ጥር 6፤2016 – የዓለማችን አምስት ቱጃር ሰዎች ከ2020 ወዲህ ያላቸውን  ሀብት በእጥፍ አሳድገዋል ተባለ

 

የዓለማችን አምስቱ ቱጃሮች ከ2020 ወዲህ ሀብታቸው በእጥፍ መጨመሩ በዳቮስ፣ ስዊዘርላንድ በተካሄደው አመታዊ ስብሰባ ላይ ኦክስፋም የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት አስታውቋል።

አምስቱ ሰዎች ባለፉት አራት ዓመታት በሰዓት 14 ሚሊዮን ዶላር ሀብታቸውን ያሳደጉ ሲሆን በድምሩ 869 ቢሊዮን ዶላር ግምት ሀብይ እንዳላቸው ኦክስፋም በዛሬው ዕለት ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል።አምስቱ ከፍተኛ ትርፍ በትርፍ ሆነዋል የተባሉት ባለሀብቶች የኤልቪኤምኤች ኃላፊ በርናርድ አርኖልት፣ የአማዞን ባለቤት ጄፍ ቤዞስ፣ ኢንቨስተሩ ዋረን ቡፌት፣ የኦራክል መስራች ላሪ ኤሊሰን እና የቴስላ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢሎን ማስክ ናቸው።

ምንም እንኳን የአምስቱ ቢሊየኖሮች ኃብት በእጥፍ ቢጨምር 5 ቢሊዮን የዓለም ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ድህነት ውስጥ ገብተዋል ሲል ኦክስፋም ተናግሯል። ቢሊየነሮች እ.ኤ.አ. በ2020 ከነበራቸው ሀብት የ3.3 ትሪሊየን ዶላር ብልጫ ያለው ሀብት አከማችተዋል።

እነዚሁ አምስቱ ቢሊየነሮች ከ10ሩ የአለም ታላላቅ ኩባንያዎች 7ቱን እንደሚመሩ በለንደን መቀመጫውን ያደረገው የበጎ አድራጎት ድርጅት ገልጿል።አሁን ያለው አዝማሚያ በዚሁ ከቀጠለ አለም በአስር አመታት ውስጥ የመጀመሪያ ትሪሊዮኔር ባለቤት ትሆናለች ነገር ግን ድህነት ለ229 አመታት አይጠፋም ሲል ይህው የፀረ ድህነት ቡድኑ ኦክስፋም ገልጿል።

ኦክስፋም መንግስታት የዋና ስራ አስፈፃሚዎችን ክፍያ መቆጠብ ፣የግል ሞኖፖሊ ማዳከም እና የሃብት ግብር ማስተዋወቅ አለባቸው ሲል ምክረ ሀሳብ ሰንዝሯል።በ1970ዎቹ በጀርመን መሐንዲስ እና ኢኮኖሚስት ክላውስ ሽዋብ “የባለድርሻ አካላት ካፒታሊዝምን” ከፍ ለማድረግ የተጀመረው ዓመታዊ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም (WEF) ከመከፈቱ በፊት ስለ እኩልነት አመታዊ ሪፖርቱን ኦክስፋም ያወጣል።

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-01-15_10-27-58

ጥር 6፤2016 – በቦሌ አየር መንገድ በኩል የካንሰር መድኃኒቶች በሕገወጥ መንገድ ሊገባ ሲል ተያዙ

 

ግምታዊ ዋጋቸው ከ750 ሺ ብር በላይ የሚያወጡ የካንሰር መድኃኒቶች በሕገወጥ ሁኔታና መንገድ በቦሌ አየር መንገድ ተርሚናል በኩል ሊገቡ ሲል መያዙን በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የደቡብ ምስራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስታውቋል።

በባለስልጣኑ የደቡብ ምስራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የቦሌ ተርሚናል አስተባባሪ አቶ አለምሰገድ ካብቲመር  እንደተናገሩት ታህሳስ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በአንድ ግለሰብ የተለያዩ ሻንጣዎች ውሰጥ ተደብቀው ወደ አገር ውስጥ በህገወጥ መንገድ ሊገቡ ያሉት የካንሰር መድኃኒቶች የባለስልጣኑና  የጉምሩከ ባለሙያዎች የተቀናጀ ፍተሻ አማካኝነት በቁጥጥር ስር መዋል ችሏል፡፡

504 ብዛት ያላቸው ጥራታችው፤ ደህንነታቸውና ምንነታቸው በባለስልጣኑ ሳይረጋገጡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ወደ አገር ውሰጥ ሊገቡ ሲሉ የተያዙት በመርፌ የሚሰጡ የካንሰር መድኃኒቶች መሆናቸው ብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል። መድኃኒቶቹ በሕንድ አገር የተመረቱ ሲሆኑ ግለሰቡም ከሕንድ ወደ አዲስ አበባ በሕገወጥ መንገድ ለማስገባት ሲሞክሩ  በቁጥጥር ስር መዋሉን አቶ አለምሰገድ  ጨምረው ተናግረዋል።

እነዚህ መድኃኒቶች  በጤናው ላይ ጉዳት ያስከትሉ ይችሉ እንደነበር በመግለጽ ሕገወጥ ድርጊት በሀገር ኢኮኖሚም ላይ ቢሆን የራሱ ችግር ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሕብረተሰቡ ቁጥጥር በሚደረግባቸው የምግብና የጤና ግብዓቶች ዙሪያ ማንኛውም ሕገወጥ ደርጊት ሲመለከት በባለስልጣኑ ነጻ የስልክ መስመር 8482 ጥቆማ እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

ጥር 6፤2016 – በንፋስ ስልክ ቀለም ፋብሪካ ላይ ከባድ የእሳት አደጋ ደርሷል❗️❗️

 

በንፋስ-ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7  ንፋስ ስልክ ቀለም ፋብሪካ ላይ ከባድ የእሳት አደጋ ተነስቶ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱን ለማጥፋት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ ኮሚሽን ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን አስታውቋል።።

አደጋው ያደረሰውን ጉዳት እና በአደጋው ዙሪያ መረጃዎች እንደደረሰን ወደ እናንተ የምናቀርብ ይሆናል።

ተጨማሪ አለን…

በትግስት ላቀው

ጥር 6፤2016 – በራፋ በኩል የሚደረገውን እርዳታ የሚዘገየው በእስራኤልን ‘ግትርነት’ የተነሳ ነው ስትል ግብፅ ተናገረች

 

የግብፅ መንግስታዊ መረጃ አገልግሎት (ኤስአይኤስ) ሊቀመንበር የሆኑት ዲያ ራሽዋን እንዳሉት በራፋ እና በሌሎች የድንበር ማቋረጫዎች ወደ ጋዛ እርዳታ ሊገባ ያልቻቸው በእስራኤል ግትርነት የተነሳ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ባለፉት 100 ቀናት ውስጥ የእስራኤል ባለስልጣናት ግትርነት እና ሆን ተብሎ በሌሎች የጋዛ ሰርጥ መሻገሪያዎች ላይ የእርዳታውን ፍተሻ በማዘግየት ወደ ፍልስጤም በኩል እንዲያልፍ ባለመፍቀድ ወታደራዊ ቁጥጥር የተነሳ ነው ሲሉ አክለዋል።

በጋዛ የእስራኤል ጦርነት የጀተመረበትን 100ኛ ቀናትን በማስመልከር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዓለም ዙሪያ ከፖርቹጋል እስከ ቱርክ ፣ ከዩናይትድ ኪንግደም እስከ ፓኪስታን ጎዳናዎች ላይ በመውጣት ለፍልስጥኤማውያን አጋርነታቸውን አሳይተዋል። በሌላ በኩል የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ በዚህ ሳምንት ወደ ዮርዳኖስ፣ እስራኤል፣ የፍልስጤም ግዛቶች እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እንደሚጓዙ ቢሮዋቸው በዛሬው እለት ገልጿል።

