ጥር 13፤2016 – በአሜሪካ በከባድ አውሎ ንፋስ ከ90 በላይ ሰዎች ህይወታቸዉ ማለፉ ተሰማ

 

በዩናይትስ ስቴትስ ባለፈው ሳምንት በአስከፊ የክረምት አውሎ ንፋስ ከ90 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉ ተመዝግቧል።ሞት ከተመዘገበባቸዉ መካከል በቴነሲ ቢያንስ 25 እና በኦሪገን 16 ሰዎች ህልፈት ይፋ ተደርጓል፡፡ ከባድ የበረዶ አውሎ ነፋሱን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታዉጇል፡፡በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም በሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት ተቋርጦባቸዋል፡፡

በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የበረዶ ግግር ይቀላል ተብሎ ይጠበቃል።ሲቢኤስ ቴሌቪዥን ባገኘው መረጃ መሰረት ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ በአጠቃላይ 92 ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ የሞት አደጋዎች በመላ ሀገሪቱ ተመዝግበዋል።በቴነሲ እና በኦሪገን የሟቾች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም በሚሲሲፒ፣ ኢሊኖይ፣ ፔንስልቬንያ፣ ዋሽንግተን፣ ኬንታኪ፣ ዊስኮንሲን፣ ኒው ዮርክ፣ ኒው ጀርሲ እና ሌሎችም ከተሞች ላይ የሰዎች ህልፈት ተመዝግቧል።

ባለፈው ረቡዕ በፖርትላንድ ኦሪገን ውስጥ በአንድ ክስተት፣ ኃይለኛ ንፋስ የኤሌክትሪክ መስመር ወድቆ ይጓዙበት የነበረውን ተሽከርካሪ በመምታቱ ሶስት ሰዎች በኤሌክትሪክ አደጋ ህይወታቸዉ አልፏል። በተሽከርካሪው ውስጥ የነበረ ህፃን ከሞት ተርፏል።በሚሲሲፒ የአየር ሁኔታዉን ተከትሎ ባለሥልጣናቱ አሽከርካሪዎች “አስፈላጊ ከሆነ ብቻ እንዲያሽከረክሩ” ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡በሚሲሲፒ የሚገኙ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች ከክረምት እረፍት የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲዘገይ አድርገዋል፡፡

በክረምቱ የአየር ጠባይ ምክንያት በአሜሪካ የተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል በአብዛኛው ወደነበረበት የተመለሰ ቢሆንም፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ያለ ኃይል አቅርቦት ይቆያሉ፡፡እስከ እሑድ ምሽት ድረስ በኦሪገን 45ሺ ሰዎች ኃይል አጥተው ነበር። በፔንስልቬንያ፣ ካሊፎርኒያ፣ ኒው ሜክሲኮ እና ኢንዲያና ተጨማሪ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ተዘግቧል።

የብሔራዊ የአየር ሁኔታ አገልግሎት በዛሬዉ እለት ሰኞ ለአርካንሳስ እና ኦክላሆማ ከፍተኛ የበረዶ አውሎ ንፋስ ሊኖር ይችላል ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *