photo_2024-06-28_10-05-13

ሰኔ  21፤2016 – በጋምቤላ ወደ ጤና ተቋማት ከሚሄዱ ነፍሰጡር ሴቶች 26 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ናቸው ተባለ

በጋምቤላ ክልል በእናቶችና ህፃናት ጤና ዙሪያ የሚከሰትን ህመምና ሞት ለመከላከል የአፍላ ወጣትነት እርግዝናን መታደግ እንደሚገባ የክልሉ ጤና ቢሮ ያስታወቀ ሲሆን ያለዕድሜ ጋብቻ፣ የአፍላ ወጣቶች እርግዝና እንዲሁም በኤች አይ ቪ ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱ ተገልጿል ።

በክልሉ ጤና ተቋማት ለእርግዝና ክትትል ከሚሄዱ ነፍሰጡር ሴቶች 26 በመቶ ከ18 አመት እድሜ በታች ናቸው የተባለ ሲሆን ይህም በሴት አፍላ ወጣቶች በሚፈጸም ያለዕድሜ ጋብቻና እርግዝና በእናቶችና ህፃናት ላይ ለሚስተዋለው ህመምና ሞት ከፍተኛ ድርሻ አለው ተብሏል ።

ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የሚያስከትለው የአፍላ ወጣትነት እርግዝና እንዲሁም በኤች አይ ቪ ኤድስ የመያዝ መጠን ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር የሚከሰቱ ችግሮች የመታደግ ጉዳይ የአንድ አካል ሃላፊነት ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላትና የእያንዳንዱ ሰው የተጠናከረ ተሳትፎን እንደሚጠይቅ ተጠቁሟል ።

ወጣቶችን  ከኤች አይቪ ኤድስና ካልታቀደ እርግዝና እንዲሁም ጥንቃቄ ከጎደለው ጽንስ ማቋረጥ እና የአዕምሮ እክል ከሚፈጥሩ ነገሮች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይገባል መባሉን የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ ይጠቁማል ።

በአበረ ስሜነህ

photo_2024-06-27_12-14-50

ሰኔ  20፤2016 – አሜሪካ ፥ የኬንያ መንግስት ከሰሞኑ አጋጥሞት የነበረዉን ተቃዉሞ ያበረደበትን መንገድ አደነቀች

አሜሪካ ፥ የኬንያ መንግስት ከሰሞኑ አጋጥሞት የነበረዉን ተቃዉሞ ያበረደበትን መንገድ አድንቃለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ  አንቶኒ ብሊንከን እና የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በአፍሪካ ስላለው ሁኔታም በስልክ ተወያይተዋል ተብሏል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኬንያውን ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶን ያለውን ውጥረት ለመቀነስ የወሰዱትን ርምጃ አድንቀዉ  ከተቃዋሚዎች እና ከሲቪል ማህበረሰቡ ጋር ለመወያየት ቃል ስለገቡ ፕሬዝዳንት ሩቶ አመስግነዋል” ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ጠቅሷል።

ፕሬዚዳንት ሩቶ በመላ ሀገሪቱ ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ያስነሳና ከ 20 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን አከራካሪ የግብር ረቂቅ ህግ አንፈርምም ማለታቸዉ ይታወሳል።

የኬንያ ወጣቶች ከሰሞኑ ይህን የግብር ረቂቅ ህግን በመቃወም ተከታታይ ሰላማዊ ሰልፎችን እንዳደረጉና ከፖሊስና ጸጥታ አካላት ጋር ግጭት ዉስጥ ገብተዉ እንደነበር ይታወሳል። ተቃዉሞዉ በፈጠረዉ ጫናም መንግስት ረቂቅ ህጉን ዉድቅ አድርጎታል። በተቃዉሞዉ ከጸጥታ አካላት ጋር ግጭት ዉስጥ ከገቡ ሰዎች ዉስጥ ከ 20 በላይ ያህሉ ህይወታቸዉ አልፏል።

በበረከት ሞገስ

photo_2024-06-26_15-24-21 (2)

ሰኔ  18፤2016 – በሞተር ሳይክል እየተንቀሳቀሱ ከግለሰቦች ሞባይል በመንጠቅ ሱቅ ውስጥ ሲያከመቹ የነበሩ 4 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አቶ ሱራፌል ቢያብል   የተባሉ የግል ተበዳይ በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 14   ዋና ስራ አስፈፀሚ  ሲሆኑ   ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም  በክፍለ ከተማው  ልዩ ቦታው ኢምፔሪያል አካባቢ እየተሰራ ያለውን  የኮሪደር ልማት ስራዎችን ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ እያደረጉ በነበሩበት ወቅት 2 ተጠርጣሪዎች በጥቁር ሞተር ሳይክል ኮድ 2,A 19,21,6 ደ.ሕ( ደቡብ ህዝብ)  መልኩ ጥቁር በሆነ 1ኛ ተጠርጣሪ  እያሽከረከረ ፣ 2ኛ ተጠርጣሪ ሞተር ሳይክል ላይ ከኋላ በመሆን ከግለሰቡ  ነጥቀው በፍጥነት እያሽከረከሩ ከአካባቢው ይሰወራሉ።

የግል ተበዳይ ወንጀሉ እንደተፈፀመባቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለገርጂ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ቀርበው ያመለክታሉ ። ፖሊስም የግል ተበዳዩን አቤቱታ በመቀበል  ባደረገው ክትትል ከሁለቱ ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ ከሌቦቹ የሚረከቡ 2 ተጠርጣሪዎች  በድምሩ  4 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ህግን በተከተለ አግባብ ባደረገው ብርበራ  ተጠርጣሪዎቹ ተከራይተው የሞባይል ጥገና የሚሰሩበት ሱቅ ውስጥ በተለያየ  ጊዜ ከተለያዩ ግለሰቦች ተቀምተው የተከማቹ 32 ስማርት ሞባይል ስልኮችን በኤግዚቢት ተይዘዋል ።

የንግድ ሱቆችን በመከራየት ወንጀል የሚፈፅሙ እና የሚያስፈፅሙ ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በቁጥጥር ስር እያዋለ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል ።

ሞባይል  ስልክ  ጠፍቶብኛል የሚል ግለሰብ በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ  በአካል  በመቅረብና ትክክለኛ ማስረጃ በማቅረብ ንብረቱን መውሰድ  እንደሚችል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

photo_2024-06-25_21-52-01

ሰኔ  18፤2016 – ተሽከርካሪ ሰርቃ የተሰወረችው ግለሰብ በሰዓታት  ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለች

ተጠርጣሪዋ የስርቆት ወንጀሉን የፈፀመችው ሰኔ  17 ቀን 2016 ዓ.ም  በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ቢጫ ፎቅ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡

በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ከቤተል አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው  በወቅቱ በግምት ከጠዋቱ 12:30 ሰዓት ገደማ የግል ተበዳይ በስፍራው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B32912 አ.አ የሆነ ተሽከርካሪያቸውን  መኖሪያ ቤታቸው በር ላይ ሞተር አስነስተው እያሞቁ የነበሩ ሲሆን ወደ ስራ ለመሄድ ጃኬት ሊደርቡ ወደ ቤት በገቡበት ቅስፈት ተሽከርካሪያቸውን ከቆመበት ቦታ እንደሌለ አረጋግጠው ለፖሊስ ሪፖርት ያደርጋሉ።  የኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አቤቱታው ከደረሰው ሰዓት ጀምሮ ተሰውሮ የነበረውን ተሽከርካሪ ለማግኘት ግማሽ ቀን በፈጀ ጠንካራ ክትትልና መረጃ የማሰባሰብ ሥራ ተጠርጣሪዋን ከነተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር አውሏታል።

