ጥር 13፤2016 – ባለፉት ስድስት ወራት ከ19 ሺህ በላይ ዜጎች ከጎዳና ላይ እንዲነሱ መደረጉ ተገለጸ

 

በተጠናቀቀው ግማሽ አመት 19 ሺህ 756 ዜጎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት የማቋቋም ስራ መከናወኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ሁሪያ አሊ  እንደተናገሩት ባለፉት ስድስት ወራት በከተማ ልማታዊ ሴፍትኔትና ሥራ ፕሮጀክት 4 ሺህ 550 እንዲሁም ከክልሎችና ከፌዴራል ከተማ አሥተዳደሮች በተገኘ በጀት 15 ሺህ 206 ወገኖችን ከጎዳና ላይ በማንሳት የተቋም አገልግሎት እንዲያገኙ እና  ወደ መጡበት አካባቢና ቤተሰቦቻቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ተደርጓል።

በጎዳና የሚገኙ ወገኖችን ለማንሣት እንደ ሀገር እስካሁን በተከናወነው ሥራ የተነሺዎች ቁጥር ከነበረበት 39 ሺህ 082 ወደ 54 ሺህ 288 ከፍ ማለቱንም ሚኒስትር ዲኤታዋ መናገራቸውን ብስራት ሰምቷል።

በቅድስት ደጀኔ

ጥር 13፤2016 – የእስራኤል ጥቃት ከጀመረ ወዲህ በጋዛ ከ25ሺ በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

 

👉 በ24 ሰዓታት ውስጥ 178 ፍልስጥኤማውያን ተገድለዋል

በሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስራኤል ባካሄደችው ጥቃት እስከአሁን በጋዛ ሰርጥ ከ25,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ብቻ 178 ሰዎች መገደላቸው የተገለፀ ሲሆን ይህም እስካሁን በጦርነቱ በአንድ ቀን ከተገደሉት ሰዎች በከፍተኛ ከተመዘገቡት መካካል አንዱ ያደርገዋል።

ጦርነቱ በቀጠለበት ወቅት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የፍልስጤም አገር መፍጠርን በድጋሚ እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል። ዋይት ሀውስ ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል የሁለት ሀገር መፍትሄን በተመለከተ “ነገሮችን በተለየ መንገድ በግልፅ ያዩታል” ብሏል። የእስራኤል የአየር እና የምድር ዘመቻ በአሁኑ ጊዜ በደቡባዊ ጋዛ ላይ ያተኮረ ሲሆን ወታደሮቹ የሐማስ ከፍተኛ አዛዦችን በካን ዮኒስ ከተማ ውስጥ እንደሚገኙ በማስታወቅ ማጥቃቱን ቀጥሏል።

የእስራኤል መከላከያ ሃይል 830 ሜትር ርዝመት ያለው ዋሻ ማግኘቱን ገልጿል።የእስራኤል ወታደሮችም በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል እንደገና ጥቃት ገጥሟቸውል። የእስራኤል ወታደሮችን እና ታንኮችን ወደ ደቡብ ሲያንቀሳቅስ ሃማስ በጃባሊያ ከተማ ዙሪያ ያለውን ክፍት ቦታ ዳግም መቆጣጠሩ ተነግሯል። ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ከሦስት ወራት በላይ ቢያስቆጥርም ብሎም የእስራኤል ሠራዊት ከሃማስ አቅም እጅግ የላቀ ቢሆንም አሁንም በጋዛ ላይ ከፍተኛ ውጊያ እየገጠማቸው ይገኛል።

የአሜሪካ የስለላ ኤጀንሲዎች የእስራኤል ጦር ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆኑ የሃማስ ተዋጊዎችን እንደገደለ ይገምታሉ፣ይህም ኔታንያሁ የታጠቀውን ቡድን “ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት” ከገለፁት አላማ እጅግ ያነሰ ነው። ሚስጥራዊው ዘገባው ሃማስ አሁንም በእስራኤል ወታደሮች ላይ ለወራት ትግል ለማድረግ በቂ ጥይቶች እንዳሉት ተነግሯል።ይህም እስራኤል የተራዘመ ጦርነት እንደሚጠብቃት ማሳያ ሆኗል።

በስምኦን ደረጄ

ጥር 13፤2016 – የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ለመስራት ካቀዳቸዉ 54 የዲዛይን ፕሮጀክቶች ዉስጥ 21 ያህሉን በጸጥታ ችግር መተግበር እንዳልቻለ አስታወቀ

 

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን የ 2016 አመት ስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትን ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርበዋል።

አስተዳደሩ በወራቱ ለመከወን ካከቀዳቸዉ 54 የዲዛይን ፕሮጀክቶች ዉስጥ 21 ያህሉን በጸጥታ ችግር መተግበር እንዳልቻለ ዋና ዳይሬክተሩ ለቋሚ ኮሚቴዉ ተናግረዋል። በዚህም በስድስቱ ወራት የነበረዉ የዲዛይን ስራዎች አፈጻጸም 57 በመቶ ሲሆን ይህም ዝቅተኛ እንዲሆን እንዳደረገበት ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል። በተጨማሪም በዉጭ አማካሪ ድርጅት ለተሰራ ስራ ክፍያ የዉጭ ምንዛሪ በመዘግየቱ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች መኖራቸዉንም ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል። በተለያዩ ምክኒያቶችም 84 ፕሮጀክቶች መቋረጣቸዉ እና ሙሉ በሙሉ የኮንትራት ዉላቸዉ መዘረዙም ተነግሯል።

የግብዓት እጥረት ፣ የወሰን ማስከበር ችግር እና የተጋነነ የካሳ ተመን ተቋሙ በወራቱ ካጋጠሙት ችግሮች ዉስጥ ችግር ሆነዉ መቀጠላቸውን አስረድተዋል። ሌላዉ አስተዳደሩ በመንገዶች ጥገና እና ግንባታ በወራቱ የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን በኢትዮጵያ 169 ሺህ 450 ኪ.ሜ መድረሱን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን መናገራቸውን ብስራት ሰምቷል።

በበረከት ሞገስ

photo_2024-01-22_13-20-03

ጥር 13፤2016 – በኬንያ የሚገኙ የአርሰናል ደጋፊዎች ከድል በኋላ በቤተክርስቲያን ዉስጥ ምስጋና አቀረቡ

 

በኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ የሚገኙት የአርሰናል ደጋፊዎች ቅዳሜ እለት ባደረጉት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ቡድናቸው ክሪስታል ፓላስን 5 ለ 0 በመርታቱ አድናቆትን ከማትረፍ ባለፈ በአንድ አጥቢያ ቤተክርስትያን በመሰባሰብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ደጋፊዎቹ የመድፈኞቹን ማሊያ ለብሰው በእሁድ ጠዋት አገልግሎት ላይ ቡድናቸው ላሳየው አስደናቂ ብቃት በደስታ ውዳሴ እና ምስጋና አቅርበዋል።በመጪው የውድድር ዘመን ለአርሰናል ቀጣይ ስኬት ተስፋ በማድረግ ጸሎት አቅርበዋል።

ከታዳሚዎቹ መካከል ጋዜጠኛ ኬኔዲ ሙሪቲ በፀሎት ስነ ስርዓቱ ላይ የተነሱትን ፎቶዎች በማህበራዊ ሚዲያ ተጋርቷል።የሰሜን ለንደኑ አርሰናል አንድ ጨዋታ ከሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ እኩል እና ከሊቨርፑል በአምስት ነጥብ ዝቅ ብሎ ተቀምጧል።

ፎቶዎቹ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን የፈጠሩ ሲሆን አንዳንዶቹ በደጋፊዎች ላይ ተሳልቀዋል፡፡

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-01-22_07-44-58

ጥር 13፤2016 – ሮን ዴሳንቲስ ከፕሬዝዳንትነት ውድድር በመውጣት ትራምፕን በይፋ ደገፉ

 

የፍሎሪዳ ገዥ ሮን ዴሳንቲስ እ.ኤ.አ. ከ2024 ፕሬዚዳንታዊ ውድድር ራሳቸውን በማግለል ዶናልድ ትራምፕን ደግፈዋል። በኒው ሃምፕሻየር ከሚካሄደው የሪፐብሊካን ምርጫ አስቀድመው ይህንኑ ውሳኔ አሳልፈዋል። ዴሳንቲስ በአንድ ወቅት ለፓርቲው እጩ ጠንካራ ተፎካካሪ ተደርገው ይወሰድ የነበረ ቢሆንም በትላንትናው እለት ግን ይህ ፉክክራቸው እንዳበቃ እና ለሪፐብሊካን እጩነት የሚያበቃ ግልፅ የድል መንገድ የለም ብለዋል ።

የትራምፕ የመጨረሻ ቀሪ ተፎካካሪ የሆነችው ኒኪ ሃሌይ ስትሆን የወቅቱን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ማሸነፍ የምችለው እኔ ብቻ ነኝ ስትል ናግራለች። ኒኪ ሃሌይ በነገው እለት በኒው ሃምፕሻየር ከትራምፕ ጋር ፊት ለፊት ይፎክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህም በህዳር ወር አጠቃላይ ምርጫ የሪፐብሊካን እጩን ለመምረጥ በግዛት ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ ነው።እሁድ ከሰአት በኋላ በኤክስ ላክ በተለቀቀው አምስት ደቂቃ የሚጠጋ ቪዲዮ ላይ  ዴሳንቲስ ዘመቻዬ አብቅቷል ብለዋል።

የፍሎሪዳ ገዥው በአዮዋ የመጀመሪያውን ውድድር 51 በመቶ ድምጽ በማሸነፍ ግንባር ቀደም የሆኑትን ትራምፕን እደግፋለሁ ብለዋል።ዴሳንቲስ አብዛኞቹ የሪፐብሊካን መራጮች “ለዶናልድ ትራምፕ ሌላ እድል መስጠት እንደሚፈልጉ” ግልጽ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል።ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ጋር አለመግባባቶችን እንደነበረ ግን ዴሳንቲስ አምነዋል ።ነገር ግን ትራምፕ በህዳር አጠቃላይ ምርጫ የዴሞክራቲክ እጩ ከሆኑት ባይደን በላይ ናቸው ብለዋል ።

ዴሳንቲስ “የሪፐብሊካንን እጩ ለመደገፍ ቃል ፈርሜያለሁ፣ እናም ይህን ቃል አከብራለሁ” ብለዋል። ትራምፕ እሁድ ከሰአት በኋላ በኒው ሃምፕሻየር ውስጥ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ስለ ዴሳንቲስ ከተፎካካሪነት ራሳቸውን ማግለል አስመልክቶ የመጀመሪያ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ከፍተኛ ደስታ ውስጥ ነበሩ። በድጋፍ ሰልፍ ላይ ለተገኙት ታዳሚዎች ንግግር ሲያደርጉ፣  የቀድሞ ተቀናቃኛቸውን “በጣም አስፈሪ ሰው” ሲሉ ገልጸዋል፣ በማከልም “በጣም ጥሩ ዘመቻ አካሂዷል፣ ቀላል አልነበረም” ብለዋል።

በቤዛዊት አራጌ

Screenshot 2024-01-21 202649

ጥር 12፤2016 -በታታ ሙምባይ ማራቶን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ አሸነፉ

 

ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶሽ  በታታ ሙምባይ ማራቶን በበላይነት የጨረሱ ሲሆን የዓምናው ሻምፒዮኑ  ለሚ ብርሃኑ እና አበራሽ ሚንሰዎ በዛሬው እለት በተካሄደው ውድድር በወንዶች እና በሴቶች አሸንፈዋል።

