photo_2024-01-25_16-24-02

ጥር 16፤2016 – ሮፍናን “ኖር” እና “ሀራምቤ” የተሰኙ ሁለት የሙዚቃ አልበሞችን ሊለቅ ነዉ

 

የኤሌክሮኒክ ዳንስ ሚዩዚክ (EDM) የሙዚቃ ባለሙያ የሆነዉ ሮፍናን “ኖር” እና “ሀራምቤ” የተሰኙ ሁለት አልበሞችን ሊለቅ መሆኑን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል።

ሙዚቀኛዉ ሶስት እና ስድስት ከተሰኙ “የኔ ትዉልድ” እና “ነፀብራቅ” ከተሰኙ ሁለት አልበሞቹ በኋላ ዘጠኝ በተሰኘዉ አልበም ዉስጥ “ሀራምቤ” እና “ኖር “የተሰኘዉ አልበም በይፋ ይለቀቃል ተብሏል። ባልተለመደ መልኩም ሁለት አልበሞችን ሙዚቀኛዉ ይለቅቃል።

በአልበሙ ከሬጌ ሙዚቀኛዉ ክሮኒንስ ጋር በመጣመር የሰራዉ ሀራምቤ የሰተኘ ሙዚቃ እንዳለ ሮፍናን ተናግሯል። አልበሙ ከሶስት ሳምንታት በኋላ እንደሚለቀቅ ብስራት ሰምቷል። በድምሩ 21 ሙዚቃዎችን የያዘ ሲሆን በዛሬዉ እለትም አንድ ሙዚቃ ቪዲዮ እንደሚለቅ አስታዉቋል።

ሀይሌ ሩት ፣ ሸዊት መዝገበዉ ፣ ልጅ ተመስገን እና ሌሎች ወጣት ሙዚቀኞች በስራዉ ተሳትፈዉበታል። አልበሙ ሀመርኛ ፣ ሲዳምኛ ፣ ዶርዝኛ ፣ ትግርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተካተቱበት ነዉ ብሏል።

በበረከት ሞገስ

Screenshot 2024-01-25 164705

ጥር 16፤2016 – አንድን ግለሰብ  ከመኪና ውስጥ ገፍትረው በመጣል የማታለል ወንጀል ለመፈፀም የሞከሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ

 

በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B48631 አ.አ በሆነ ተሽከርካሪ ወንጀል ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው፡፡ ግለሰቦቹ  በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው 6 ኪሎ ዩኒቪርሲቲ አንደኛ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በፈፀሙት ወንጀል እንደተያዙ በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የመነን አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ሃላፊ ኢንስፔክተር ታዲዮስ ወ/አረጋይ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ባንኮች ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ እና ይህንን ወንጀል ከመፈፀማቸው በፊት በሌሎች ስድስት ባንኮች ውስጥ በመግባት ሞክረው አልተሳካለቸውም። በስተመጨረሻ ከሁለቱ አንደኛው ተጠርጣሪ 5 ኪሎ አካባቢ በሚገኝ የአንድ ባንክ ቅርንጫፍ ውስጥ በመግባት ከኤንጂኦ እንደመጣ በመግለፅ እና በድርጅቱ ስም የባንክ አካውንት ለመክፈት የፈለገ በማስመሰል  ከባንኩ ስራ አስኪያጅ ጋር ይግባባል፡፡

ስራ አስኪያጁም አካውንት ለመክፈት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ይነግሩታል። ተጠርጣሪውም ፎቶን ጨምሮ ሌሎች መስፈርቶችን አሟልቶ በድጋሚ እንደሚመለስ ከገለፀላቸው በኋላ ድርጅታችን በቅናሽ ዋጋ የሚሸጣቸው ባለ 53 ኢንች ሁለት ቴሌቪዥኖች ስላሉ የሚገዙ ከሆነ ውሰዱ ብሎ የባንኩን ስራ አስኪያጅ ይጠይቃቸዋል፡፡