ግለሰቧ የግል ተበዳይ ወደቤት በገቡበት ቅስፈት ተሽከርካሪውን አስነስታ ብትሰወርም  በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ  ልዩ ቦታው ሰሚት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በግምት ከቀኑ 9 ሰዓት ገደማ ከነተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር  ውላለች ። የተለያዩ ዘዴዎችንን በመጠቀም የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ የሁሉም ስው ኃላፊነት መሆኑን ያሳሰበው ፖሊስ
የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ መኪናቸውን አቁመውና የተሽከርካሪውን ቁልፍ በውስጡ ትተው በሚሄዱበት አጋጣሚ ለተመሳሳይ የስርቆት ወንጀል ሊዳረጉ ስለሚችሉ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ  የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል ።

photo_2024-06-25_10-52-56

ሰኔ  18፤2016 – የአዕምሮ ህመምተኛ በመምሰል እና ሌሎች ዘዴዎችን በመፈፀም የመኪና ዕቃ ሰርቀዋል የተባሉ ሁለት ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ ተያዙ

አንደኛው ግለሰብ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥሮ  በፍርድ ቤት በዋስትና የተለቀቀ መሆኑ ተነግሯል

የመኪና ዕቃ ስርቆትና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል ፖሊስ እያከናወነው ያለው ተግባር ምቹ ሁኔታ ያሳጣቸው አንዳንድ ወንጀል ፈፃሚዎች ከፖሊስ ጥርጣሬ ውጪ ለመሆን በማሰብ የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ ወንጀል ለመፈፀም እንደሚንቀሳቀሱ የአዲስአበባ ፖሊስ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ 02  ነዋሪ መሆኑን በኪሱ ውስጥ የተገኘው የነዋሪነት መታወቂያ የሚያስረዳው አንደኛው ተጠርጣሪ የአዕምሮ ህመምተኛ መስሎ እየተንቀሳቀሰ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ፊጋ አካባቢ መሲ ህንፃ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ  ቆሞ ከነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2- C34174 አ.አ ከሆነ ተሽከርካሪ ላይ የግራ ስፖኪዮ መስታወት ነቅሎ ለማምለጥ ሲሞክር እጅ ከፍንጅ እንደተያዘ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሲ.ኤም.ሲ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር  አባይ ወርቁ  ገልፀዋል፡፡

እራሱን  የአዕምሮ ህመምተኛ በማስመሰል ከተጠያቂነት ለማምለጥ ጥረት አድርጎ ያልተሳካለት ይኸው ግለሰብ  ሚያዚያ 3 ቀን 2016 ዓ/ም  በዚሁ ክፍለ ወረዳ 8 ሰሚት ሳፋሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የዋጋ ግምቱ 60 ሺ ብር የሚያወጣ የተሽከርካሪ ስፖኪዮ ሰርቆ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በፍርድ ቤት በመዋስትና መለቀቁን እና የተለያዩ ስሞችን እንደሚጠቀም ኢንስፔክተር አባይ አስረድተዋል፡፡

በተጠርጣው ላይ የምርመራ መዝገብ ተደራጅቶ ጉዳዩ በህግ አግባብ እየታየ እንደሚገኝም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና አንዲት ግለሰብ ቤተ ክርስቲያን የመጣች በመምሰል ነጠላ ለብሳ የመኪና ዕቃ ስርቆት ስትፈፅም እጅ ከፍንጅ ተይዛለች፡፡ ተጠርጣሪዋ ወንጀሉን ፈፅማለች የተባለው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ነው ብሏል ፖሊስ፡፡

በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ከቤተል አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው እሌኒ ታደሰ የተባለችው ግለሰብ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ/ም ከቀኑ 8 ሰዓት ገደማ  ቤተክርስቲያን የመጣች በመምሰል ነጠላ ለብሳ እየተንቀሳቀሰች  በአካባቢው ቆሞ ከነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ  2- C49561 አ.አ ከሆነ ተሽከርካሪ ላይ 16 ሺህ ብር የዋጋ ግምት ያለው ስፖኪዮ ነቅላ ለመሰወር ስትሞክር በፖሊስ አባላትና በህብረተሰቡ ትብብር እጅ ከፍንጅ ተይዛለች፡፡

photo_2024-06-24_06-48-38

ሰኔ  17፤2016 – በሩሲያ በቤተክርስቲያን እና ምኩራብ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ የ15 ሰዎች ህይወት አለፈ

