በምስራቅ ቦረና ዞን መደወላቡ ወረዳ መደሃሊቦ ቀበሌ በፍቺ የተለያትን የቀድሞ ሚስቱን በስለት ወግቶ የገደለው ተከሳሽ በእስራት መቀጣቱ ተገልጿል፡፡
ተከሳሽ አብዱራህማን ሀሰን የሁለት ልጆቹ እናት እና ባለቤቱ የነበረቸው የቀድሞ ሚስቱ ላይ ባደረበት የቅናት ስሜት ተገፋፍቶ በስለት ዘግናኝ በሆነ መልኩ ገድሎ ለማምለጥ የሞከረ መሆኑን የምስራቅ ቦረና ዞን ፖሊስ መምሪያ ሴቶች እና ህጻናት ጉዳዮች ጽ/ ቤት ወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ሶሶቤ ደጀኔ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡
ተከሳሹ ለይላ መሃመድ የተባለች ሴት ጋር ተጋብተው ሁለት ልጆችን ማፍራት ችለው የነበረ ቢሆንም ባለቤቷ ባደረበት የቅናት ስሜት መግባባት ባለመቻላቸው ልጆቿን ይዛ ወደ ቤተሰቦቿ ሄዳ የነበረ መሆኑም ተነግሯል፡፡ በዚህም ደስተኛ አለመሆኑን እና ሚስትም በፍርድ ቤት ፍቺ እንዲጸድቅ አድርጋ የፍቺ ሂደት እንዳጠናቀቁ ተረጋግጧል፡፡
ነገረ ግን በፍቺው ደስተኛ ያልነበረው አብዱራህማን ሀሰን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዋን መከታተልን ስራዉ ያደርጋል፡፡ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት ላይ ከሱቅ እቃ ገዝታ ስትመለስ እቤት ውስጥ ማንም አለመኖሩን አረጋግጦ በአጥር ዘሎ በመግባት በግል ተበዳይ የቤተሰብ ቤት ዉስጥ ይደበቃል ፡፡
ከዛም ሟች ለይላ ወደ መጸዳጃ ቤት ስታመራ ከተደበቀበት ወጥቶ በያዘው ስለታም ቢላዋ አንገቷን ወግቶ ህይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል። ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ለመሰወር የሞከረ ቢሆንም በሞተር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
ድርጊቱን ሲከታተል የቆየው ፖሊስ ተከሳሽ የ35 ዓመቷን ተበዳይ እና የሁለት ልጆቹን እናት መግደሉን በህክምና እና በሰው ማስረጃ ያሟላ በመሆኑ የምስራቅ ቦረና ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 28 ቀን 2016 ዓ. በዋለው ችሎት በተከሳሽ አብዱራህማን ሃሰን ላይ በ23 ዓመት እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ማሳለፉን ረዳት ኢንስፔክተር ሶሶቤ ደጀኔ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጨምረዉ ተናግረዋል ።
በኤደን ሽመልስ

2 Responses