ስራ አስኪያጁም ቴሌቪዥኑን መግዛት እንደሚፈልጉ፣ ነገር ግን ለጊዜው በእጃቸው ያለው 3 ሺህ ብር ላይ 12 ሺህ ብር ከሌላ ሰው ተበድረው በድምሩ 15 ሺህ ብር መስጠት እንደሚችሉ ይነግሩታል፡፡ ተጠርጣሪውም ቀሪውን ገንዘብ ሌላ ጊዜ እንደሚወስድ እና  ቴሌቪዥኑን ለመረከብ ሌላ ሰው እንዲልኩ ስራ አስኪያጁን ካግባባ በኋላ ስራ አስኪያጁም 15ሺህ ብሩን አስይዘው ቴሌቪዥኑን የሚያመጣ ሰው አብረው መላካቸውን ኢንስፔክተር ታዲዮስ አስረድተዋል፡፡

ተጠርጣሪው በባንኩ ማናጀር የተላከውን ሰው በር ላይ ቆሞ ይጠብቀው በነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B48631 አ.አ በሆነ የወንጀል ግብራበሩ በሚያሽከረክረው መኪና ውስጥ እንዲገባ አድርጎ ጥቂት ከተጓዙ በኋላ 6 ኪሎ ዩኒቪርሲቲ አንደኛ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ 15ሺህ ብሩን ስጠኝ ብሎ ከተቀበለው በኋላ ሾፌሩ የመኪናውን ፍጥነት ሲያቀዘቅዝለት በሩን በመክፈት ቴሌቪዥኑን እንዲያመጣ የተላከውን ሰው ገፍትሮ በመጣል በፍጥነት ለማምለጥ ሞክረዋል፡፡

ነገር ግን በወቅቱ በተሽከርካሪ በመንቀሳቀስ የወንጀል መከላከል ስራ ሲሰሩ የነበሩ የፖሊስ አባላት በደረሳቸው ጥቆማ ወንጀሉን ፈፅሟል የተባለውን ግለሰብ ከነ ግብራበሩ እና ሲጠቀሙበት ከነበረው መኪና ጋር ተከታትለው በቁጥጥር ስር ሊያውሏቸው መቻላቸውን የምርመራ ሃላፊው ገልፀዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተያዙበት ወቅት ሶስት ሞባይል ስልኮች እጃቸው ላይ እንደተገኘ እና ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛን።

ምርመራ እየተካሄደባቸው ከሚገኙት ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ጥቆማ እና መረጃ አለኝ የሚል ማንኛውም ሰው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ  መነን አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በአካል ቀርቦ ማነጋገር እንደሚችል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ጥር 16፤2016 – ኬንያ የመኪናና የስልክ ባትሪዎችን ለመስራት የሚያስችለዉን የኮልታን ማዕድን ክምችትን አገኘች

 

ኬንያ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቃሚ ማዕድን የሆነዉን ኮልታን ማግኘቷን የሀገሪቱ የማዕድን ሚኒስትሩ አስታዉቀዋል፡፡

ብርቅዬው ማዕድን የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪዎች፣ ሞባይል ስልኮች እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ለማምረት ያገለግላል።ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዓለም የኮልታን ክምችት የያዘች ሀገር እንደሆነች ይታወቃል፡፡

ይህ ሀብት ግን ለኮንጎ ከበረከትይልቅ እርግማን ሆኖባት ለአስርት አመታት ማዕድኑ በሚገኝበት በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የትጥቅ ግጭት እንዲባባስ አድርጓል።በኬንያ የሚገኙት የኮልታን ክምችቶች ምን ያህል እንደሆኑ ግን ግልጽ አይደለም::የማዕድን ባለስልጣናት ቀደም ሲል ኬንያ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ማዕድን ሊኖራት እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዉ ነበር፡፡

የኬንያ የማዕድን፣ የሰማያዊ ኢኮኖሚ እና የባህር ጉዳዮች ሚኒስትር ሳሊም ምቩርያ እንደተናገሩት ኬንያ የኮልታን ክምችት እንዳላት “አሁን ይፋ ሆኗል” ብለዋል።የማእድኑ ሀብቱ በሀገሪቱ በስድስት ክልሎች ውስጥ ተገኝቷል::ነገር ግን የክምችቱን መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

