የዓለማችን አምስቱ ቱጃሮች ከ2020 ወዲህ ሀብታቸው በእጥፍ መጨመሩ በዳቮስ፣ ስዊዘርላንድ በተካሄደው አመታዊ ስብሰባ ላይ ኦክስፋም የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት አስታውቋል።
አምስቱ ሰዎች ባለፉት አራት ዓመታት በሰዓት 14 ሚሊዮን ዶላር ሀብታቸውን ያሳደጉ ሲሆን በድምሩ 869 ቢሊዮን ዶላር ግምት ሀብይ እንዳላቸው ኦክስፋም በዛሬው ዕለት ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል።አምስቱ ከፍተኛ ትርፍ በትርፍ ሆነዋል የተባሉት ባለሀብቶች የኤልቪኤምኤች ኃላፊ በርናርድ አርኖልት፣ የአማዞን ባለቤት ጄፍ ቤዞስ፣ ኢንቨስተሩ ዋረን ቡፌት፣ የኦራክል መስራች ላሪ ኤሊሰን እና የቴስላ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢሎን ማስክ ናቸው።
ምንም እንኳን የአምስቱ ቢሊየኖሮች ኃብት በእጥፍ ቢጨምር 5 ቢሊዮን የዓለም ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ድህነት ውስጥ ገብተዋል ሲል ኦክስፋም ተናግሯል። ቢሊየነሮች እ.ኤ.አ. በ2020 ከነበራቸው ሀብት የ3.3 ትሪሊየን ዶላር ብልጫ ያለው ሀብት አከማችተዋል።
እነዚሁ አምስቱ ቢሊየነሮች ከ10ሩ የአለም ታላላቅ ኩባንያዎች 7ቱን እንደሚመሩ በለንደን መቀመጫውን ያደረገው የበጎ አድራጎት ድርጅት ገልጿል።አሁን ያለው አዝማሚያ በዚሁ ከቀጠለ አለም በአስር አመታት ውስጥ የመጀመሪያ ትሪሊዮኔር ባለቤት ትሆናለች ነገር ግን ድህነት ለ229 አመታት አይጠፋም ሲል ይህው የፀረ ድህነት ቡድኑ ኦክስፋም ገልጿል።
ኦክስፋም መንግስታት የዋና ስራ አስፈፃሚዎችን ክፍያ መቆጠብ ፣የግል ሞኖፖሊ ማዳከም እና የሃብት ግብር ማስተዋወቅ አለባቸው ሲል ምክረ ሀሳብ ሰንዝሯል።በ1970ዎቹ በጀርመን መሐንዲስ እና ኢኮኖሚስት ክላውስ ሽዋብ “የባለድርሻ አካላት ካፒታሊዝምን” ከፍ ለማድረግ የተጀመረው ዓመታዊ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም (WEF) ከመከፈቱ በፊት ስለ እኩልነት አመታዊ ሪፖርቱን ኦክስፋም ያወጣል።
በስምኦን ደረጄ

