photo_2024-01-23_15-35-08

ጥር 14፤2016 – እስራኤል 24 ወታደሮቿ በጋዛ ሰርጥ በአንድ ቀን ውስጥ መገደላቸውን አስታወቀች

 

የእስራኤል ጦር 24 ወታደሮቹ በጋዛ ሰርጥ በትላንትናው እለት መገደላቸውን ያስታወቀ ሲሆን ጦሩ የምድር ዘመቻ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እጅግ አስከፊው ቀን ነው ብሏል። ከሟቾቹ መካከል 21የእስራኤል ወታደሮች በተቀበሩ ፈንጂዎች በተፈጠረ ፍንዳታ ህይወታቸው ማለፉን የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት (አይዲኤፍ) አስታውቋል። የፍልስጤም ታጣቂ ተዋጊዎች የተተኮሱት ሚሳኤል የወታደሮቹ ፈንጂዎች ሳይመተ እንዳልቀረ ተነግሯል።

የመከላከያ ሰራዊት ምን እንደተፈጠረ እንደሆነ እየመረመረ ይገኛል። በጋዛ ሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ባለፈው 24 ሰዓት ብቻ 195 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።የእስራኤል ጦር ዋና ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ እንዳሉት ተጠባባቂ ወታደሮቹ የተገደሉት በማዕከላዊ ጋዛ ሰኞ እለት በእስራኤል ድንበር ላይ በሚገኘው ኪስሱፊም ኪብቡዝ በተባለው ስፍራ ነው።

በፍንዳታው ለተገደሉት ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት ዝናባማ በሆነው በእየሩሳሌም ሄርዝ ተራራ ተፈጽሟል። ብዙዎቹ ሀዘንተኞች የወታደር ልብስ ለብሰው ቦታው በሰማያዊ እና በነጭ የእስራኤል ባንዲራዎች ተሞልቶ ታይቷል።የእስራኤል ጦር ባለፈው ሰኞ በደቡባዊ ጋዛ በተፈፀመ የተለየ ጥቃት ሶስት መኮንኖች መገደላቸውን አረጋግጧል።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንዳሉት ምንም እንኳን መከራና ስቃይ ቢኖራትም ሀገራቸው ፍፁም ድል እስክታገኝ ድረስ ጥቃቷን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።በሌላ በኩል በጋዛ፣ በደቡባዊ ካን ዮኒስ ከተማ ውስጥ በሶስት ሆስፒታሎች ከባድ ውጊያ ተካሂዶ አካባቢው በተፈናቀሉ ሰዎች ተጨናንቋል። የእስራኤል መከላከያ ሃይሉ የካን የኒስ ከተማን ሙሉ በሙሉ መክበቧን አስታውቋል።

ይህም በሃማስ ላይ ያነጣጠረው የምድር ጥቃት ዋና ትኩረት ነው። እስራኤል የቡድኑ መሪዎች እዚያ ተደብቀው ሊገኙበት የሚችለው ስፍራ እንደሆነ እና አንዳንድ እስራኤላውያን ታግተው የሚገኙበት ሊሆን እንደሚችል ታምናለች።

በስምኦን ደረጄ

ጥር 14፤2016 – በአሜሪካ ሪፐብሊካን ፓርቲን ለመወከል በኒው ሃምፕሻየር ዶናልድ ትራምፕ እና ኒኪ ሃሌይ ዛሬ ፊት ልፊት ይፋለማሉ

 

ዶናልድ ትራምፕ በዛሬው እለት በኒው ሃምፕሻየር ቅድመ ምርጫ የመጨረሻዋን ቀሪ የሪፐብሊካን ተቀናቃኛቸውን ኒኪ ሃሌይን ይገጥማሉ። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከቀድሞዋ የደቡብ ካሮላይና ገዥ ጋር የሪፐብሊካን እጩ ለመሆን በሚያደርጉ ዘመቻ እንደሚያሸንፉ በርካቶች ተስፋ አድርገዋል።

ኒክ ሃሌይ የኒው ሃምፕሻየር መራጮች እንደሚረዷት ተስፋ እንደምታደርግ ገልጸዋል። ይህው የምርጫ ሂደት ባለፈው ሳምንት በአዮዋ ተካሂዶ ትራምፕ በከፍተኛ ድምፅ ማሸነፋቸው ይታወሳል። የመጨረሻው የሪፐብሊካን እጩ የዲሞክራቱን እጩ ምናልባትም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን በቀጣዩ ዓመት ህዳር ወር አጠቃላይ ምርጫ ላይ ይገፎካከራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

photo_2024-01-23_15-19-52

ጥር 14፤2016 – 83 ዓይነት የጨው እና የዘይት ምርቶች ጥቅም ላይ እነዳይውሉ ታገዱ

 

ከታገዱት ውስጥ 44 ዓይነት የምግብ ዘይት እና 39 ዓይነት የምግብ ጨው ምርቶች ደህንነታቸውና ጥራታቸው ያልተረጋገጡ በመሆናቸው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ይፋ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በአዮዲን የበለፀገ የምግብ ጨው እና የምግብ ዘይት ላይ በተደረገ የገበያ የቅኝት ስራ የገላጭ ጽሁፍና የኢትዮጵያ አስገዳጅ ደረጃ ሳያሟሉ እንዲሁም ደህንነታቸውና ጥራታቸው ሳይረጋገጥ ገበያ ላይ የዋሉ ምርቶችን ህብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው አሳስቧል፡፡

የባለስልጣኑ የህዝብ እና ኮምንኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ አበራ ደመቀ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን እነደተናገሩት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሰራው የገበያ ቅኝት ስራዎች እንዳረጋገጠው  44 ዓይነት የምግብ ዘይት ምርት እና 39 ዓይነት አዮዲን የበለፀገ የምግብ ጨው ምርት  ደህንነታቸውና ጥራታቸው ያልተረጋገጡ እንዲሁም የሀገሪቱን አስገዳጅ ደረጃ እና የገላጭ ጽሁፍ ደረጃ ሳያሟሉና ሳይለጥፉ መገኘታቸው ገልጸዋል፡፡

በገበያ ላይ የዋሉት ምርቶችን የገበያ ቅኝት ስራዎችን በማጠናከር እና የቁጥጥር መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ባለስልጣኑ ህብረተሰቡ እራሱ የቁጥጥር ባለቤት እንዲሆን ሲያደርግ መቆየቱ ዳሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም በየደረጃው ከሚካሄዱ በርካታ የቁጥጥሩ ስራዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የገበያ ቅኝት ሲሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ምግቦች  ላይ ባደረገው የገበያ ቅኝት በአዮዲን የበለፀገ የምግብ ጨው እንዲሁም ለምግብነት የሚውሉ   የተለያ ዓይነት ማለትም የበቆሎ፣ የሰሊጥ  ፣ የኦቾሎኒ  ፣ የሱፍ አበባ ፣ የጥጥ ዘይት  እና የአትክልት ዘይት የኢትዮጵያ አስገዳጅ ደረጃ ያላሟሉ እና የደረጃ ምልክት ያለጠፉ ምርቶችን መለየታቸውን አቶ አበራ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በምርቱ ላይ ስለምርቱ የተለጠፉ ወይም የተፃፉ የምርት ገላጭ ፅሁፍ የኢትዮጵያ እስታንዳርድ ኢንስቲቲዩት ያወጣው አስገዳጅ  ደረጃ CES 73 2013  ያላሟሉ ሲሆን በቁጥጥር ወቅት የተገኙ ግኝቶች የአምራች ድርጅት ስም ያልተጠቀሰ፣ የአምራች አድራሻ ያልተገለፀ፣ የኢትዮጵያ አስገዳጅ የደረጃ ምልክት የሌለው፣የምርቱ መለያ ቁጥር የሌለው፣የምርቱ ጥሬ ግብዓት ዝርዝር ያልተገለፀ፣ የመጠቀሚያ እና የማብቂያ ጊዜ የሌላቸው ምርቶች መሆናቸው ተለይተዋል፡፡ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የተከለከሉት የዘይትም ሆነ የጨው ምርቶች ዝርዝር ተያይዛል፡፡