ሙሉ ውጤት

በወንዶች

1.ለሚ ብርሃኑ           2:07:50 🇪🇹

2. ኃይማኖት አለው    2:09:03 🇪🇹

3.ምትኩ ታፋ           2:09:58 🇪🇹

4.ጆሽዋ ኮጎ            2:10:00 🇰🇪

5.ዲክሰን ኪፕቱ        2:11:26 🇰🇪

6.ዮሃንስ መካሻ.       2:14:39 🇪🇹

7.አሌክስ ኪባሩስ          2:16:09 🇰🇪

8.ሲሪኑ ቡጋታህ        2:17:29 🇮🇳

——
በሴቶች

1.አበታሽ ሚንሰው  2:26:06 🇪🇹

2.ሙሉኃብት ፀጋ    2:26:51 🇪🇹

3. መድኅን ደጀኔ     2:27:34 🇪🇹

4.ዓይንአዲስ ተሾመ 2:27:58 🇪🇹

5.አበራሽ ደምሴ 2:29:04 🇪🇹

6.አንቺዓለም        2:29:58 🇪🇹

7.አያንቱ ገመቹ   2:30:19 🇪🇹

8.ፋንቱ ገለዛ         2:30:31 🇪🇹

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-01-20_13-35-11

ጥር 11፤2016 – አሽከርካሪውን ገድለው ሞተር ሳይክል የወሰዱ ተከሳሾች ከ24 ዓመት እስከ እድሜ ልክ እስራት ተቀጡ

 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በዳውሮ ዞን በሎማ ቦሣ ወረዳ ሻይቲ ፉላሳ ቀበሌ ተሳፋሪ መስለው ሞተር ሳይክል ለመቀማት አሽከርካሪውን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉ ተካሳሾች ከ24 ዓመት ፅኑ እስራት እስከ እድሜ ልክ እስራት መቀጣታቸው ተነግሯል ።

ተከሳሾች 1ኛ አረጋ አርጃ ፣ 2ኛ ካለብ ዲናቶ እና 3ኛ ሰውለሰው በቀለ ሲሆኑ  በረቀቀ መንገድ በምስጥር በመደራጀት ያልተገባ የንብረት ጥቅም ለማግኘት ሟች ጌታሁን ከንፈሻ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪ ላይ የግድያ ወንጀል መፈጸማቸው ተነግሯል ።

የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት ገደማ ከሚኖርበት ዲሣ ከተማ ተሳፋሪ በመምሰል በ3ኛ ተከሳሽ አቀናባሪነት ሟችን ጠርተው  በማስወጣት ወደ ገሣ ከተማ አስተዳደር አድርሰን በማለት በሟች ሞተር ሳይክል ተሳፍረው ለመሄድ እንደተስማሙ ተገልጿል ።

በዚህም መሠረት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በሟች ሞተር ሳይክል ተሳፍረው ወደ ሎማ ቦሣ ወረዳ ሻይቲ ፉላሳ ቀበሌ ኦቺ የሚባል ቦታ ሲደርሱ ሟችን ሽንት እንሸናለን በማለት ወርደው በቦታው በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለው አስክሬኑን ከእንጨት ጋር አስረው በማስቀመጥ የሟች ሞተር ሳይክል ይዘው እንደተሰወሩ ተጠቅሷል ።

ተከሳሾቹ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ከተሻገሩ እና ከአከባቢው ከተሰወሩ በኃላ የዞኑ ፓሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላትና ከህብረተሰብ ጋር ባደረገው ብርቱ ክትትል እንደተያዙ የዳውሮ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አ/ቶ ፍቃዱ ደምሴ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ። የዞኑ ፍትህ መምሪያ ልዩ ልዩ ወንጀሎች ዐቃቤ ህግ በሶስቱም ተከሳሾች ላይ ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መመሰረቱ ተገልጿል።

ተከሳሾች ችሎት ቀርበው የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም በማለት ክደው ቢከራከሩም በዐቃቤ ህግ የቀረበው ማስረጃ ተከሳሾች ወንጀል መፈጸማቸውን  የሚያስረዳ በመሆኑ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን እንደተሰጣቸውም ተነግሯል።  ነገር ግን ተከሳሾች አቅርበው ባሰሙት መከላከያ ማስረጃ የዐቃቤ ህግን ክስና ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተልፏል ።