ጥቃቱን አይኤስ መፈፀሙ ተነግሯል

በሩሲያ ሰሜን ካውካሰስ ሪፐብሊክ ዳግስታን ውስጥ በፖሊስ መኮንኖች፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ምኩራቦች ላይ በደረሰ ጥቃት የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፏል። በጴንጤቆስጤ የሩሲያ ኦርቶዶክስ በዓል ላይ ታጣቂዎች በደርቤንት እና ማካችካላ ከተሞች ላይ ጥቃት አድርሰዋል። ከሟቾቹ መካከል ቢያንስ 15 የፖሊስ አባላት፣ ቄስ እና የጥበቃ ሰራተኛ ይገኙበታል። ከአጥቂዎቹ መካከል ስድስቱ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ፖሊስ ሌሎችን እያደነ ይገኛል።

የአጥቂዎቹ ማንነት ባይታወቅም በዳጌስታን ከዚህ ቀደም ተከታታይ ጥቃቶች ሲደርሱ ቆይቷል።በእሁዱ ጥቃት ሁለት አብያተ ክርስቲያናት እና ሁለት ምኩራቦች ኢላማ ተደርገዋል። የዳግስታን ትልቋ ከተማ በሆነችው በማካችካላ አንድ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ተገድለዋል።15 ፖሊሶች በጥቃቱ መገደላቸውን የዳግስታን ሪፐብሊክ መሪ ሰርጌ ሜሊኮቭ ተናግረዋል። በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተለጠፉት ምስሎች እንዳሳዩት የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪዎች  ወደ ስፍራው ከመድረሳቸው በፊት ጥቁር ልብስ የለበሱ ሰዎች በፖሊስ ተሽከርካሪ ላይ ሲተኩሱ ያሳያል።

በቴሌግራም የመልእክት መላላኪያ መተግበሪያ ላይ ያለ ይፋዊ ባልሆነ ገፅ ማሽ ታጣቂዎች በደርቤንት በሚገኝ ህንፃ ውስጥ እንደነበሩ ተነግሯል። በሰርጎካል መንደር የፖሊስ መኪና ጥቃት ደርሶበታል።ዳግስታን በጣም ድሃ ከሆኑት የሩስያ ክፍሎች አንዷ ስትሆን አናሳ ክርስቲያኖች መኖሪያ ነች። እ.ኤ.አ. ከ 2007 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት የካውካሰስ ኢሚሬትስ የተባለ ቡድን በዳግስታን እና በአጎራባች የሩሲያ ሪፑብሊኮች በቼችኒያ ፣ኢንጉሼቲያ እና ካባርዲኖ-ባልካሪያ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወሳል።

በመጋቢት ወር በሞስኮ አቅራቢያ በሚገኘው ክሮከስ ከተማ አዳራሽ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ፣ የአይኤስ ቡድን ድርጊቱን ስለ መፈፀሙ ኃላፊነቱን ቢወስድም የመንግስት ባለስልጣናት ግን ለጥቃቱ ጥፋተኛ ሲሉ ጣታቸውን በዩክሬን እና በምዕራቡ ዓለም ላይ ቀስረዋል። በወቅቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ሩሲያ በአክራሪ የአሸባሪዎች ጥቃት ዒላማ ልትሆን አትችልም” ምክንያቱም “በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ልዩነት እና በሃይማኖቶች እና በጎሳ መካከል ያለውን አንድነት የሚያሳይ ልዩ ተምሳሌት ነው” ብለው አጥብቀው ተናግረው ነበር። ከሶስት ወራት በፊት የሩሲያ የሀገር ውስጥ ደህንነት አገልግሎት ኤፍ.ኤስ.ቢ በሞስኮ ምኩራብ ላይ ጥቃት ለማድረስ የአይኤስ ሴራ ማክሸፉን ማስታወቁ ይታወሳል።