አስገዳጅ የሀገሪቱን ደረጃና የገላጭ ጽሁፍ ደረጃን ሳያማሉ ገበያ ላይ የተገኙ
የምግብ ዘይት ምርቶች ዝርዝር

1. ሰመር  ንፁህ የምግብ ዘይት
2. ማሚ የተጣራንፁህ የምግብ ዘይት
3. እስካይ  /Sky Sun flower oil
4. ሳኒ /SANI  Edible Cooking Oil)
5. አዚማር/Azimar Sunflower Oil
6. ኑራ ንፁህ የምግብ ዘይት
7. አበባ ንፁህ የምግብ ዘይት
8. አደይ ንፁህ የምግብ ዘይት
9. ዘቢብ/Zebib Sunflower oil
10. አስሊ ንፁህ የምግብ ዘይት
11. ሪል (Real Pure Food Oil)
12. ዙፋን ንፁህ የምግብ ዘይት
13. ሀኒ(Hani Sunflower Oil)
14. ዲና ንፁህ የምግብ ዘይት
15. ሊና ንፁህ የምግብ ዘይት
16. ማማ የተጣራ የምግብ ዘይት
17.  አል ኑር Al-Nur Sunflowor Oil
18. ዋሪዳ Warida sunflower Oil
19. ዜድ ንፁህ የምግብ ዘይት
20. ደሴት ንፁህ የምግብ ዘይት
21. ከፍታ ንፁህ የምግብ ዘይት Pure Food Oil
22. ንግስት ንፁህ የምግብ ዘይት Nigist pure Food oil
23. ሸገር Sheger pure Edible Oil
24. አሪፍ Arif  የኑግ የምግብ ዘይት
25. አመለ AMEL Edible Oil
26. ብሉ የኑግ ዘይት
27. ንፁህ Nitsuh Food Oil
28. ኡማ ንፁህ የምግብ ዘይት
29. ማዕድ Maed ንፁህ የምግብ ዘይት
30. ሀያት የተጣራ የምግብ ዘይት
31. የምስራች ንፁህ የምግብ ዘይት
32. ህብረት ንፁህ የምግብ ዘይት
33. ጎንደር የምግብ ዘይት Gonder Food Oil
34. ዜማ Zema pure Edible Oil
35. ፋና fana
36. ናና የኑግና የለውዝ የምግብ ዘይት
37. ሪም ንፁህ የምግብ ዘይት
38. አንድነት ANDNET
39. ሲያም ንፁህ የምግብ ዘይት
40. ቤላ  የምግብ ዘይት
41. ሐሊማ  የምግብ ዘይት
42. ወሲላ ንፁህ የምግብ ዘይት Wesila
43. ዝና ንጹህ የምግብ ዘይት
44. ሰነዓ ንጹህ የምግብ ዘይት