የማዕድኑ ክምችት ካላቸው ስድስት አውራጃዎች አንዱ የሆነው በምስራቅ ኬንያ የሚገኘው የኢምቡ ክልል ነዋሪዎች መሬታቸውን ከመሸጥ እንዲቆጠቡ ምክር ተለግሷቸዋል፡፡የክልሉ የፓርላማ አባል የሆኑት ነባርት ሙሪዩኪ ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት “ውድ የሆነ ማዕድን ተገኝቷል እና ጥቅም ለማግኘት ከፈለጋችሁ መሬታችሁን አትሽጡ” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ምቩርያ እንዳሉት ግኝቱ ተጨማሪ የስራ እድል ይፈጥራል እንዲሁም የየኬንያን ማዕድን ኢንዱስትሪ ያሰፋል ብለዋል።

የማዕድን ቁፋሮ ከኬንያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ከ1 በመቶ በታች ቢሆንም እስከ 10 በመቶ ለማዋጣት የሚያስችል አቅም እንዳለው የኬንያ ብሄራዊ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ገልጿል።ኮልታን ብዙውን ጊዜ በብረታ ብረት ታንታለም ውስጥ ይጣራል ፡፡ከዚያም የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ለማምረት ያገለግላል፡፡የኮልታን ዋጋ ምን በያዘዉ ታንታለም መሰረት ይወሰናል፡ ነገርግን በአማካይ አንድ ኪሎ ግራም  ማዕድኑ 48 ዶላር ያስገኛል ሲል ፎርብስ ዘግቧል።

ተንታኞች እንደሚናገሩት ዓለም አቀፉ የኮልታን ፍላጎት በፍጥነት እያደገ ሲሆን በምስራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ለተፈጠረው ግጭት መንስኤ ከሆኑት መካከል አንዱ ተቀናቃኝ ሚሊሻዎች ኮልታን እና ሌሎች ጠቃሚ ማዕድናትን የሚያመርቱ ስፍራዎችን ለመቆጣጠር በመፈለጋቸዉ የተነሳ ነው፡፡ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከጎረቤቷ ሩዋንዳ ጋር በመሆን በዓለማችን ከፍተኛ የኮልታን አቅራቢ ሀገራት የሚለዉን ስም ይዘዋል፡፡

በስምኦን ደረጄ

ጥር 16፤2016 – የጤና ባለሙያዋን በቢላዋ በመዉጋት ወርቅና ሞባይል የዘረፉ ሁለት ተጠርጠሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

 

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ቡለን ወረዳ 01 ቀበሌ ውስጥ መሆኑን የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ኮማንደር ብራሃኑ እጀታ ለብስራት ቴሌቬዥንና ራዲዮ ተናግረዋል።

የግል ተበዳይ የሆነችውን ወ/ሮ ሚሚ ፈረደ የቡለን መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ባለሙያ ስትሆን ጥር 06 ቀን 2016 ዓ/ም  ከቀኑ 10:00 አከባቢ  ከሆስፒታል ወደ ቤት በመሄደ ላይ እያለች አቶ  ፍቃዱ መለሰ እና አቶ ሐይማኖት ደሴ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ወ/ሮ ሚሚ ፈረደን በቢላዋ ወግተዉ ጉዳት በማድረስ አንድ ጥቅል ወርቅ ወደ ብር ሲተመን በአሁኑ ዋጋ 90,000 ብር ንብረት እና አንድ ስማርት ስልክ በድምሩ 106,000 ብር ንብረት ዘርፈዉ  ይሰወራሉ።

ማህበረሰቡ ለፖሊስ በሰጠውዉ ጥቆማ  ክትትል በማድረግ ተጠርጣሪዎቹ ከቡለን ወደ ቻግኒ ለመሸሽ ሲሞክሩ ከሙሉ ንብረቱ ጋር በቁጥጥር ስራ መዋላቸዉን ኮማንደር ብራሃኑ እጀታ ለብስራት ቴሌቬዥንና ራዲዮ ገልፀዋል ።

ኮማንደር ብርሃኑ እጀታ አከለዉም ተጠርጣሪዎች በተመሳሳይ አርብ  ጥር 3 ቀን 2016 ዓ/ም ከአንድ የአከባቢው ወጣት በካራ በማስፈራራት 2000 ብር እና አንድ ስፖርት ሞባይል ወደ ብር ሲተመን 15000 ብር እንደዘረፉ ገልፀዋል።

በበቀለ ጌታሁን

ጥር 16፤2016 – በአዲስ አበባ ከተማ የደም ግፊት በሽታ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተነገረ

 