ስለሆነም የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት አንደኛ ተከሳሽ አ/ቶ አረጋ አርጃ እና 2ኛ ተከሳሽ አ/ቶ ካለብ ዲናቶ በ24 አመት ጽኑ እስራት እና 3ኛ ተከሳሽ አ/ቶ ሰውለሰው በቀለ በዕድሜ ልክ እስራት እንድቀጡ ወስኗል።

በአበረ ስሜነህ

photo_2024-01-19_12-32-09

ጥር 10፤2016 – በአሜሪካ አንድ ግለሰብ 27 ሴቶች ከእኔ ጋር በነበራቸውን የፍቅር ግንኙነት ላይ አሉታዊ አስተያየትን በፌስቡክ ሰጥተዋል ሲል ክስ መሰረተ

 

በቺካጎ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ በፌስቡክ የፍቅር ጓደኝነት ቡድን ላይ ስለ እኔ አሉታዊ አስተያየቶችን ሰጥተዋል በማለት 27 ሴቶችን በመክሰስ 75 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ጠይቋል።

ግለሰቡ እነዚሁ ሴቶች እኔ በጣም ተንኮለኛ እና ከመናፍስታዊ አሰራር ጋር ትስስር ያለኝ በማስመሰል ጠርተውኛል ብሏል።የ32 አመቱ ኒኮ ዲ አምብሮሲዮ ከእርሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው በርካታ ሴቶች አሉታዊ ቆይታ ነበር ሲል በፌስቡክ ላይ የጋራ መድረክ በሆነው ‘ከተመሳሳይ ሰው ጋር በፍቅት ተጣምረን ይሆን’ በሚለው ግፅ ላይ ሴቶቹ ታሪካቸውን ካጋሩ በኋላ ስሜ ጠፍቷል ብሏል።

ታዋቂው ይህ የፌስቡክ ገፅ መነሻውን በኒውዮርክ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ ሌሎች ዋና ዋና የአሜሪካ ከተሞች ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል። የፌስቡክ ገፁ ዋና ተጠቃሚ ሴቶች ሲሆን ከፍቅረኛቸው ጋር የነበራቸውን ልማድ እርስ በእርስ ከመለዋወጣቸው ባለፈ ተመሳሳይ ወንድ ግን በተለያየ በአንድ አጋጣሚ ፍቅር ውስጥ ከነበሩ ያ ሰው ምን ዓይነት ባህሪና ድክመት እንዳለበት መረጃ የሚለዋወጡበት ስርዓት ነው።

የዚሁ ገፅ ሰለባ የሆነው ዲ አምብሮሲዮ በደርዘን የሚቆጠሩ ሴቶች ተንኮለኛ የፈለገውን ካገስኘ በኋላ የሚሰወር ሰው በማለት የገለፁት ሲሆን በአብዛኛው እርሱን የሚያንቋሽሹ አስተያየቶችን ጽፈዋል።ይህው የቺካጎው ሰው ታዲያ ሴቶቹ ላይ ፣የፌስቡክ ገፁን መስራች እና የፌስቡክ ወላጅ ኩባንያ ሜታ ለጠፋው ስሜ 75 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ክፈሉኝ ብሏል።

የሰውዬው ጠበቆች በተከሳሾቹ ድርጊት የተነሳ የስም ማጥፋት፣የማስፈራራት እና የግላዊ መብትን የሚጥስ ወረራ እንደተፈጸመበት እና ካሳ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል።ዲ አምብሮሲዮ ፎቶዎቼ በፌስቡክ ላይ መሰራጨቱ የበዛ አሉታዊ አስተያየቶች ዒላማ ሆኛለሁ “በግል ውርደት፣ አእምሮአዊ ስቃይ ፣የስሜት ጭንቀት፣ እንዲሁም የገቢ ማጣት” እንዳስከተለበት ተናግሯል።

በስምኦን ደረጄ

ጥር 10፤2016 – በበቆሎ እርሻ ዉስጥ ከማሳ ጋር የተዘራ አደንዛዥ እፅ እንዲወገድ ተደረገ

 

በምዕራብ አርሲ ዞን ወንዶ ወረዳ ከበቆሎ እርሻ ዉስጥ ከበቆሎ ጋር የተዘራ አደንዛዥ እፅ እንዲወገድ መደረጉን የወንዶ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ገለፀ።

