👉 በ24 ሰዓታት ውስጥ 178 ፍልስጥኤማውያን ተገድለዋል
በሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስራኤል ባካሄደችው ጥቃት እስከአሁን በጋዛ ሰርጥ ከ25,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ብቻ 178 ሰዎች መገደላቸው የተገለፀ ሲሆን ይህም እስካሁን በጦርነቱ በአንድ ቀን ከተገደሉት ሰዎች በከፍተኛ ከተመዘገቡት መካካል አንዱ ያደርገዋል።
ጦርነቱ በቀጠለበት ወቅት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የፍልስጤም አገር መፍጠርን በድጋሚ እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል። ዋይት ሀውስ ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል የሁለት ሀገር መፍትሄን በተመለከተ “ነገሮችን በተለየ መንገድ በግልፅ ያዩታል” ብሏል። የእስራኤል የአየር እና የምድር ዘመቻ በአሁኑ ጊዜ በደቡባዊ ጋዛ ላይ ያተኮረ ሲሆን ወታደሮቹ የሐማስ ከፍተኛ አዛዦችን በካን ዮኒስ ከተማ ውስጥ እንደሚገኙ በማስታወቅ ማጥቃቱን ቀጥሏል።
የእስራኤል መከላከያ ሃይል 830 ሜትር ርዝመት ያለው ዋሻ ማግኘቱን ገልጿል።የእስራኤል ወታደሮችም በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል እንደገና ጥቃት ገጥሟቸውል። የእስራኤል ወታደሮችን እና ታንኮችን ወደ ደቡብ ሲያንቀሳቅስ ሃማስ በጃባሊያ ከተማ ዙሪያ ያለውን ክፍት ቦታ ዳግም መቆጣጠሩ ተነግሯል። ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ከሦስት ወራት በላይ ቢያስቆጥርም ብሎም የእስራኤል ሠራዊት ከሃማስ አቅም እጅግ የላቀ ቢሆንም አሁንም በጋዛ ላይ ከፍተኛ ውጊያ እየገጠማቸው ይገኛል።
የአሜሪካ የስለላ ኤጀንሲዎች የእስራኤል ጦር ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆኑ የሃማስ ተዋጊዎችን እንደገደለ ይገምታሉ፣ይህም ኔታንያሁ የታጠቀውን ቡድን “ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት” ከገለፁት አላማ እጅግ ያነሰ ነው። ሚስጥራዊው ዘገባው ሃማስ አሁንም በእስራኤል ወታደሮች ላይ ለወራት ትግል ለማድረግ በቂ ጥይቶች እንዳሉት ተነግሯል።ይህም እስራኤል የተራዘመ ጦርነት እንደሚጠብቃት ማሳያ ሆኗል።
በስምኦን ደረጄ