትከፍትለት የግብረ-ስጋ ግንኙነት እንዲፈፅሙ ጠይቋት ፈቃደኛ ባለመሆንዋ አንገትዋን በቢላ በመውጋት ሕይወትዋ እንዲያልፍ አድርጓል፡፡

በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕ/አ 539/1/ሀ መሰረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ መቆየቱን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክሮች በማስረጃነት አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት ተከሳሽ በ23 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡

ጥር 8፤2016 – ቻይና ለተከታታይ ሁለተኛ አመት የህዝብ ቁጥሯ ቀነሰ

 

ቻይና የህዝብ ቁጥሯ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ለተከታታይ ሁለት አመታት መቀነስ ማሳየቱን የቻይና ብሔራዊ የስታትስቲክስ ቢሮ አስታዉቋል።

ቻይና በ 2022 አመት ከስልሳ አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የህዝብ ቁጥሯ ቀንሶ በአለም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያለባት የሚለዉን ቅጽያ ወደ ህንድ ማዘዋወሯ ይታወሳል። በ 2022 አመትም በ 2.8 ሚሊዮን የቻይና የህዝብ ቁጥር ቀንሶ ወደ 1.411 ቢሊዮን ወርዶ ነበር።

በ 2023 አመትም በቻይና ወደዚህች ምድር ከተቀላቀሉት የዉልደት መጠን ይልቅ በአመቱ የተመዘገበዉ ሞት እንደሚበልጥ ተዘግቧል። ይህም የህዝብ ቆጠራ ከተጀመረበት 1949 ወዲህ በቻይና የተመዘገበው ዝቅተኛ የዉልደት መጠን መሆኑ ተነግሯል።

በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ አመትም የዉልደት መጠኑ ከ 1 ሺህ ሰዎች 6.39 ህጻናት ይገኛሉ የሚል ነዉ። በባለፈዉም አመት በቻይና 9.02 ሚሊዮን ህጻናት ሲወለዱ በቀዳሚዉ አመት ከተመዘገበው 9.56 ሚሊዮን ህጻናት ቁጥር ያነሰ ነዉ ።

በበረከት ሞገስ

photo_2024-01-17_10-14-52

ጥር 8፤2016 – የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ልጅ በቱርክ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ሰው በመግደሉ ቅጣት ተጣለበት

 

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ልጅ በቱርክ ውስጥ መኪናውን ሲያሽከረክር ከሞተር ሳይክል መልእክተኛ ጋር በመጋጨቱ እና ተጎጂው ከቀናት በኃላ ህይወቱ በማለፉ 900 ዶላር ተቀጥቷል ። የኢስታንቡል ፍርድ ቤት ባለፈው ማክሰኞ መሀመድ ሀሰን ሼክ መሀሙድን በቸልተኝነት አደጋ በማድረስ ለተፈጠረው የሞት ምክንያት ጥፋተኛ ብሎታል። ያሽከረክረው የነበረው መኪና በህዳር ወር ላይ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪውን ዩኑስ ኤምሬ ጎሰርን ገጭቷል።

የተጎጂው ጎሰር ጉዳት የተከታተሉ ሰዎች ቅጣቱ በጣም ቀላል ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል እናም ፍትህ አልተሰጠም ሲሉ ተደምጠዋል። የፕሬዝዳንቱ ልጅ መሐሙድ በታኅሣሥ ወር ከቱርክ መውጣቱ የፖሊስ ምርመራ በተቃዋሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ አስነስቷል ሲል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የቱርክ ፖሊስ ተቺዎች የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ልጅ መሀሙድ ከሀገር እንዲወጠ ባለስልጣናቱ ፈቅደውላቸዋል ብለዋል።

ቱርክ መሀሙድ ላይ አለም አቀፍ የእስር ማዘዣ አውጥቶ ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት በገዛ ፍቃዱ ወደ ቱርክ ተመልሷል። ፍርድ ቤቱ መጀመሪያ ላይ የሁለት አመት ተኩል እስራት ቢፈረድበትም ይህን ውሳኔ ወደ ገንዘብ ቅጣት ተቀይሮታል።በችሎቱ ወቅት ያሳየው ፀፀት ለፍርዱ መቀነስ ምክንያት ነው የተባለ ሲሆን ለስድስት ወራት ያህል መኪና እንዳያሽከረክርም ተከልክሏል።

አቃቤ ህግ ግን የስድስት አመት እስራት እንዲጣልበት ጠይቆ ነበር። የሞተር ሳይክል ተላላኪ ህይወት 27,000 ሊራ ወይም 900 ዶላር ብቻ ሊሆን አይችልም፤ ይህ ፍትህ ነው ወይ? ሲሉ የኩሪየር መብቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ሜሱት ቄኪ ከፍርድ ቤቱ በራፍ ላይ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ባለፈው ወር፣ በተፈጠረው የህዝብ ቁጣ እየበረታ ሲሄድ፣ የኢስታንቡል ከንቲባ ኤክሬም ኢማሞግሉ በህዳር 30 ስለተፈጠረው ክስተት የሲሲቲቪ ምስል በኤክስ ገፅ ላይ አጋርተዋል። በተሽከርካሪ በተጨናነቀ መንገድ መጋጠጠሚያ ላይ አንድ ሞተር ሳይክል ከጀርባው በመኪና ሲመታ ይታያል። ተጎጂው የሁለት ልጆች አባት የ38 አመቱ ጎከር ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ህይወቱ ግን ማትረፍ ሳይቻል ከስድስት ቀናት በኃላ መሞቱ ተሰምቷል።የመጀመርያው የፖሊስ ዘገባ ላይ ጎከር ጥፋተኛ እንደነበር እና በዚህም ምክንያት መሀሙድ እንደተፈታ ገልጿል። ነገር ግን ጫናው ሲበረታበት ፖሊስ ቃሉን ቀይሯል።

በስምኦን ደረጄ

ጥር 8፤2016 – በቡታጅራ ከተማ በተሽከርካሪ የታገዘ ስርቆት ሲፈፅሙ የተገኙ 27 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ

 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ህገ-ወጥ እንቅስቃሴን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተደረገ ስምሪት በዘረፋ ወንጀል የተሰማሩ 27 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል ።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 17 ግለሰቦች ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም ለስርቆት ሲንቀሳቀሱባቸው ከነበሩ 8 ባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪ እና አንድ ሞተር ሳይክል ጋር እንደተያዙ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ክፍል ሃላፊ ምክትል ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል  ።

ሌሎች 10 ተጠርጣሪዎች ቀደም ሲል የተያዙ ሲሆን ምርመራ ተጣርቶ ክስ እንደተመሠረተባቸው አክለዋል ። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ ከሌሎች አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የገቡ ግለሰቦች ይገኙበታል ተብሏል ።

ማህበረሰቡ በግብይት ፣ በንግድና በሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ስልክ ገንዘብና ሌሎች ንብረቶችን በጥንቃቄ እንዲይዝ እና ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በአበረ ስሜነህ

photo_2024-01-16_09-59-07

ጥር 7፤2016 – የኬንያ ዋና ዳኛ ፕሬዝዳንት ሩቶ በዳኞች ላይ በሰነዘሩት ዛቻ ዙሪያ መነጋገር እንደሚፈልጉ አስታወቁ

 

የኬንያ ዋና ዳኛ ማርታ ኩሜ እንዳሉት በአንዳንድ ዳኞች ላይ ፕሬዝዳንቱ የፈጠሩትን ስጋት ለመፍታት እንዲቻል የፍትህ አካላት ለፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ደብዳቤ ፅፈዋል። ፕሬዝዳንት ሩቶ ከቅርብ ቀናት ወዲህ በፍትህ አካላት ላይ ጦርነት ከፍተዋል አንዳንድ ስማቸውን ያልገለጿቸውን ዳኞች  “ሙሰኞች” በማለት የመንግስታቸውን ፕሮጀክቶች ከተቃዋሚዎች ጋር በማበር እያሰናከሉ ነው ሲሉ ከሰዋል።

ኩሜ ሰኞ እለት በተካሄደው የሚዲያ ማብራሪያ ላይ እንደተናገሩት በፍትህ አካላት ላይ የሚሰነዘሩት ጥቃቶች ሀገሪቱን ለሁከትና ብጥብጥ እየዳረገ ነው ብለዋል። እንዲህ ዓይነት ጥቃይ ያለማቋረጥ እንዲቀጥል ከፈቀድን ወደ ማይታወቅ የእርስ በርስ ግጭት ሊመራ ወደሚችል እና ህገ-መንግስታዊ ቀውስ ላይ ያደርቀናል ሲሉ ወይዘሮ ኩሜ አክለዋል። “ስለዚህ ይህንን ውይይት ከፕሬዝዳንቱ እንጠብቃለን ፣ እንዲደረግም ውይይቱ ደብዳቤ ጽፈናል እናም ፕሬዚዳንቱ ቀጠሮ ይሰጡናል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል ።

የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ፕሬዝዳንት ሩቶ በማውገዝ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ባደረጉት ንግግር ዳኞችን ለማስፈራራት ሞክረዋል ሲሉ መክሰሳቸው ይታወሳል። እ.ኤ.አ በመስከረም 2022 ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንቱ በኑሮ ውድነት ላይ አዳዲስ ቀረጥ በማውጣታቸው ወቀሳ ደርሶባቸዋል። ሁለት አዳዲስ ታክሶች ማለትም የመኖሪያ ቤት ቀረጥ እና ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ቅነሳዎች ሲሆኑ ይህም በፍርድ ቤት ክስ እንዲመሰረትባቸው ሆኗል።

በአበረ ስሜነህ