photo_2024-06-05_14-35-06

ግንቦት 28፤2016 – ወደ ሀገር ዉስጥ የሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ደረጃ መዘጋጀቱ ተነገረ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስትም አስገዳጅነት ወደ ሀገር ቤት በብዛት እየገቡ ለሚገኙት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የደረጃ መለኪያ መስፈር መዘጋጀቱን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል። በርካታ ባለሙያዎች ወደሀገር ዉስጥ የሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወኪል አልባ ናቸዉ ከሚለዉ ጀምሮ ካለ መለኪያ መስፈርት የሚገቡ መሆናቸውን ሲናገሩ ይደመጣል።

የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን የሚገቡ ተሽከርካሪዎች በምን ደረጃ ላይ መገኘት አለባቸዉ የሚለዉን የሚመዝን ደረጃ ማዘጋጀቱን የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሩ ዶ/ር አለሙ ስሜ መናገራቸውን ብስራት ሰምቷል። በተጨማሪም የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

በሌላ በኩል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሀይል መሙያ ማዕከላት የአተገባበር መመሪያ መዘጋጀቱንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የሀይል መሙያ ማዕከላትን መላዉ ኢትዮጵያን የሚሸፍን ለማድረግ የቅድመ አዋጭነት ጥናት መደረጉንም ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሀይል መሙያ ለመገንባት ለሚያቅዱ ባለሃብቶችም ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የፕሮጀክት እቅድ መዘጋጀቱንም ሚኒስትሩ ይፋ አድረወገዋል። በአሁኑ ወቅትም ለ 162 የኤሌክትሪክ መኪና አስመጪዎች ፈቃድ መሰጠቱን የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ መናገራቸውን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል።

በበረከት ሞገስ

photo_2024-06-05_14-34-17

ግንቦት 28፤2016 – ከጫት ማሳ ውስጥ ጫት እየወሰደ ይሸጥብናል በማለት የግድያ ወንጀል የፈፀመው ተከሳሽ በእስራት ተቀጣ

 

በምስራቅ ሀረርጌ ዞን በደኖ ወረዳ ዋሬ ቀበሌ ከጫት ማሳ ውስጥ ጫት እየወሰደ ይሸጥብናል በማለት የተጠረጠረን ግለሰብ ላይ የግድያ ወንጀል የፈፀመው ተከሳሽ በእስራት መቀጣቱን የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል፡፡

የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ሳሊም ሙፍቲሀል ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደገለፁት ተከሳሽ ጁነዲን ኢብራሂም የተባለው ግለሰብ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም ሌሎች ስድስት ሰዎችን በማስተባበር ነው ወንጀሉን የፈፀመው፡፡

ከጫት ማሳ ውስጥ ጫት እየወሰደ የሚሸጠው አህመድ ሹሙሚ  የተባለው ግለሰብ ነው በማለት ወደ መኖሪያው አካባቢ በመሄድ አህመድን ሹሙሚ  ከተኛበት ቀስቅሰው በመውሰድ በጥይት ተኩሰው መግደላቸው ዓቃቢ ህግ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በከፈተው የክስ መዝገብ ላይ መጥቀሱን ተናግረዋል ፡፡

አቃቢ ህግ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 5391 መሰረት በሰባት ሰዎች ላይ በግድያ ወንጀል የመሰረተው ክስን ሲከታተል የነበረ የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቢህግ ያቀረበው ማስረጃ በስድስቱ ተከሳሾች ላይ ጥፋታቸው በበቂ ሁኔታ ባለመረጋገጡ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 141 መሰረት በነፃ እንዲለቀቁ ወስኗል፡፡

አንደኛ ተከሳሽ ጁነዲን ኢብራሂም ደግሞ በአቃቢ ህግ ማስረጃ ጥፋተኛ መሆኑ በመረጋገጡ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን አቶ ሳሊም ሙፍቲሀል ጨምረው ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን  ተናግረዋል ፡፡

