👉 በጋዛ ሰርጥ ከ26 ሺ በላይ ፍልስጥኤማውያን ተገድለዋል
የሃማስ እስራኤል ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በእስራኤል ጦር በተወሰደ እርምጃ ቢያንስ 26 ሺ 083 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 64 ሺ 4 መቶ 87 ሰዎች ቆስለዋል።
የሀማስ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ቢያንስ 183 ሰዎች መገደላቸውንና 377 ሰዎች መቁሰላቸውን በሪፖርቱ አመላክቷል።የእስራኤል ጦር በበኩሉ በጋዛ ሰርጥ በኩል ያሉ አካባቢዎችን በየብስ፣ በአየር እና በባህር ላይ ማጥቃት እንደሚቀጥል አረጋግጧል። የአየር ኃይሉ የፍልስጤም ተዋጊዎች ንብረት የሆኑትን የዘመቻ ማዕከላትን፣ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ስፍራዎችን፣ የመመልከቻ ቦታዎችን እና የፀረ ታንክ ኬላ ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ገልጿል።
የባህር ሃይሉ በባህር ዳርቻው ላይ በርካታ ኢላማዎችን መምታቱን ተናግሯል። የወታደራዊው የአረብ ሚዲያ ቃል አቀባይ አቪቻይ አድራይ በደቡብ ካን ዮኒስ ከባድ ውጊያ መቀጠሉን አረጋግጠዋል። ነገር ግን እስራኤላውያን በአካባቢው በሚገኙ ሆስፒታሎች እና መጠለያዎች ላይ እየደረሰ ስላለው ጥቃት ምንም የተናገሩት የለም። ይህም በርካታ ፍልስጤማውያንን በድጋሚ ከግዛቱ ሳይወጡ ነገር ግን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አስገድዷቸዋል።
በሌላ በኩል የእስራኤል አየር መንገድ ኤል አል በቴል አቪቭ እና በደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ ከተማ የሚያደርገውን የቀጥታ በረራ ሊሰርዝ መሆኑን የእስራኤሉ የዜና ወኪል ቻናል 12 ዘግቧል። በሁለቱ ከተሞች መካከል የነበረው የኤል አል በረራ ከወርሃ ሚያዚያ 1 ጀምሮ ይሰረዛል።
አየር መንገዱ ይህንን እርምጃ የወሰደው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት ባለበት ሁኔታ የደንበኞች ፍላጎት መቀነስ ተከትሎ ነው።ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅማለች ስትል ለአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ክስ ካቀረበች በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል።
የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ዳኞች እስራኤል በጋዛ ውስጥ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንድታቆም የሚያስገድድ ትእዛዝ ለመስጠት እና ከሌሎች “የአደጋ ጊዜ እርምጃዎች” ጋር በተያያዘ በዛሬ እለት ውሳኔ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል።
በስምኦን ደረጄ