👉 በከተማዋ ከአንድ መቶ ሰዎሽ 23 በሚሆኑት ላይ በደም ግፊት በሽታ እንደሚያዙ ተጠቁሟል

በአዲስ አበባ ከተማ  በደም ግፊት በሽታ እየተያዙ ያሉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታውቋል።በቢሮው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ወንድወሰን በርሄ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቪዥን እንደገለጹት በተደረገው ጥናት መሰረት እንደ ሃገር ከአንድ መቶ ሰዎች በ16ቱ ላይ በሽታው እንዳለ ያሳያል።

በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ደግሞ ከአንድ መቶ ሰዎች 23 የሚሆኑ በከፍተኛ የደም ግፊት በሽታ ይይዛሉ ፡፡የደም ግፊት በሽታ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ እየጨመረ በመምጣቱ በርካታ ዜጎች ለስነ ልቦና ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር እየዳረገ ይገኛል።

በሽታው ባህሪው ለረጅም ዓመታት ምንም አይነት ምልክትን ሳያሳይ በሰውነት ውስጥ መቆየቱ በበሽታው የመያዝና የመጠቃት እድልን ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።በተጨማሪም ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን  አለመከተል፣ አካላዊ እንቅስቃሴ አዘውትሮ አለማድረግ፣ ትምባሆ ማጨስ ፣ አልኮል መጠጥን አብዝቶ መጠጣት ፣ ጨው  እና  ስብ የበዛባቸውን ምግቦች አዘወትሮ መመገብ  ዋና ዋና የሚባሉ አጋላጭ መንስኤ እንደሆኑ አቶ ወንደሰን ጨምረው ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

ቢሮው  በ2016 በጀት ዓመት ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ  ለ560 ሺህ  ለሚሆኑ ነዋሪዎች  የደም ግፊት ልየታ እና ምርመራ ማድረግ መቻሉን ቡድን መሪው ገልጸዋል። በተደረገው ምርመራ 25 ሺህ 931 የሚሆኑ ሰዎች የደም ግፊታቸው ጨምሮ የተገኘ ሲሆን  ከእነዚህም ውስጥ 17 ሺህ 300  የሚሆኑ የህክምና አገልግሎት ክትትል መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ጤና ቢሮ  የደም ግፊትን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ተብሏል፡፡ከዚህ ቀደም በማዕከል ደረጃ ሲሰጥ የነበረውን የደም ግፊት የህክምና አገልግሎት በጤና ጣቢያዎች እንዲሰጥ እየተደረገ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን  ምርመራውም በነጻ እንዲሰጥ እየተሰራ ይገኛል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ማንኛውም እድሜው 30 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ለደም ግፊት የመጋለጥ እድል ሊኖራቸው ይችላል። የደም ግፊት ዋና ዋና ምልክቶች ራስ ምታት፣ ትንፋሽ ማጠር፣ ነስር፣ የድካም ስሜት፣ የደረት ህመም፣ የእይታ መድከም፣ በሽንት ውስጥ ደም መታየት መሆናቸውን የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የደም ግፊትን በመለካት፣ የደም ግፊት ህመም እንዳለ ወይም አለመኖሩን ማወቅ ተገቢ እንደሆነ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

በቅድስት ደጀኔ

photo_2024-01-24_17-49-18

ጥር 15፤2016 – የሩሲያ ወታደራዊ ማመላለሻ አውሮፕላን በቤልጎሮድ ተከስክሶ ከ70 በላይ ሰዎች ህይወት አለፈ

 

የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴርን እንዳስታወቀዉ የሩሲያ ኢሊዩሺን ኢል-76 ወታደራዊ ማመላለሻ አውሮፕላን በሩሲያ ቤልጎሮድ ክልል ተከስክሷል።

በአውሮፕላኑ ውስጥ 65 የዩክሬን የጦር እስረኞች ከስድስት የበረራ ሰራተኞች እና ሌሎች ሶስት ተሳፋሪዎች ጋር እንደነበሩ ሚኒስቴሩ አስታዉቋል፡፡ኤ.ፒ.ኤ እንደዘገበው አደጋው የተከሰተው እሮብ ከረፋዱ 5 ሰዓት አካባቢ ነው። በሕይወት የተረፈ ሰው እንደሌለ ተገልጿል፡፡