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-06-21_12-39-21

ሰኔ  14፤2016 – ትራምፕ በአሜሪካ ኮሌጆች ተምረው ሊሚመረቁ የውጭ ሀገራት ተማሪዎች ግሪን ካርድ እሰጣለሁ አሉ

በኢሚግሬሽን ላይ ባላቸው ጠንካራ አቋም የሚታወቁት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ተምረው የሚመረቁ ሰዎች በአገር ውስጥ መቆየት መቻል አለባቸው ብለዋል።

የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2024ቱ ምርጫ ከተመረጡ በአሜሪካ ኮሌጆች ለሚገኙ የውጭ ሀገራት ምሩቃን ግሪን ካርድን እንደሚሰጡ የገለፁ ሲሆን ይሄም በኢምግሬሽንና ስደተኞች ላይ የነበራቸውን ጠንካራ አቋም መለሳለሱ ማሳያ ተብሏል።

ሐሙስ ዕለት ከሲሊኮን ቫሊ የቴክኖሎጂ ባለሀብቶች ጋር በፖድካስት ቃለ መጠይቅ ላይ ትራምፕ ተሰጥኦዎችን ወደ አሜሪካ ለማምጣት ቀላል ለማድረግ ቃል በመግባት ማንኛውም ከአሜሪካ ኮሌጅ የሚመረቅ ሰው በአገሪቷ መቆየት መቻል አለበት ብለዋል።

ትራምፕ ኦል-ኢን ፖድካስት ላይ “ከሃርቫርድ፣ MITና ሌሎች ታላላቅ ትምህርት ቤቶች ያፈሩዋቸውን ሰዎችን ስናጣ በጣም ያሳዝናል ብለዋል። ትራምፕ አክለውም “በዚህ አገር ለመቆየት እንድትችል እንደ ዲፕሎማህ አካል ግሪን ካርድ ወዲያውኑ ማግኘት ያለብህ ይመስለኛል” ሲሉ ትራምፕ ገልፀዋል።

ግሪን ካርድ ለግለሰቦች በአሜሪካ ውስጥ በቋሚነት የመኖር እና የመስራት መብትን እንዲሁም የሀገሪቱን የዜግነት ማግኛ መንገድን ያመቻቻል። በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አዲስ የዜግነት አመልካቾችን ይፈጥራል የተባለው የትራምፕ ሀሳብ በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነትና ቦታ እንዲያገኝ ካደረገው የኢሚግሬሽን ጠንካራ አቋም መውጣቱን ያሳያልም ተብሎለታል።

በአንድ ወቅት ስደተኞች “የአገራችንን ደም እየበከሉ ነው” ያሉት ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ትልቁ የሆነውን ሰነድ አልባ ስደተኞችን ለማባረር ቃል ገብተውም ነበር።

ማክሰኞ በዊስኮንሲን ውስጥ በተካሄደው የዘመቻ ዝግጅት ላይ ትራምፕ በዚህ ሳምንት ባወጁት ፕሮግራም ላይ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው የአሜሪካ ነዋሪዎች ባለትዳሮች ጨመ ከአገሪቱ መውጣት ሳያስፈልጋቸው ለቋሚ መኖሪያነት እንዲያመለክቱ ያስችላቸዋል። “አገራችን በወረራ ላይ ነች። አሁን ስለ ሌላ ነገር መነጋገር የለብንም ፣ ይልቁንም ወረራውን ለማስቆም መነጋገር አለብን ብለዋል።

የአገር ውስጥ ደህንነት ዲፓርትመንት ባወጣው ግምታዊ ቁጥር መሠረት 11 ሚሊዮን የሚሆኑ ስደተኞች ያለፈቃድ በአሜሪካ ይኖራሉ ብሎል። ትራምፕ በኦል-ኢን Podcast ላይ በታዩበት ወቅት ምንም እንኳን በቀደመው የስልጣን ዘመናቸው ግሪን ካርዶችን ለተመራቂ ተማሪዎች የመስጠት እቅድ የነበራቸው እንደሆነ ቢገልፅም የኮቪድ ወረርሽኙ ግን ግሪን ካርዶችን ለውጭ ተመራቂዎች የመስጠት እቅዱን እንዳስተጓጎለው ገልፀዋል።