#ተጨማሪ

አስገዳጅ የሀገሪቱን ደረጃና የገላጭ ጽሁፍ ደረጃን ሳያማሉ ገበያ ላይ የተገኙ
የምግብ ጨው
1.    አርኪ የገበታ ጨው  ARKY IODIZED SALT
2.    ኢኮ  አዮዳይዝድ ጨው EKKO IODIZED SALT
3.    ስጦታ ጨው  SITOTA Iodized Salt
4.    መስቱራ ባለ አዮዲን የተፈጨ ጨው MESTURA REFIND & IODIZED SALT
5.    አስቤዛ የገበታ ጨው  Asbeza Iodized salt
6.    ዘሀራ የገበታ ጨው  ZAHARA IODIZED SALT
7.    መነስ ጨው MENES IODIZED SALT
8.   ግዩን አዮዲን ጨው Ghion Iodin Salt
9.    አርዲ የገበታ ጨው  ARDI IODIZED SALT
10.    ሳሊህ የገበታ ጨው  SLIHA IODIZED SALT
11.    ናና ጨው NANA SALT
12.    ቤስት የገበታ ጨው Best Iodized Salt
13.    ቅመም የገበታ ጨው Iodized Salt
14.    ረሃ የገበታ ጨው REHA IODIZED SALT
15.    አርዲ የገበታ ጨው ARDY IODIZED SALT
16.    አፊአ የገበታ ጨው AFIA IODIZED SALT
17.    ፋና የገበታ ጨው  Fana table salt
18.    እቴቴ የገበታ ጨው  Etete Iodized Table Salt
19.    ልዩ ጣዕም የገበታ ጨው  LIYU TAEM IODIZED Salt
20.    ሀሮኒ  HARONI Table Salt
21.    ሮም  ROME  ንጹሁ የገበታ ጨው
22.    ቶፕ የገበታ ጨው  TOP IODIZED SALT
23.    ጤና ጨው Tena Iodized salt
24.     ማሬ የገበታ ጨው  MARE IODIZED SALT
25.     ሳፊ የገበታ ጨው  SAFI IODIZED SALT
26. እሜቴ  አዮዳይዝድ  የገበታ ጨው  Iodized Table Salt
27.     ሀላል የገበታ ጨው  HALAL IODIZED SALT
28.     ጡልት ጨው TULIT SALT
29. ሪል የገበታ ጨው  REAL IODIZED SALT
30.     ጎልድ GOLD IODIZED SALT
31.     ስፔሻል የገበታ ጨው  SPECIAL Iodized Table Salt
32.     ሰላም  የገበታ ጨው  IODIZED SALT
33.     ሸሙ በአዮዲን የበለጸገ የገበታ ጨው  SHEMU  IODIZED SALT
34. ኢምሬት ጨው Emirate salt
35.     ኑር NUR IODIZED SALT
36. ሀገሬ አዮዳይዝድ ጨው  HAGERE  Iodized Salt
37.     ኢቲ ኤምኢየገበታ ጨው  ET ME IODIZED SALT
38. ማራኪ MARAKI  በአዮዲን የበለጸገ የገበታ ጨው
39.     ታሪክ የገበታ ጨው TARIK TABLE SALT

በትግስት ላቀዉ

photo_2024-01-23_11-48-47

ጥር 14፤2016 – ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ወራት  11.05 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

 

👉🏼ባለፈው ስድስት ወር 18.5  ቢሊዮን ብር  ታክስ መክፈሉም ተነግሯል

ኢትዮ ቴሌኮም የ2016 ዓ.ም የስድስት ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን አቅርቧል።  በስድስት ወሩ  አዳዲስ አገልግሎቶችን ከማስተዋወቅ አንጻር ለመስራት  አቅዶ የነበረ መሆኑን ተጠቁሟል ። በዚህም 232 አዳዲስ የሞባይል  ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

በ 3G 678.2 ሺህ  ፣ 4G 1.1 ሚሊዮን  ፣5G 148.2 ሺህ በድምሩ 1.9 ሚሊዮን  ተጨማሪ አዳዲስ የሞባይል  ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም የፈጠረ የሞባይል ኔትዎርክ የተዘረጋ መሆኑን እና በዚህም  የደንበኞች ቁጥር በአጠቃላይ 81 ሚሊዮን መድረሱ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ በሪፖርታቸው ገልጸዋል ።