ባለሥልጣናቱ የአደጋውን መንስኤ በማጣራት ላይ ሲሆኑ ልዩ ወታደራዊ ኮሚሽን ወደ አደጋው ቦታ መላኩን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።ሪያ ኖቮስቲ የተሰኘ የዜና ወኪል የክልሉ ገዥ ቪያቼስላቭ ግላድኮቭ ስለ አደጋዉ ማረጋገጫ ቢሰጡም ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የሩሲያ ፕሬዚዳንታዊ ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ እንደተናገሩት ክሬምሊን ስለ አደጋው እንደሚያዉቅ ቢገልጹም ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ለመግባት ፈቃደኛ አልሆኑም።

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-01-23_08-38-13

ጥር 15፤2016 – የአንጋፋዉ ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ(ሊብሮ) ስርዓት ቀብር ተፈጸመ

 

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ በተጫዋችነት፣ ጋዜጠኝነት እና በመፅሐፍ ደራሲነት ለረጅም ዓመታት ያገለገለው ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ባደረበት ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም ንጋት ላይ ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል።

ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) በእግር ኳስ ተጫዋችነት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ጨምሮ ለሌሎች ክለቦችም ተጫውቷል። ከተጫዋችነት ከተገለለ በኋላ ከ30 ዓመታት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት አሳልፏል፡፡በበርካቶች ዘንድ”ተንቀሳቃሹ ቤተ መፅሐፍት”የሚል ቅፅል ስም የተሰጠው ገነነ መኩርያ ኢህአፓና ስፖርት”1፣ 2፣ 3፣ ሊብሮ፣ እና ፍትሃዊ የጠጅ ክፍፍል የሚሉትን ጨምሮ ስምንት ያህል መፅሐፍትንም ለንባብ አብቅቷል።

ገነነ መኩርያ ሊብሮ” የተሰኘ ጋዜጣንም ለረጅም ዓመታት ለአንባቢው አድርሷል። በተጨማሪም በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው በተወዳጁ  ብስራት ኤፍ ኤም 101.1 “መሴ ሪዞርት” እና ሌሎች ዝግጅቶች ላይ ታሪክና ስፖርትን አዋህዶ ሲያቀርብ ቆይቷል። ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ለእግር ኳሱ ላበረከተው የላቀ አስተዋፅኦም በአዲስ አበባ በተሰናዳው የካፍ ኮንግረስ ላይ የረጅም ዘመን አግልግሎት ሜዳይ ተበርክቶለታል።

ካፍ በ2009 ዓ.ም የ60 ዓመት ጎንደል ኦፍ ሜሪት የሸለመው ሲሆን፤ ስድስት ጋዜጠኞች ብቻ ያገኙትን ሽልማት በመውሰድ ገነነ ከምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው እንደሆነም ይነገራል። ጋዜጠኛው መጋቢት 5 ቀን 1957 ዓ.ም በይርጋለም ከተማ እንደተወለደ ሲሆን፤ እድገቱ ደግሞ በሻሸመኔ ከተማ እንደሆነ የህይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ስርዓተ ቀብሩ በዛሬዉ እለት ጥር 15 ቀን በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ቤተሰብ ፣ወዳጅ ዘመድና የሙያ ዘጋሮቹና አድናቂዎቹ በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡

ብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን በአንጋፋዉ ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ(ሊብሮ) የተሰማዉን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ መጽናናትን ይመኛል፡፡

ጥር 15፤2016 – ዶናልድ ትራምፕ ድላቸውን ተከትሎ ባይደን ሁለት ዓረፍተ ነገር እንኳን ማያያዝ አይችሉም ሲሉ ተናገሩ

 

👉 ተሸናፊዋ ሃሌይ ዲሞክራቶች ከእኔ ይልቅ ትራምፕን ይፋልጋሉ ምክንያቱም ከእድሜያቸው ጋር ተያይዞ የአእምሮ ብቃታቸው ቀንሷል ብላለች

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያገኙት ግዙፍ ድል በህዳር ወር የፓርቲው ፕሬዚዳንታዊ እጩ ለመሆን የሚያስችላቸው እንደሆነ ተነግሯል። የውድድሩ የመጨረሻ ተቀናቃኛቸው የሆነችው ኒኪ ሃሌይ በቀሩ ሂደቶች ለመታገል ትራምፕ ቃል ገብተዋል።ይህ ውድድር ገና አልተጠናቀቀም ፤ እሷም ጠንካራ ተፎካካሪ ነች ብለዋል።