በምህረት ታደሰ

 

ግንቦት 27፤2016 – በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጫት የጫነ ተሽከርካሪ ተገልብር የስድስት ሰዎች ህይወት አለፈ

በምዕራብ ሀረርጌ ዞን አንጨር ወረዳ ጫት የጫነ ተሽከርካሪ በመገልበጡ የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ፖሊስ አስታውቋል።

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ፖሊስ የትራፊክ ቁጥጥር እና ደህንነት አስተባባሪ ረዳት ኢንስፔክተር ታምራት እሸቱ  ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ግንቦት 26 ቀን ለግንቦት 27 አጥቢያ  ከለሊቱ 9:30 ላይ ከሀረር ከተማ ጫት በመጫን አስር ሰዎችን አሳፍሮ ወደ አዳማ ከተማ ሲጓዝ ነበር።

የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 35111 አአ የሆነ ተሽከርካሪ 10 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ አንጨር ወረዳ ኢንጪኒ የተባለ ቦታ ሲደርስ በመገልበጡ ስድስት ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ አራት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሷል።

ህይወታቸው ያለፈው ስድስት ሰዎች ተሽከርካሪው ላይ ጫት በማውረድ ስራ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን እና አሽከርካሪውን ጨምሮ ሁለቱ ሟቾች ጋቢና ውስጥ እንደነበሩ ረዳት ኢንስፔክተር ታምራት እሸቱ ጨምረው  ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በምህረት ታደሰ

ግንቦት 27፤2016 -በኦሮሚያ ክልል በአንድ ሳምንት ውስጥ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ10 ሰዎች ህይወት አልፏል

 

በኦሮሚያ ክልል ከግንቦት 19 እስከ ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናቶች በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች የ10 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ፤ በ11 ሰዎች ላይ ከባድ እና በ1 ሰው ላይ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡

አብዛኞቹ የሞት አደጋዎች የተከሰቱት ምስራቅ ቦረና ፣ቄለም ወለጋ፣ምስራቅ አርሲ፣ጅማ፣ምስራቅ ጉጂ ዞኖች እንዲሁም ሸገር እና ቢሾፍቱ ከተማዎች የተከሰቱ መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል የትራፊክ ቁጥጥር ክፍል ባለሙያ የሆኑት ኢንስፔክተር መሰለ አበራ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

አብዛኛዎቹ አደጋዎች የተከሰቱት በቀኑ ክፍለ ጊዜ ሲሆን የሞት አደጋዎች የደረሱት በጭነት ተሽከርካሪ፣በህዝብ ማመላለሻ፣ በባለ ሦስት እግር (ባጃጅ) እና በሞተር ሳይክል የተከሰቱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የአደጋዎቹ መንስኤዎቹ ያለ መንጃ ፍቃድ ማሽከርከር፣ከፍጥነት ወሰን በላይ ማስከርከር፣ለእግረኛ ቅድሚያ አለመስጠት፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር፣ርቀትን ጠብቆ አለማሽርከር፣ ደርቦ ማለፍ ምልክቶችን አለማክበር ፣የጥንቃቄ ጉድለት መሆኑን ኢንስፔክተር መሰለ አበራ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በሳምራዊት ስዩም

Screenshot 2024-04-13 201651

ሚያዝያ 5፤2016 – በዲላ ከተማ ንፋስ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሁለት ሰዎች ተጎድተል

 

በዛሬዉ እለት በዲላ ከተማ ከባድ የተባለ ዝናብ መጣሉን ብስራት ሰምቷል። በጌዴኦ ዞን በዲላ ከተማ ንፋስ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያትም ሆኗል።