የወንዶ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ኑሩ ጃርሶ ለብስራት ቴሌቬዥንና ራዲዮ እንደገለፁት በበቆሎ እርሻ ዉስጥ ከበቆሎ ጋር ተደባልቆ የተዘራ አደንዛዥ እፅ እንዲወገድ የተደረገዉ ህብረተሰቡ ለፖሊስ በሰጠዉ ጥቆማ መሆኑን ገልፀዋል።

በሻሸመኔ ዙሪያ በሻላና በወንዶ ገነት አካባቢ አርሶ አደሩ ከሰብል ምርቶች ጋራ በመቀላቀል ሀሽሽን በድብቅ ዘርቶ እንዲያበቅል የተደረገ በመሆኑ ማህበረሰቡ እራሱ ባደረገዉ ዉይይት ሀሽሽን ከአዝዕርት ጋራ ቀላቅሎ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ከበድ ያለ ዉሳኔ እዲተላለፍባቸዉ መወሰኑን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም አንዳንድ አርሶ አደርች ሀሽሽን ከሚያዘዋዉሩ ነጋዴዎችና ደላሎች በመታለል ከዲርጊቱ ያልተቆጠቡ በመሆናቸዉ ስር ነቀል ልዉጥ ለማምጣት ሰፊ እርምጃና የማነቃቂያ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ምክትል ኢንስፔክተር ኑሩ ጃርሶ ጨምረዉ ተናግረዋል።

በበቀለ ጌታሁን

ጥር 10፤2016 – በሰሜን ኮርያ የደቡብ ኮርያን ተከታታይ ድራማ ሲከታተሉ የተገኙ ታዳጊዎች የ12 ዓመታት ቅጣት ተጣለባቸው

 

በሰሜን ኮሪያ ሁለት ታዳጊ ወንድ ልጆች የደቡብ ኮርየን ድራማ በመመልከታቸው ለ12 ዓመታት ከባድ የጉልበት ሥራ በአደባባይ ተፈርዶባቸዋል። እ.ኤ.አ. በ2022 የተቀረፀ በሚመስል ቪዲዮ ላይ እንደተመላከተው ሁለት የ16 አመት ወንድ ልጆች በመቶዎች በሚቆጠሩ ተማሪዎች ፊት እጃቸውን በካቴና ታስረው በስታዲየም ውስጥ ይታያሉ።

በተጨማሪም የደንብ ልብስ የለበሱ የፖሊስ መኮንኖች ስህተታቸው በጥልቀት እንዲያሰላስሉ ሲገሰጹ ያሳያል። የቲቪ ድራማን ጨምሮ የደቡብ ኮሪያ የመዝናኛ ፕሮግረሞች በሰሜን ኮርያ መከታተል ክልክል ነው። ያም ሆኖ ግን፣ አንዳንዶች ዓለም አቀፋዊ ተመልካቾች ያላቸውን ያላቸውን የደቡብ ኮርያ ድራማዎች መከታተል ከባድ ቅጣት ሊያስጥል የሚችል ቢሆንም ይህንን ቅጣት ለመቀበል ሲደፍሩ ይታያል።

በ2020 ፒዮንግያንግ የደቡብ ኮሪያን መዝናኛ መመልከት ሆነ ማሰራጨት በሞት የሚያስቀጣ ህግ አውጥታ ነበር። የደቡብ ኮሪያ ፊልሞች በቻይና በኩል ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚገቡ ሲሆን ለሰሜን ኮርያ ወጣቶች ከመዝናኛነት ባለፈ ችግርና ጭንቀትን ለመርሳት እንደሚረዱ ይታመናል። የአሜሪካን ድራማ ስትመለከት ከተያዝክ ጉቦ ሰጥተህ ማምለጥ ትችላለህ ነገር ግን የኮሪያ ድራማ ከተመለከትክ ጥይት ይተኮስብኃል ሲል አንድ የሰሜን ኮርያ ተወላጅ ተናግሯል።

በስምኦን ደረጄ