አስቀድሞ በነበረው የምረጡኝ ዘመቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ትራምፕ ለጋዜጠኞች ኒኪ ሃሌይ በምርጫው ፉክክሩ ላይ ብትቆይ ግድ የለኝም “የፈለገችውን እንድታደርግ መፍቀድ” ይኖርብናል በማለት ተናግረዋል። ዶናልድ ትራምፕ ከድላቸው በኃላ ባደረጉት ንግግር የዴሞክራቲክ ተቀናቃኛቸውን ጆ ባይደንን በመተቸት በስልጣን ዘመናቸው በጣም መጥፎ ከሚባሉት 10 ፕሬዚዳንቶች ጋር ሲጣመሩ በጣም ደካማው ባይደን ናቸው ሲሉ ተችተዋል።

የ77 ዓመቱ ትራምፕ የ81 ዓመቱን አዛውንት ተፎካካሪያቸውን ባይደንን ሁለት ዓረፍተ ነገሮችን አንድ ላይ ማያያዝ እንኳን አይችሉ ሲሉ ተሳልቀዋል።ትራምፕ አክለው እኛ ካላሸነፍን ይህች ሀገር ያበቃላታል ሲሉ ተደምጠዋል። የቀድሞው ፕሬዝደንት ከኒኪ ሃሌይ ጋር የሪፐብሊካን ፕሬዝደንት ለመሆን በተለይም በኒኪ ሃሌይ የትውልድ ስፍራ ደቡብ ካሮላይና ውስጥ ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።

ኒክ ሀይሌ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ በትራምፕ መሸነፏን ተከትሎ ባስተላለፈችው መልዕክት ተቀናቃኛቸውን እንኳን ደስ አላችሁ ብላለች። ነገር ግን ሪፐብሊካኖች ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ለመለየት ጊዜው አሁን ነው በማለት ተናግራለች። በፖለቲካ ውስጥ በጣም የተደበቀው ሚስጥር ልንገራችሁ ዲሞክራቶች ከእኔ ይልቅ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር መወዳደር ይፈልጋሉ ስትል ለተሰበሰበው ህዝብ ተናግራለች።

በሀገሪቱ ውስጥ ጆ ባይደን የሚያሸንፈው ብቸኛው ሪፐብሊካን ትራምፕን መሆኑን ያውቃሉ ያለችው ሃሌይ ከትራምፕ የበለጠ ተመራጭ እኔ ነኝ በማለት ተናግራለች። ትራምፕ በሁከትና ብጥብጥ የሚታወቁ ናቸው ያከለችው ሃሌይ የአእምሮ ብቃታቸው ከእድሜያቸው መጨመር ጋር ተያይዞ እየቀነሰ መምጣቱን አንስታለች። የ52 ዓመቷ ሃሌይ “አብዛኛዎቹ አሜሪካውያን በባይደን እና በትራምፕ መካከል የድጋሚ ውድድር አይፈልጉም” በማለት ገልፃለች።

በበረከት ሞገስ

ጥር 15፤2016 – የአምስት ዓመቷ ህፃን ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

 

በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጀሬ ወረዳ ቱሉ ኤጀሬ ቀበሌ ውስጥ ተከሳሽ ታደሰ ሚልኬሳ የተባለ ግለሰብ ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ወንጀሉን ፈፅሟል።

በእለቱ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ የ5 ዓመቷን ህፃን ልጅ በተከራየበት ቤት ውስጥ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደፈፀመባት በማስረጃ መረጋገጡን የምዕራብ ሸዋ ዞን ፖሊስ ኮሙኒኬሽን  ፅ/ቤት  አስታውቋል፡፡

የ5 ዓመቷን ልጅ ላይ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ካደረሰባት በኃላ በከፍተኛ ህመም ስትሰቃይ ቆይታለች። ወላጆቿ የደረሰባትን ሲጠይቋት የተፈፀመባትን ድርጊት በመናገሯ ድርጊቱ ፖሊስ ጆሮ በመድረሱ ተከሳሹ በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉን ብስራት ሬድዮና ቴሌቭዥን ከኮሙኒኬሽኑ ቢሮ ያገኘው መረጃ ያመላክታል ፡፡