አደጋው የተከሰተው ዝናብ ተጠልለው ባሉት ልጆች ላይ በግንባታ ላይ ያለ አጥር ተደርምሶ ሲሆን በዚህም  የ 2 ሰዉ ህይወት ስያልፍ በ 2 ሰዉ ደግሞ ከባድ ጉዳት ማድረሱን ነዉ የዲላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ምክትል እንስፔክተር እድገት ህርባዬ መናገራቸውን ዳጉ ጆርናል የሰማዉ።

ከዚህም በተጨማሪ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን  ኢንስፔክተር እድገት ህርባዬ መናገራቸውን ብስራት የደረሰዉ መረጃ ያመላክታል።

Screenshot 2024-04-13 195833

ሚያዝያ 5፤2016 – 18 ሰዓታት በፈጀ  የቀዶ ህክምና 20 ሳ.ሜ ከፍታ ያለው የጭንቅላት እጢ በተሳካ ሁኔታ ተወገደ

 

18 ሰዓታት በፈጀ የጭንቅላት እጢ በቀዶ ህክምና ማስተካከል መቻሉን የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታውቋል።በሆስፒታሉ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አለምሰገድ ጫኔ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት  በቀዶ ህክምናው ዋና ዋና ተግባራት በጭንቅላቱ ላይ የነበረውን 20 ሳንቲሜትር ከፍታ የለው እብጠት በቀዶ ህክምና እንዲወጣ ተደርጓል ።

አያይዘውም እብጠቱ የወጣበትን ቦታ በሌላ የሰውነት ክፍል የመተካት ተግባር ተከናውኗል።በሶስተኛ ደረጃ ከታካሚው ከተለያዮ የሰውነት ክፍሎች ማለትም ከእጆቹ ላይ ደም ቅዳና ደም መልስ ተመሳሳይ ደም ስሮችን ወደጭንቅላቱ እንዲደርስ ተደርጓል  በማለት ለጣቢያችን ገልፀዋል።

በአራተኛ ደረጃ ደግሞ በቀዶ ህክምና  ወቅት በሰውነት ክፍሉ የደም መፍሰስ ችግር እንዳይኖር አስቀድሞ በቂ ደም የመያዝና  የደም ስሮችን የመቋጠር ተግባር  መከናወኑ ተገልጿል።በመጨረሻም ታካሚው ከ18 ሰአታት በኋላ በፅኑ ህሙማን ክፍል እንደቆየ ተደርጓል ያሉት አቶ አለምሰገድ በአሁኑ ሰአት  በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ ይገኛል ሲሉ ገልፀዋል።

በዚህም የተሳካ ቀዶ ህክምና የተሳተፉ የተለያዩ  ስፔሻሊስቶች ፣  ሰብ ስፔሻሊስት ሀኪሞች፣ አኒስቴትክስ፣ ነርሶች ፣ፖርተሮች እና ፅዳቶች  ሲያከናውኑ የነበሩ የቡድን አባላቶች ስራ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ  ተጠቅሷል።ዶ/ር አብዱራዛቅ  የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ስፔሻሊስት ባለሙያና የማክሮ ሰርጀሪ ሰብ ስፔሻሊስት በዚህ ህክምና ላይ ለተሳተፉ አጠቃላይ ሰራተኞች  ምስጋናቸውን  አቅርበዋል።

በቅድስት ደጀኔ

photo_2024-04-08_18-00-21

መጋቢት 30፤2016 – በኦሮሚያ ክልል በአንድ ሳምንት ውስጥ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ23 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ

 

በኦሮሚያ ክልል ከመጋቢት 23 እስከ መጋቢት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናቶች በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች የ24 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ፤ በ20 ሰዎች ላይ ከባድ እና በዘጠኝ ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡

በንብረት ላይ የደረሰዉ ዉድመት በገንዘብ ሲተመን ከ2 ሚሊየን 6መቶ ሺ ብር በላይ እንደሚገመት የኦሮሚያ ክልል የትራፊክ ቁጥጥር ክፍል ባለሙያ የሆኑት ኢንስፔክተር መሰለ አበራ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