ዎንግ ከማቅናታቸው በፊት በጋዛ የዜጎች ሞትን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ለጋዜጠኞች በሰጡት ምላሽ “እንደ እስራኤል ወዳጅ አለም አቀፍ ህግ አስፈላጊ መሆኑን ማረጋገጥ እንቀጥላለን” ስትል ሚኒስትሯ ተናግራለች። በዩናይትድ ስቴትስ በሚመራው የቀይ ባህር ዘመቻ ላይ የአውስትራሊያን ሚና በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ዎንግ “ከጦር ዘመቻው ውጭ ብንሆንም የሰው ሃይል አቅም ውስጥ እንሳተፋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው በጋዛ የሚገኙ ቀሪ ታጋቾች ከሃማስ እጅ እንዲወጡ ጦርነቱ የተጀመረበትን 100ኛ ቀን በማስመልከት ጥሪ አቅርበዋል። “በጋዛ ውስጥ የ100 ቀናት ምርኮ በጣም ረጅም ነው” ሲሉ ብሊንከን በኤክስ ላይ በጽሁፍ አጋተዋል። አክለውም “ስድስት አሜሪካውያንን ጨምሮ ቀሪዎቹ ታጋቾች በሙሉ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እስኪገናኙ ድረስ ዩናይትድ ስቴትስ እረፍት አይኖራትም ብለዋል።

በስምኦን ደረጄ

ጥር 3፤2016 – ለገና በዓል ማክበሪያ ተማሪዎቻቸዉን እስከ 1 ሺህ ብር ድረስ የጠየቁ ትምህርት ቤቶች መኖራቸዉን ወላጆች ተናገሩ

 

👉 መንግስት በትምህርት ቤቶች የወርሃዊ እና ሌሎች ክፍያዎች ላይ ልጓም ሊያበጅ ይገባል ብለዋል ወላጆች

በየአመቱ በወላጆች እና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል የሚፈጠረዉ አለመግባባት ዘላቂ እና ወጥ የአሰራር መፍትሔ የሚያስፈልገው ጉዳይ መሆኑን ወላጆች ተናግረዋል። ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ያነጋገራቸው ወላጆች ለልጆቻቸዉ የገና በዓል ማክበሪያ ከትምህርት ቤቶቻቸዉ እስከ 1ሺህ ብር ድረስ እንደተጠየቁ ተናግረዋል።

ወላጆች በየአመቱ መጨረሻ እና መጀመሪያ ላይ ብቻ የሚዲያዎች ርዕስ እና የመንግስት ስራ የሚሆነዉ የግል ትምህርት ቤቶች ወርሃዊ ክፍያ በቂ ትኩረት ሊሰጠዉ የሚያሻ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። ወላጆች ከዘንድሮዉ በበለጠም መጪዎቹ ጊዜያት አስጊዎች መሆናቸዉን አንስተዋል።

አንዳንድ ወላጆች መንግስት የራሱን የትምህርት ቤቶች ደረጃ አዉጥቶ በእርሱ መሰረት ታሪፍ ሊተምንበት ይገባልም ብለዋል። በአንጻሩ በመምህራን ደሞዝ እየተንተራሰ የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎች በትክክል ለመምህራን ክፍያ ላይ መዋሉንም ሊከታተል ይገባል ብለዋል። ትምህርት ወደ ንግድ ማዘንበሉም የትምህርት ጥራቱ እንዳይሻሻል አድርጎታል የሚሉም አልጠፉም። በአንጻሩ የትምህርት ጥራት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሰልጣን ወላጆችን ከትምህርት ቤቶች ጋር በማስማማት ጭማሪዉን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ቢገልፁም ይህም ፍትሃዊነት የጎደለዉ ነዉ ብለዉናል።

የኢኮኖሚ ባለሙያና የኢኮኖሚክስ ትምህርት መምህር የሆኑት አቶ ፋሲል ጣሰዉ ፤ በትምህርት ቤቶች ላይ የሚደረገዉ የዋጋ ጭማሪ ከገበያ ስርዓቱ ጋር የተጻረረ መሆኑን ጠቅሰዋል። አክለዉም መንግስት በፖሊሲ በታገዘ መልኩ ለትምህርት ቤቶች የራሳቸዉን የመስሪያ ቦታ እንዲያገኙ ማመቻቸት ፤ ርካሽ የሰራተኛ ሀይል የሚል ፖሊሲዉን መቀየርና ሰራተኞች የተሻለ ገቢ ሊያገኙበት የሚችሉበትን አማራጭ መመልከት እንዳለበት ምክረ ሃሳባቸዉን ሰጥተዉናል።