በመፈንቅ ዓመቱ ለገጠር  ቀበሌዎች የሚውል  በ10 ክልሎች ለ41 ወረዳዎች ፣ 229 ሺህ ደንበኞች ማስተናገድ  የሚችሉ 41 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎች  አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ የኦፕሬተሮች ቁጥር በመያዝ  በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል  በተጨማሪም 42.9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ችሏል በዚህም ከተያዘው እቅድ 98 በመቶ  ማሳካት መቻሉ እና 26 በመቶ እድገት ማሳየት መቻሉ  ብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ሰምቷል ። ከዚህም ከፍተኛ ድርሻውን የሚይዘው የድምፅ አገልግሎት  መሆኑም ተጠቁሟል። ባለፈው ተመሳሳይ ዓመት 9. 7 ቢሊዮን  ብር የነበረው ትርፍ በዘንድሮ ዓመት 14 በመቶ  እድገት አሳይቷ 11.05 ቢሊዮን ብር   ትርፍ ማግኘቱም ተነግሯል።

ኢትዮ ቴሌኮም ካደረጋቸው ዋና ዋና ክፍያዎች መካከል ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘው የታክስ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በዚህም 18.5 ቢሊዮን ብር ታክስ መክፈሉ የኢትዮ ቴሌኮም  ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ገልጸዋል ።

በኤደን ሽመልስ

ጥር 14፤2016 – በእፎይታ የገበያ ማዕከል ጀርባ በደረሰ የእሳት አደጋ ሰባት የንግድ ሱቆችና ሁለት መጋዘኖች ሙሉ በሙሉ ወደሙ

 

👉🏼 በእሳት አደጋው ሁለት ሰዎች ላይም ጉዳት አድርሷል

ትላንት ምሽት 2:47 በአዲስ ከተማ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 10 እፎይታ የገበያ ማዕከል ጀርባ በሚገኙ የንግድ ሱቆች እና መጋዘኖች ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት በእሳት አደጋዉ  ሰባት የንግድ ሱቆችና ሁለት መጋዘኖች በዉስጣቸዉ ካሉ ንብረቶች ጋር ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።

በእሳት አደጋዉ በሁለት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት የደረሱ ሲሆን በሰባቱ የንግድ ሲቆች የተለያ የልብስ መስፊያ በርካታ ሲንጀሮች ሚሊ በሚሊ የወደሙ ሲሆን በሁለቱ መጋዘን  ውስጥ የነበሩ ጨርቃ ጨርቆችን እና ስፖንጆችም መውደማቸው ተነግራል፡፡

የእሳት አደጋዉን ለመቆጣጠር 11 የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪዎች ከ60 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጋር የተሰማሩ ሲሆን የእሳት አደጋዉ በአካባቢዉ ባሉ የንግድ ሱቆች ተዛምቶ በገበያ ማዕከላቱ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር ተችሏል።

የእሳት አደጋዉን ለመቆጣጠር ከሶስት ሰዓት በላይ መፍጀቱን አቶ ንጋቱ ጨምረው ነግረውናል፡፡ አካባቢዉ በከተማ ደረጃ ለእሳት አደጋ ከተለዩ የገበያ ቦታዎች አንዱ ሲሆን በተደጋጋሚ የእሳት አደጋ አጋጥሞ በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

የገበያ ማዕከላቱ የተገነቡበት ግብዓትና የዉስጥ አደረጃጀቱና ስራዎች የሚከናወኑበት ሁኔታ እንዲሁም ለአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪዎች መግቢያ መንገድ ከአጋላጭ ሁኔታዎቹ የሚጠቀሱ ናቸዉ ተብላል።

በትግስት ላቀዉ

photo_2024-01-23_08-38-12

ጥር 14፤2016 – ታሪክ አዋቂው እውቁ ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

 

በኢትዮጵያ እግርኳስ ያለፉትን ሃምሳ አመታት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት በታታሪነት ፣ በታሪክ አዋቂነት እና ሊብሮ ጋዜጣን በማዘጋጀት እንዲሁም በብስራት ሬዲዮ መሴ ሪዞርት ፕሮግራም የሚታወቀዉ አንጋፋው ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ተሰምቷል።

ብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን የታላቁ የስፖርት ጋዜጠኛ ሕልፈተ ሞት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰቦቹ ለወዳጆቹ እና ለመላው የስፖርት ቤተሰብ መፅናናትን ይመኛል