በሚሊዮን ሙሴ

448825499_889948019816639_8271812621063267569_n

ሰኔ  14፤2016 – የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ 2 ሽልማቶችን አሸነፈ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ምርጥ የበረራ ላይ መዝናኛና የበረራ ላይ ገመድ አልባ ኢንተርኔት አገልግሎት ሽልማት አሸናፊ ሆነ፡፡

በዓመታዊው የ“ኤየርላይን ፓሴንጀር ኤክስፔሪያንስ አሶሴሽን“ (አፔክስ) በተባለ የ2024 የደንበኞች ምርጫ ሽልማት ላይ ዓየር መንገዱ ፥ የአፍሪካ ምርጥ የበረራ ላይ መዝናኛ እና የአፍሪካ ምርጥ የበረራ ላይ ገመድ ዓልባ ኢንተርኔት አገልግሎት ተሸላሚ መሆኑን አስታውቋል፡፡

አፔክስ ፥ የመንገደኞችን ድምፅ መሰረት በማድረግ ለዓየር መንገዶች ዕውቅና የሚሰጥበት መድረክ በአቪዬሽን ኢንደስትሪው ትልቅ ስፍራ ከሚሰጣቸው ሽልማቶች አንዱ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ዓየር መንገዶች ለሚያቀርቡት የላቀ የደንበኞች አገልግሎት ዕውቅና የሚሰጥበት መሆኑን ከአየር መንገዱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Capture

ሰኔ  12፤2016 – ለ ሶስት ወራት ጠፍታ የነበረችዉ ታዳጊ #ማህሌት ተክላይ ህይወቷ አልፎ ተገኘች

የ 16 ዓመቷ ታዳጊ ማህሌት ተክላይ መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ከመኖርያ ቤቷ ወደ ትምህርት በወጣችበት መታገቷን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን መዘገቡ አይዘነጋም።

ታዳጊዋ ከሶስት ወራት ፍለጋ በኋላ በዛሬው እለት ህይወቷ አልፎ መገኘቷን የአድዋ ከተማ ፖሊስ አዛዥ አቶ ተስፋዬ አማረ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን አረጋግጠዋል።

አቶ ተስፋዬ የታዳጊዋን ህልፈት ከማረጋገጣቸው ዉጪ ገዳይ ናቸዉ ተብለዉ የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉንም ለብስራት ተናግረዋል። ሆኖም ምን ያህል ሰዎች በቁጥጥር ስር ስለማዋላቸዉ ያሉት ነገር የለም።

ታዳጊዋ ማህሌት ተክላይ በእለቱ ከቀኑ 11 ሰዓት ከ 30 አካባቢ ነበር የቋንቋ ትምህርቷን ለመከታተል በወጣችበት የጠፋችዉ። ማህሌት ምሽቱን በተንቀሳቃሽ ስልኳ ወደ አባቷ በመደወል መታገቷን የሚያመላክት መረጃ ሰጥታ አጋቾቿም 3 ሚሊዮን ብር ጠይቀዉ እንደነበር ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን መዘገቡ አይዘነጋም።

የታዳጊዋ ማህሌት ተክላይ አስክሬን በእዛዉ አድዋ ከተማ ጭላ በተሰኘ አካባቢ መገኘቱንም ጣቢያችን ሰምቷል። ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያደርግም የአድዋ ከተማ ፖሊስ አዛዥ አቶ ተስፋዬ አማረ ጨምረው ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በበረከት ሞገስ

photo_2024-06-19_09-02-04

ሰኔ  12፤2016 – ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን አቀባበል የፒዮንግያንግ ከተማ አደባባይ በፊኛዎች እና ባንዲራዎች ማጌጡ ተሰማ