በበረከት ሞገስ

ጥር 3፤2016 – በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ስድሰት ወራት 31 ሰዎች በድንገተኛ አደጋዎች ህይወታቸዉ ማለፉ ተነገረ

 

በ2016 ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ 239 ድንገተኛ አደጋዎች መድረሳቸውን የአዲስ አበባ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ ኮሚሽን አስታውቋል ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት ባጋጠሙት 239 አደጋዎች ከ475 ሚሊየን ብር በላይ ንብረት ሲወድም የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ባደረጉት ጥረት 7.8 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን ተችሏል፡፡

ከደረሱት አደጋዎች መካከል 208 አደጋዎች በአዲስ አበባ ያጋጠሙ ሲሆን 33 አደጋዎች ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የደረሱ መሆናቸውንን ተነግሯል፡፡በስድስት ወራቱ ካጋጠሙት ከአደጋዎቹ ዉስጥ 150 የሚሆኑት የእሳት አደጋዎች ሲሆኑ 89 አደጋዎች ከእሳት ዉጪ ያጋጠሙ አደጋዎች ናቸው ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል 31 ሰዎች ከእሳት ዉጪ ባጋጠሙ ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ህይወታቸዉ አልፎ የተገኙ ሲሆን አስከሬናቸው የኮሚሽኑ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አንስተዉና አዉጥተዉ ለፖሊስ አስረክበዋል ያሉን አቶ ንጋቱ የደረሱትን አደጋዎች ለመቆጣጠር በተደረገ ጥረት ቁጥራቸዉ 25 የሆኑ ሰዎችን ከአደጋዎቹ ህይወታቸውን መታደግ ተችሏል ።

አደጋዎቹ የደረሱት ወንዝ ዉስጥ፣ተቆፍረዉ ክፍቱን በተተዉ ጉድጓዶች ፣በኤሌክትሪክና በመሳሰሉት ናቸዉ፡፡ ከነዚህ ዉስጥም ፖሊስ ምርመራ እያደረገባቸዉ የሚገኙ አንዳሉበት ተመላክቷል፡፡

በትግስት ላቀዉ

ጥር 3፤2016 – የየመኑ ሁቲ በአሜሪካ እና እንግሊዝ የሚፈፀምበት ጥቃት ለጋዛ የሚሰጠውን ድጋፍ እንደማያስቆመው አስታወቀ

 

ሁቲዎች በቀይ ባህር ወደ እስራኤል የሚሄዱ መርከቦችን ማጥቃት እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን ይታወሳል። የቡድኑ ቃል አቀባይ መሐመድ አብዱልሰላም እንደተናገሩት “በቀይ እና በአረብ ባህር ላይ ለአለም አቀፍ የባህር ጉዞ ምንም አይነት ስጋት ስለሌለ ጥቃቱ ይቀጥላል። ኢላማው የእስራኤል መርከቦችን መግታት ነው ሲሉ ገልፀዋል። አብዱልሰላም የዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም ጥቃቱ “የመንን ፍልስጤም እና ጋዛን ከመደገፍ ያግዳታክ” ብለው ካሰብ  ይሳሳታሉ ሲሉ አክለዋል።

የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ጦር በየመን የሁቲ አማጽያን ላይ ኢላማ ያደረገ የአየር ጥቃት መፈፀማቸውን ገልፃዋል። በዋና ከተማዋ ሰነዓ፣ በሁዳይዳህ የቀይ ባህር ወደብ፣ በዳማር እና በሰሜናዊ ምዕራብ የሁቲ ጠንካራ ግዛት ሰአዳ ላይ ድብደባ መፈፀማቸው ተዘግቧል። ፕሬዝዳንት ባይደን ጥቃቱ በኢራን የሚደገፉ ሁቲዎች ከህዳር ወር ጀምሮ በቀይ ባህር መርከቦች ላይ ላደረሱት ጥቃት ምላሽ ነው ብለዋል።