ጥር 13፤2016 – የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልተቀበልከንም በማለት ግለሰብን ደብድበው ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረጉት የቀበሌ ፅህፈት ቤት ሰራተኞች በእስራት ተቀጡ

 

በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ደደር ወረዳ ቼካ ቀበሌ ከባለቤቱ የተላከለትን የእስር ማዘዣ አልቀበልም በማለቱ ደብድበው ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረጉት ግለሰቦች በእስራት መቀጣታቸውን የደደር ወረዳ ፖሊስ አስታውቋል።

አልየ ሃምዳ የተባለው ግለሰብ  ከባለቤቱ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሁለት ልጆቿን  ይዛ ከቤት መውጣቷን እንዲሁም የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡  ይሁን እና ባለቤቱ ከቤት ከወጣች በኋላ የገንዘብ ችግር ያጋጥማታል፡፡ በዚህም ሰዓት ንብረቴን ትካፈለኛለች በማለት ንብቱን ማሸሽ ፣ መሸጥ ፣ መለወጥ ጅምሮ እንደነበር የደደር ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር  ግዛቸው ተፈራ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በፍርድ ቤት የወጣውን የንብረት እግድ  የያዘ የትዕዛዝ  ደብዳቤ ለማድረስ የአካባቢው የጸጥታ አካላት የሆኑት አብዱልዓማን የሱፍ ፣ ጀማል አቡበከር ፣ ጃፋር ሶፊያን    ትእዛዙን ለማድረስ ወደ ተጎጂው መኖሪያ ቤቱ ያመራሉ  ። ነገር ግን ትዕዛዙን አልቀበልም በሚል በመካከላቸው ግጭት ይፈጠራል ።

ሶስቱ ግለሰቦች አልታዘዘንም በማለት ወደ ቀበሌ ጽ /ቤት ለመውሰድ ሲሞክሩ አልሄድም እንዳለቸው ቃላቸውን ለፖሊስ ሰጥተዋል።  የተፈጠረው ግጭት ከቃላት አልፎ ወደ ዱላ ይቀየር እና በያዙት ዱላ ጆሮ ግንዱን መተው እጅ እና እግሩን  አስረው ወደ  ቀበሌ ጽ/ቤት  ይወስዱታል፡፡

ወደ ቀበሌ ጽ/ቤት ሲደርስ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረ በመሆኑ ወዲያው ወደ ህይወት ፋና ሆስፒታል ይወስዱታል፡፡ ለሁለት ቀናት የህክምና ክትትል  ሲደግለት ቢቆይም ህይወቱ ማትረፍ አልተቻለም፡፡

ሶስቱ ግለሰቦችም የተሰጣቸውን ስልጣን በመጠቀም አላግባብ በኃይል በታገዝ መንገድ ሰው ለመያዝ በመሞከር እና በመደብደብ ወንጀል ዓቃቢ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው የምስራቅ ሀረረጌ  ዞን  ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ተከሳሾችን ጥፋተኛ በማለት እያንዳንዳቸውን በስምንት ዓመት ከስድስት ወር እስራት እና በአራት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ቅጣት የወሰነባቸው መሆኑን ኢንስፔክተር ግዛቸው ተፈራ  ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በኤደን ሽመልስ

photo_2024-01-22_18-36-12

ጥር 13፤2016 – ታዋቂዉ አሜሪካዊዉ ራፐር አፍሪካ ዉስጥ የሚገኙ ሰዎች ሙዚቃን በምን ቴክኖሎጂ ነዉ የሚሰሙት በማለቱ ከፍተኛ ትችት ተሰነዘረበት

 

ታዋቂው የዩናይትድ ስቴትስ ራፐር ሜክ ሚል በናይጄሪያ እና በደቡብ አፍሪካ ያሉ ሰዎች እንዴት ሙዚቃን እንደሚያዳምጡ በመጠየቁ ከፍተኛ ትችቱ በጥቁር አሜሪካዊዉ ድምጻዊዉ ላይ ተቀስቅሷል፡፡