ከተማዋ ፑቲንን ለመቀበል ባደረገችው ዝግጅት የፒዮንግያንግ ማዕከላዊ አደባባይ በሰዎች ተጨናንቋል። በሰሜን ኮሪያ መስራች በኪም ኢል ሱንግ ስም በተሰየመው አደባባይ ላይ ፑቲን ሲደርሱ ከፍተኛ አቀባባል ዛሬ ማለዳ ተደርጎላቸዋል። መደበኛ ልብስ የለበሱ ልጆች ትናንሽ ፊኛዎችን ይዘው ታይተዋል። አደባባዩ ዙሪያ ያሉ ህንጻዎች በሩሲያ እና በሰሜን ኮሪያ ባንዲራ ያጌጡ ሲሆን የሁለቱን ሀገራት መሪዎች ምስል ተሰቅሎባቸዋል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በታጠቁ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚፈልጉ ፍንጭ ሰጥተዋል። ፑቲን ፒዮንግያንግ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በቀይ ምንጣፍ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ፑቲን ዛሬ እሮብ ማለዳ ጎህ ሳይቀድ በሰሜን ኮሪያ ዋና ከተማ ደርሰዋል። ሁለቱ መሪዎች ሲጨባበጡ እና አንዲት ሴት ለፑቲን ቀይ አበባ ስትሰጥ የሚያሳይ መረጃን የሰሜን ኮርያ መገናኛ ብዙሃን አጋርተዋል። ከዛም መሪዎቹ ወደ ኩምሱሳን ግዛት እንግዳ ማረፊያ ቤት ሲያቀኑ ታይተዋል።

የመንግስት የዜና ወኪል ኬሲኤንኤ የሁለቱ መሪዎች ስብሰባ በሰሜን ኮሪያ እና በሩሲያ መካከል ያለውን ወዳጅነት እና አንድነት “የማይበገር እና ዘላቂነት” ያሳየ ታሪካዊ ክስተት ነው ብሏል። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት “ዓለም አቀፍ ፍትህን ፣ ሰላምን እና ደህንነትን ለመጠበቅ እንዲሁም ለአዲሱ የብዝሃ-ዋልታ ዓለም ግንባታን ለማፋጠን እንደ ጠንካራ ስትራቴጂካዊ ምሽግ ሆኗል” ብለዋል ። ፑቲን ከ 24 ዓመታት በኋላ ወደ ሰሜን ኮሪያ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን አድርገዋል።

በየካቲት 2022 ሙሉ በሙሉ በዩክሬን ላይ ሩሲያ ወረራ ከጀመረች በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል። ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ የጦር መሳሪያ ዝውውር በመካከላችን የለም ብለው ቢክዱም ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ ግን ቃል ገብተዋል። ፑቲን እና ኪም ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በምስራቅ ሩሲያ በመስከረም 2023 ነበር። ሰሜን ኮሪያ በኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቿ እና በሚሳኤል ፕሮግራሞቿ ምክንያት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጥብቅ ማዕቀብ ለዓመታት ተጥሎባታል። ሩሲያም በዩክሬን ወረራ ምክንያት በዩናይትድ ስቴትስ እና በምዕራባውያን በኩል የተጣለባትን ማዕቀብ እየታገለች ትገኛለች።

ከሩሲያ እና ከሰሜን ኮሪያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት ቻይና የፑቲን እና የኪም ግንኙነት እንዳስደሰታት ገልፃለች። ፑቲን ከአንድ ወር በፊት ቻይናን መጎብኘታቸው ይታወሳል። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊን ጂያን የፑቲንን የፒዮንግያንግ ጉብኝት አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቤጂንግ “ሩሲያን ከባህላዊ ወዳጆቿ ጋር ያላት ግንኙነት ማሳደጓን በደስታ ትቀበለዋለች ሲሉ ተናግረዋል።

በስምኦን ደረጄ