አደጋዎቹ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ለሊቱ 8 ፡00 ሰዓት የተመዘገቡ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሞት አደጋዎች የደረሱት በጭነት ተሽከርካሪ፣በህዝብ ማመላለሻ እና በባለ ሦስት እግር (በተለምዶ ባጃጅ) የተከሰቱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የአደጋዎቹ መንስኤዎቹ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማስከርከር፣ለእግረኛ ቅድሚያ አለመስጠት፣የተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር፣ርቀትን ጠብቆ አለማሽርከር፣ ምልክቶችን አለማክበር ፣የጥንቃቄ ጉድለት መሆኑን ኢንስፔክተር መሰለ አበራ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በሳምራዊት ስዩም

photo_2024-04-08_17-58-07

መጋቢት 30፤2016 – በጣሊያን ብልት ለማስረዘም ቀዶ ህክምና የተደረገለት ግለሰብ የብልት መቆም ችግር ያጋጠመው በመሆኑ ዶክተሩ ላይ ክስ መሰረተ

 

የ40 አመቱ ጣሊያናዊ ወንድ ብልት የማሳደግ ቀዶ ህክምና ከተደረገለት በኋላ በተፈጠረበት “የአቅም ማነስ እና የብልት መቆም ችግር” ዶክተር እና ሁለት የህክምና ክሊኒኮች ላይ ክስ መስርቷል።በቱስካኒ፣ ጣሊያን ነዋሪ የሆነው ግለሰብ ለቀዶ ህክምናው 5,400 የአሜሪካን ዶላር ከፍሎ ነበር፣ ነገር ግን ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ዶክተሩን በመደወል ስለ አካላዊ ሁኔታው የደረሰበትን ቅሬታ አቅርቧል።

የጣሊያን የዜና ማሰራጫዎች ከፍርድ ቤት ሰነዶች እንደተመለከቱ ግለሰቡ በተደረገለ ሁለት ቀዶ ህክምና ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ስብ ወደ ብልቱ እንዲዛወር በማድረግ ቅርፁን እንዲያስተካክል ተደርጓል። በሚያሳዝን ሁኔታ ግብ የወንዱ ብልት የሚጠበቀው ቅርፅ እና መጠን ስላልያዘ የተፈለገውን ውጤት አላሳየም። የጣሊያን ጋዜጣ ላ ሪፑብሊካ እንደዘገበው ግለሰቡ በብልት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማስተካከል ሌሎች በርካታ ሂደቶችን አድርጓል ተብሎ ቢነገርም ነገሩን የበለጠ እንዳባባሰው ጽፏል።

በ12 የህክምና ሂደቶች ጉዳት የደረሰበት ግለሰቡ የህክምና ተቋማት ክስ ለመመስረት ወስኗል። ሐኪሙ 60 በመቶውን ካሳ እንዲከፍል የታዘዘ ሲሆን ክሊኒኮቹ እያንዳንዳቸው 20 በመቶ እንዲከፍሉ ተወስኗል። የካሳ ክፍያው 153,000 ዩሮ እንዲሆን ተወስኖ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን 110,000 ዩሮ አካባቢ ተሰጥቶታል። ምክንያቱ ደግሞ ብልቱ ላይ የደረሰው ጉዳት 30 በመቶው በራሱ ጥፋት ነው። ግለሰቡ በቤት ውስጥ ብልቱ ላይ በተመሳሳይ ሀኪም ታዝዘዋል ያላቸውን መርፌ መሰጠቱን አምኗል ይህም ፍርድ ቤቱ ለአካል ጉዳተኝነት እና ለብልት መቆም አስተዋጽኦ አድርጓል ሲል ወስኗል።

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-04-08_16-40-19

መጋቢት 30፤2016 – ከ35 ሺህ በላይ ዜጎች የምገባ አገልግሎት እያገኙ መሆኑ ተነገረ

 