“ብዙ ሰዎች የእኔን ሙዚቃ በደቡብ አፍሪካ ይጫወታሉ? ከጥቂት አመታት በፊት እዚያ ትልቅ ትርኢት እንደነበረኝ አስታውሳለሁ። በደቡብ አፍሪካ ያላችሁ ሰዎች ግን የኛን ሙዚቃ እንዴት ነው የምታዳምጡት? በየትኛው መድረክ ነው በተመሳሳይ ናይጄሪያ ውስጥ የምትገኙ ሰዎች ሙዚቃችንን በምንድን ነዉ የምታዳምጡት?” በማለት በቀድሞ ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ላ|ይ ሀሳቡን አስፍሯል፡፡

በጉዳዩ ላይ ብስጭት የተሰማቸዉ በርካታ አፍሪካውያን የድምጻዊዉን ፅሁፉ አላዋቂ እና ስድብ ሲሉ ተችተዋል። በራፐሩ ላይ ጹሁፉን ባጋራበት ፍጥነት ብዙም ሳይቆይ ትችት ያጋጠመ ሲሆን የመወያያ ርዕስ ሆነ ቀጥሏል።ተቺዎች እንደሚሉት የራፕሩ ጥያቄ አፍሪካ ሙዚቃን ለመስማት በቴክኖሎጂ የራቀች ነች የሚል ግምት እንዳለዉ ያሳያል ብለዋል፡፡

አንዳንድ አፍሪካውያን ለራፐሩ በሰጡት የአጸፋ ምላስ በዝሆን ኩንቢ እና በከተማ የድምጽ ማጉያ ሙዚቃን ያዳምጣሉ በማለት በቀልድ መልክ በራፐር ላይ አሾፈዋል።ድምጻዊዉ ሚክ ሚል ጥያቄውን ያቀረበው ሙዚቃው በአፍሪካ እንዴት እየተሰራጨ እንደሆነ ለመረዳት መሆኑን አስተባብሏል፡፡የእኔ ጥያቄ በአፍሪካ ውስጥ ሙዚቃዬን እንዴት እንደሚያዳምጡ እየጠየቅኩ ነበር፤ ምክንያቱም ንግዴን ማስፋት ስለምፈልግ እና የትኛውም የስራ ዉሎቼ በአፍሪካ የእኔን ስራ ለማሰራጨት ስላለኝ መብት አይነግሩኝም ብሏል፡፡

በመሠረቱ ጥያቄዬ የገንዘብ ነዉ፤ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የእኔ ስራዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ ግን በምን መድረኮች እንደሚሸጡ አላዉቅም ሲል የተሰነዘረበትን ትችት የሚያለዝብ አስተያየር ሰጥቷል፡፡በማለት እሁድ እለት ተናግሯል፡፡ራፐሩ ባለፈው አመት በጋና ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግስት ውስጥ የሙዚቃ ቪዲዮ በመቅረጽ ትችት ገጥሞት ነበር፡፡

በሚሊዮን ሙሴ

ጥር 13፤2016 – በአሜሪካ በከባድ አውሎ ንፋስ ከ90 በላይ ሰዎች ህይወታቸዉ ማለፉ ተሰማ

 

በዩናይትስ ስቴትስ ባለፈው ሳምንት በአስከፊ የክረምት አውሎ ንፋስ ከ90 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉ ተመዝግቧል።ሞት ከተመዘገበባቸዉ መካከል በቴነሲ ቢያንስ 25 እና በኦሪገን 16 ሰዎች ህልፈት ይፋ ተደርጓል፡፡ ከባድ የበረዶ አውሎ ነፋሱን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታዉጇል፡፡በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም በሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት ተቋርጦባቸዋል፡፡

በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የበረዶ ግግር ይቀላል ተብሎ ይጠበቃል።ሲቢኤስ ቴሌቪዥን ባገኘው መረጃ መሰረት ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ በአጠቃላይ 92 ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ የሞት አደጋዎች በመላ ሀገሪቱ ተመዝግበዋል።በቴነሲ እና በኦሪገን የሟቾች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም በሚሲሲፒ፣ ኢሊኖይ፣ ፔንስልቬንያ፣ ዋሽንግተን፣ ኬንታኪ፣ ዊስኮንሲን፣ ኒው ዮርክ፣ ኒው ጀርሲ እና ሌሎችም ከተሞች ላይ የሰዎች ህልፈት ተመዝግቧል።

ባለፈው ረቡዕ በፖርትላንድ ኦሪገን ውስጥ በአንድ ክስተት፣ ኃይለኛ ንፋስ የኤሌክትሪክ መስመር ወድቆ ይጓዙበት የነበረውን ተሽከርካሪ በመምታቱ ሶስት ሰዎች በኤሌክትሪክ አደጋ ህይወታቸዉ አልፏል። በተሽከርካሪው ውስጥ የነበረ ህፃን ከሞት ተርፏል።በሚሲሲፒ የአየር ሁኔታዉን ተከትሎ ባለሥልጣናቱ አሽከርካሪዎች “አስፈላጊ ከሆነ ብቻ እንዲያሽከረክሩ” ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡በሚሲሲፒ የሚገኙ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች ከክረምት እረፍት የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲዘገይ አድርገዋል፡፡

በክረምቱ የአየር ጠባይ ምክንያት በአሜሪካ የተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል በአብዛኛው ወደነበረበት የተመለሰ ቢሆንም፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ያለ ኃይል አቅርቦት ይቆያሉ፡፡እስከ እሑድ ምሽት ድረስ በኦሪገን 45ሺ ሰዎች ኃይል አጥተው ነበር። በፔንስልቬንያ፣ ካሊፎርኒያ፣ ኒው ሜክሲኮ እና ኢንዲያና ተጨማሪ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ተዘግቧል።

የብሔራዊ የአየር ሁኔታ አገልግሎት በዛሬዉ እለት ሰኞ ለአርካንሳስ እና ኦክላሆማ ከፍተኛ የበረዶ አውሎ ንፋስ ሊኖር ይችላል ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡

ጥር 13፤2016 – በሀረማያ ወረዳ በቧንቧ ውሃ ወረፋ ላይ በተፈጠረ ጸብ የሰዉ አካል ያጎደለችው ግለሰብ በእስራት ተቀጣች

 

በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ሀረማያ ወረዳ ውስጥ በቧንቧ ውሃ ወረፋ ላይ በተፈጠረ ጸብ በድንጋይ የአንዲትን ግለሰብን አራት ጥርስ ላይ ጉዳት ያደረሰችው ተከሳሽ  በእስራት መቀጣቷን  የሀረማያ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት  ወንጀል ምርመራ  ክፍል ሃላፊ ኢንስፔክተር ተስፋዬ አየለ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ  እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ተከሳሽ ናሂ አህመድ የውሃ ቧንቧ ወረፋ ይዘው ሲቀዱ ከነበሩ ሶስት ግለሰቦች ውስጥ ዘሃራ በከር  ጋር በወረፋ ምክንያት በመጣላታቸው ጉዳት ልታደርስባት መቻሏ ተረጋግጧል ።መጠኑ ትልቅ የሆነ ድንጋይ በመወርወር አራት ጥርሶቿ ላይ ጉዳት ያደረሰች ሲሆን አንደኛው ጥርስ በመውለቁም በአካል ማጉደል በቁጥጥር  ስር ውላለች።

በወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረትም ክስ ተመስርቶባታል ። የክስ መዝገቡ  በሰው እና በሰነድ ማስረጃ ተረጋግጦ  ጥፋተኛ መሆኗን የሀረማያ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አረጋግጧል ። በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በተከሳሿ ላይ የሁለት ዓመት እስራት እንድትቀጣ የወሰነባት መሆኑን ኢንስፔክተር  ተስፋዬ አየለ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