ሁቲዎች አብዛኛውን የመን ግዛት የተቆጣጠሩ ሲሆን ወደ እስራኤል የሚያመሩ መርከቦች ላይ በማነጣጠር ሃማስን እየደገፉ ይገኛል። የሃውቲዎች ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ እና እንግሊዝ ለዚህ “ግልጽ ጥቃት” “ከባድ ዋጋ እንደሚከፍሉ” አስጠንቅቀዋል። የሮያል ኤር ሃይል የጦር አውሮፕላኖች በወታደራዊ ተቋማት ላይ “ያነጣጠሩ ጥቃቶችን” ለመፈጸም ረድተዋል ሲሉ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ አክለውም ጥቃቱ “እራስን ለመከላከል የተገደቡ፣ አስፈላጊ እና ተመጣጣኝ እርምጃዎች ናቸው” ብለዋል። ኔዘርላንድስ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ባህሬን የተልእኮው አካል በመሆን ድጋፍ አድርገዋል ሲሉ ባይደን በበኩላቸው ተናግረዋል።

በስምኦን ደረጄ

ጥር 2፤2016 – የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሄሊኮፕተር እና መንገደኞች በአልሻባብ እጅ ውስጥ መግባታቸው ተሰማ

የሶማሊያ ታጣቂ ቡድን አልሸባብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሄሊኮፕተርን ከስምንት የሚጠጉ ተሳፋሪዎች እና የበረራ ሰራተኞች ጋር መያዙን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ሄሊኮፕተሩ በማዕከላዊ ሶማሊያ በቡድኑ እጅ ስር በሚገኝ ስፍራ ላይ አርፏል። በሶማሊያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮ (ኡንሶም) ሄሊኮፕተሩ የህክምና አቅርቦት ላይ እንደነበር በመግለፅ ክስተቱ መፈጠሩን አረጋግጧል።

አልሸባብን ተልዕኮው ባይጠቅስም ለማስለቀቅ ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው ብሏል። በኤኤፍፒ የዜና ወኪል የታየውን ክስተት አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳለው ሄሊኮፕተሯ  ከዱሳማሬብ በስተደቡብ ምስራቅ 70 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ያረፈ ሲሆን በአውሮፕላኑ ውስጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኛ አለመኖራቸውን ገልጿል።በውስጡ የነበሩ ሰዎች የሶስተኛ ወገን የስራ ተቋረጮች መሆናቸውን ዘገባው አመላክቷል።

በሄሊኮፕተሩ ውስጥ የተሳፈሩት ሰዎች ዜግነት እና ብዛታቸው በትክክል አልተገለፀም። አንድ ተሳፋሪ ሲሞት ሁለት ሌሎች ደግሞ መሸሻቸው ተዘግቧል። አልሸባብ በደቡብ እና መካከለኛው ሶማሊያ ሰፊ ግዛቶችን አሁንም ተቆጣጥሮ ይገኛል። ቡድኑ ከአልቃይዳ ጋር የተቆራኘ ሲሆን ለ20 አመታት ያህል የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ ቆይቷል።ሄሊኮፕተሯን በቁጥጥር ስር በአልሻባብ መዋሏን የጋልጉዱግ ክልል የጸጥታ ሚኒስትር መሀመድ አብዲ አዳን አረጋግጠዋል።

በሄሊኮፕተሩ ላይ በርካታ የውጭ ሀገራት ዜጎች እና ሁለት የሀገር ውስጥ ተወላጆች እንደነበሩ የሶማሊያ ወታደራዊ ባለስልጣን ሻለቃ ሀሰን አሊ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል። “በተጨማሪም የህክምና ቁሳቁስ ጭኖ የነበረ ሲሆን የተጎዱ ወታደሮችን ከጋልጉዱድ ክልል ማጓጓዝ ነበረበት” ሲሉ ተናግረዋል። ሄሊኮፕተሩ በአልሸባብ ላይ የመንግስት ሃይሎች ባደረገው ጥቃት በግንባሩ አቅራቢያ ወደሚገኘው ዊሲል ከተማ በማቅናት ላይ ነበር።

በስምኦን ደረጄ