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ 20 የምገባ ማዕከላት ከ35 ሺህ በላይ ዜጎች የምገባ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በዝቅተኛ ኑሩ ደረጃ የሚኖሩ እና በቀን አንድ ግዜ መመገብ ለማይችሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ስንታየው ማሞ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የተናገሩ ሲሆን ከተማ አስተዳደሩ በቀን ከ35ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በ20 የመመገቢያ መአከላት የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛልም ብለዋል፡፡

እንደከተማ ከ90 ሺ በላይ ሰዎች በቀን አንዴ መብላት አይችሉም ተብሎ እንደሚገመት እና በሂደት እነዚህን ዜጎች በምገባ አገልግሎቱ ተጠቃሚ የማድረግ ስራም እየተሰራ እንደሆነ ኤጀንሲው አስታውቃል፡፡

የምገባ ማዕከላቱ በበጎ አሳቢ ግለሰቦች እና ተቋማት ትብብር እውን መሆናቸውን ያነሱት ምክትል ዳይሬክተር ስንታየው አሁንም እነዚህ በጎ አሳቢ ሰዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው በመቀጠል በከተማዋ የሚስተዋሉትን ማህበራዊ ችግሮች በአብሮነት በመተባበር ማቃለል እንደሚቻል አንስተዋል፡፡

ኤጀንሲው በ2016 ዓ.ም በምገባ አገልግሎት በአዲስ አበባ በ477 ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ 629 በድምሩ 1ሺ አንድ መቶ ስድስት በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ለሚገኘ  ከሰባት መቶ ሺ በላይ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉን ብስራት መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በትግስት ላቀዉ

photo_2024-04-02_15-41-01

መጋቢት 23፤2016 – ወደ ጎረቤት ሀገራት በህገወጥ መንገድ ሊሰደዱ የነበሩ ከ 1 ሺህ 100 በላይ ወጣቶች ወደመጡበት አካባቢ ተመለሱ

 

የባሌ ዞንን መሸጋገሪያ በማድረግ ወደ ኬንያ እና ሶማሊያ አጎራባች ሀገራት በህገወጥ መንገድ ሲያዘዋዉሩ የነበሩ 1 ሺህ 115 ወጣቶች በቁጥጥር ስር ዉለዉ ወደመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ ተደርጓል።

በባሌ ዞን የዲንሾ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማደር እሸቱ ለማ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ፤ በዲንሾ ኬላ ላይ በተደረገ ፍተሻ እድሜያቸው ከ 18 እስከ 30 የሚገመቱ ወንዶች በህገወጥ መንገድ ወደ ምስራቅ ባሌ ፣ ቦረና እና ሶማሌ ክልል በማቅናት ወደ ኬንያ እና ሶማሊያ ለመሰደድ ሲጓዙ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ ከአራቱ የወለጋ እና የሸዋ ዞኖች እንዲሁም ከምዕራብና ምስራቅ አርሲ እና ከደብረብርሃን የመጡ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል ብለዋል።

ወጣቶቹ በህገወጥ አዘዋዋሪዎች ተታለዉና ፈቅደዉ የተጓዙ ሲሆን በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላም የተሃድሶ ስልጠና ወስደዉ ወደመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ መደረጉን የዲንሾ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማደር እሸቱ ለማ ጨምረው ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ ሙሉ በሙሉ ወንዶች ሲሆኑ አብዛኞቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ እንዳልያዙም አክለዋል። ኮማንደር እሸቱ እንዳሉት አንዳንዶቹ ተጓዦች ወደየት ሀገር እየተጓዙ መሆኑንም በቂ መረጃ የሌላቸው ነበሩ ብለዉናል። በዚህ ብዛት ደረጃ ወደ ባሌ ዞን የገቡ ህገወጥ ስደተኞች በቁጥጥር ስር ሲዉሉም ይህ የመጀመሪያው ነው።

በበረከት ሞገስ