የአስገድዶ መደፈር ጥቃት የደረሰባትም የ5 ዓመቷ ልጅ የህክምና ምርመራ ከተደረገላት በኃላ በተጠርጣሪው ላይ ፖሊስ የወንጀል መዝገብ በማጣራት በሰው እና ህክምን ማስረጃ በማጠናከር የምርመራ መዝገቡን ለአቃቢ ህግ ልኳል፡፡

አቃቢ ህግም ከፖሊስ የተላከለትን መዝገብ ተመልክቶ ክስ መስርቷል። የቀረበለትን ክስ ሲመለከት የነበረው የምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሽ ታደሰ ሚልኬሳ በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ እንደተወሰነበት የምዕራብ ሸዋ ዞን ፖሊስ ኮምኒኬሽን ፅ/ቤት አስታውቋል።

photo_2024-01-23_15-18-32

አሜሪካዊው ሙዚቀኛ በእኩል ሰዓት ከአምስት ሴቶች የልጆች አባት ለመሆኑ መቃረቡ ተከትሎ ቤቢ ሻወር የተሰኘው ዝግጅት በጋራ አዘጋጀ

 

በአሜሩካ አንድ የኒውዮርክ ከተማ ነዋሪ የሆነ ሙዚቀኛ አምስት የተለያዩ ሴቶችን በተመሳሳይ ጊዜ የልጆች አባት ሊያደርጉት መሆኑን በማስመልከት ከሁሉም ጋር በጋራ ቤቢ ሻወር የተሰኘውን ዝግጅት በማዘጋጀቱ ውዝግብ አስነስቷል።

የ22 አመቱ የኒውዮርክ ከተማ ሙዚቀኛ ዜዲ ዊል የሚባል ሲሆን የበርካቶችን ትኩረት የሳበውን አምስት ወጣት ሴቶችን ነፍሰ ጡር እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ በጋራ አንድ ዝግጅት ላይ እንዲሳተፉ ማሳምኑ አነጋጋሪ አድርጎታል። ይህ አስገራሚ ይፋ ያደረገችው ከሴቶቹ መካከል አንዷ የሆነችው ሊዚ አሽሌይ ናት። የ29 ዓመቷ ሴት የቤቢ ሻወር ግብዣን የጥሪ ካርድ በማህበራዊ ሚዲ ላይ ይፋ ስታደርግ የዜዲ ዊል እና የአምስቱ ሴቶችን ፎቶ ያሳያል።

የግብዣው ወረቀት ላይ ትንሹ ዜዲ ዊልስ ከአንድ እስከ 5 እንኳን ደህና መጣህ የሚል ነበር። ሊዚ ባጋራችው ቪዲዮ ላይ አምስቱ ሴቶች ለሕፃናቱ ጥቅም ሲሉ እርስ በእርሳቸው ለመከባበር እና ለመጠባበቅ ቃል ገብተዋል።በጋራ ባስተላለፉት መልዕክት “ቆንጆ ቤተሰብ እንደሆንን ተመልከቱ፤ ባለቤታችንን እንወዳለን! የልጆቻችንን ህይወት ያማረ ይሆናል መላው ቤተሰቦቻችን ይህንን ተቀብሏል ሲሉ ይፋ አድርገዋል።

ከነፍሰ ጡር ሴቶች መካከል አንዷ የሆነችው ሊዚ ያጋራችእ ቪዲዮ በስፋር ተሰራጭቷል። የተለያዩ አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን ድርጊቱን መፈፀማቻው ሳያንስ በአንድ ዝግጅት ላይ መታደማቸውን  “አሳፋሪ” ሲሉ ገልጸውታል። ኒውዮርክ ፖስት ስለ አስገራሚው ቤተሰብ የበለጠ መረጃ ለማግኘት በሰራው ዘገባ መሰረት ወጣቱ ራፐር የአምስት ልጆች አባት ለመሆን ብስለት እንዳለው ተነግሯል ሲል አስነብቧል።

ከህብረተሰቡ ግፊት ተላቀናል በሚል የሚወሰኑ ውሳኔዎች በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረጉ የፍቅር ግንኙነቶችን እያዳከሙ የቤተሰብን ትክክለኛ መገለጫን እያደበዘዙ መሆኑን በርካቶች አስተያየት ሰንዝረዋል።

በስምኦን ደረጄ