ጥር 3፤2016 – ለገና በዓል ማክበሪያ ተማሪዎቻቸዉን እስከ 1 ሺህ ብር ድረስ የጠየቁ ትምህርት ቤቶች መኖራቸዉን ወላጆች ተናገሩ

 

👉 መንግስት በትምህርት ቤቶች የወርሃዊ እና ሌሎች ክፍያዎች ላይ ልጓም ሊያበጅ ይገባል ብለዋል ወላጆች

በየአመቱ በወላጆች እና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል የሚፈጠረዉ አለመግባባት ዘላቂ እና ወጥ የአሰራር መፍትሔ የሚያስፈልገው ጉዳይ መሆኑን ወላጆች ተናግረዋል። ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ያነጋገራቸው ወላጆች ለልጆቻቸዉ የገና በዓል ማክበሪያ ከትምህርት ቤቶቻቸዉ እስከ 1ሺህ ብር ድረስ እንደተጠየቁ ተናግረዋል።

ወላጆች በየአመቱ መጨረሻ እና መጀመሪያ ላይ ብቻ የሚዲያዎች ርዕስ እና የመንግስት ስራ የሚሆነዉ የግል ትምህርት ቤቶች ወርሃዊ ክፍያ በቂ ትኩረት ሊሰጠዉ የሚያሻ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። ወላጆች ከዘንድሮዉ በበለጠም መጪዎቹ ጊዜያት አስጊዎች መሆናቸዉን አንስተዋል።

አንዳንድ ወላጆች መንግስት የራሱን የትምህርት ቤቶች ደረጃ አዉጥቶ በእርሱ መሰረት ታሪፍ ሊተምንበት ይገባልም ብለዋል። በአንጻሩ በመምህራን ደሞዝ እየተንተራሰ የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎች በትክክል ለመምህራን ክፍያ ላይ መዋሉንም ሊከታተል ይገባል ብለዋል። ትምህርት ወደ ንግድ ማዘንበሉም የትምህርት ጥራቱ እንዳይሻሻል አድርጎታል የሚሉም አልጠፉም። በአንጻሩ የትምህርት ጥራት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሰልጣን ወላጆችን ከትምህርት ቤቶች ጋር በማስማማት ጭማሪዉን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ቢገልፁም ይህም ፍትሃዊነት የጎደለዉ ነዉ ብለዉናል።

የኢኮኖሚ ባለሙያና የኢኮኖሚክስ ትምህርት መምህር የሆኑት አቶ ፋሲል ጣሰዉ ፤ በትምህርት ቤቶች ላይ የሚደረገዉ የዋጋ ጭማሪ ከገበያ ስርዓቱ ጋር የተጻረረ መሆኑን ጠቅሰዋል። አክለዉም መንግስት በፖሊሲ በታገዘ መልኩ ለትምህርት ቤቶች የራሳቸዉን የመስሪያ ቦታ እንዲያገኙ ማመቻቸት ፤ ርካሽ የሰራተኛ ሀይል የሚል ፖሊሲዉን መቀየርና ሰራተኞች የተሻለ ገቢ ሊያገኙበት የሚችሉበትን አማራጭ መመልከት እንዳለበት ምክረ ሃሳባቸዉን ሰጥተዉናል።

በበረከት ሞገስ

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *