photo_2024-06-13_09-09-58

ሰኔ 6፤2016 – እንቁላል ጣይ ዶሮ የሰረቀው ታዳጊ የ1 አመት ከ8 ወር እስር ተቀጣ

በምእራብ ጉጂ ዞን ሀምባላ ወረዳ ቢምቱ ከተማ  02 ቀበሌ ውስጥ አንድ ዶሮ ሲሰርቅ የተያዘው ግለሰብ ላይ የእስራት ቅጣት መወሰኑን የሀምባላ ፖሊስ አስታወቀ።

የሀምባላ ወረዳ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል እንደገለፀው ተከሳሽ ሮቤል ሽብሩ የተባለው የ18 አመት ታዳጊ ወጣት ሰኔ 3 ቀን 2016አ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ የአንድ ግለሰብን እንቁላል የምትጥል ዶሮ ሰርቆ በመውሰድ ሲሮጥ እጅ ከፍንጅ መያዙ ተገልጿል።

ግለሰቡ በፖሊስ የምርመራ መዝገብ በአስቸኳይ የተጣራበት ሲሆን የምርመራዉም መዝገብ ለአቃቢ ህግ ተልኳል።

አቃቢ ህግም ወድያውኑ ክስ መስርቶበት በአስቸኳይ ችሎት ውሳኔ እንዲሰጠው በመጠየቁ እንቁላል ጣይ ዶሮ የሰረቀው ታዳጊ ሮቤል ሽብሩ ሙሉ ለሙሉ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በ1 አመት ከ8 ወር እስራት እንዲቀጣ  የሀምባላ ወረዳ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማስተላለፉን የሀምባላ ወረዳ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን የላከው መረጃ ያመላክታል።

S117352748_g

ሰኔ 4፤2016 – ኤርትራ በሌሊት ብቻ የሚሰራ የኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት መጀመሯ ተሰማ

የሙሉ ሌሊት ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እስከ 105 ዶላር ድረስ መክፈል ይጠበቅባቸዋል ተብሏል

ኤርትረ በትናንትናው እለት የሌሊት ኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት መጀመሯን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል።

ኤርትራ በሌሊት ብቻ ይሰጣል ባለችዉ የኢንተርኔት አገልግሎት እጅግ ዉድ ሊሰኝ እንደሚችል የኢንተርኔት እና የኮምፒውተር ባለሙያ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል። በሰከንድ 512 ኪሎ ባይት ድረስ አገልግሎት ይሰጣል የተባለዉ ኢንተርኔት በቤት ስልክ መስመር የሚመጣ ሲሆን ተጠቃሚዎች ወደ ሞባይል እና ኮምፒውተሮቻቸዉ ማገናኘት እና መጠቀም ይችላሉ ተብሏል።

ኤርትራ በትናንትናው እለት ሌሊቱን ያስጀመረችዉ የኢንተርኔት አገልግሎት ባለሙያዎች ገለጻ ዘንድ ቀርፋፋ ነዉ የተሰኘዉን ነዉ።

ሁለት አይነት የኢንተርኔት ማስተላለፊያ መስመሮች ያሉ ሲሆን ኤዲኤስኤል (ADSL) በሲርናል ኢንተርኔት የሚደርስበት ሲሆን ቀርፋፋ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጥበትም ነዉ። በአንጻሩ በፋይበር የሚተላለፈዉ ኢንተርኔት በብርሃን አጋዥነት አገልግሎት የሚሰጥበት ሲሆን እጅግ ፈጣኑም እንደሆነ ባለሙያዉ ገልጸዋል።

ታድያ ኤርትራ አስጀመረችዉ የተባለዉ የኢንተርኔት አገልግሎት ኤዲኤስኤል (ADSL) የተሰኘዉን ነዉ። ይህ አሁንም በኢትዮጵያ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም ቀርፋፋዉ አገልግሎት መሆኑን ባለሙያዉ ገልጸዋል።

ከሌሊቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ ከ 512 እስከ 1 ሜጋባይት ድረስ በሰከንድ ኢንተርኔት የሚያስጠቅነዉን አገልግሎት ለማግኘት ኤርትራውያን 1575 ናቅፋህ ወይንም 105 የአሜሪካ ዶላር መክፈል አለባቸው ተብሏል።

የተለያዩ አገልግሎቶች ይሰጣሉ የተባለ ሲሆን ተጠቃሚዎች እስከ 10 ጊጋ ባይት ድረስ የሆነና ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎትን ማግኘት ካሻቸዉ ደግሞ 4200 ናቅፋህ ወይንም 280 የአሜሪካ ዶላር ከፍያ መፈጸም እንዳለባቸው ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ከተሰራጨው ማስታወቂያ ላይ መታዘብ ችሏል።

በበረከት ሞገስ

photo_2024-06-11_12-09-30

ሰኔ 4፤2016 – የማላዊው ፕሬዝዳንት የሀገሪቱን ምክትልፕሬዝዳንት ይዞ የጠፋውን አውሮፕላን ለማግኘት ድጋፍ ጠየቁ

የማላዊ ፕሬዝዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ ሰኞ እለት ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሎስ ቺሊማን እና ዘጠኝ ሌሎች ሰዎችን ይዞ የተሰወረዉን ወታደራዊ አውሮፕላን ለማግኘት መንግስታቸው የሀገሪቱን ጎረቤቶች እና የልማት አጋሮችን እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ፕሬዚደንት ቻኩዌራ ስለጠፋው አውሮፕላን መረጃ ለማግኘት መንግስታቸው የአሜሪካን፣ እስራኤልን፣ ኖርዌይን እና የእንግሊዝን መንግስታትን ማነጋገሩን ተናግረዋል።እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ የልማት አጋሮች ልዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም “አውሮፕላኑን በቶሎ የማግኘት አቅማችንን የሚያጎለብት” ድጋፍን በተለያዩ መንገዶች ሰጥተዋል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡“ይህ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ እንደሆነ አውቃለሁ። ሁላችንም እንደምንፈራ እና እንደሚያሳስበን እረዳለሁ። እኔም ያሳስበኛል።

ነገር ግን ይህ አዉሮፕላን ለማግኘት ምንም አይነት ሃብት እንደማልቆጥብ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ እና በህይወት የተረፉ ሰዎችን እንደምናገኝ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ምክትል ፕሬዝዳንቱን ያሳፈረዉ አዉሮፕላን ሰኞ እለት ከሀገሪቱ ዋና ከተማ ሊሎንግዌ ተነስቶ ወደ ሰሜናዊቷ የሀገሪቱ ከተማ ምዙዙ በማምራት ላይ የነበረ ሲሆን የሀገሪቱ የቀድሞ የፍትህ ሚኒስትር እና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ራልፍ ካሳምባራ የቀብር ስነስርዓት ላይ ለመታደም ዉጥን ነበራቸዉ፡፡

ከምክትል ፕሬዝዳንቱ በተጨማሪ በአውሮፕላኑ ውስጥ በርካታ የፓርቲያቸው ባለሥልጣናት ነበሩ።ምክትል ፕሬዝዳንቱን የያዘው አውሮፕላን መጥፋት በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት አዛዥ ከተነገራቸው በኋላ የማላዊው ፕሬዝዳንት ላዛረስ ቻክዌራ ወደ በውጭ ሊያደርጉት የነበረውን ጉዟቸውን ሰርዘዋል። የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ “የተረጋገጡ መረጃዎች በተገኙ ጊዜ ለሕዝቡ ይፋ ይደረጋል” ብሏል።የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄኔራል ቫለንቲኖ ፊሪ ለፕሬዝዳንቱ ክስተቱን ባሳወቁበት ጊዜ ለአውሮፕላኑ መሰወር ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዳልታወቀ ተናግረዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ወደ ፖለቲካው ዓለም ከመግባታቸው በፊት ዩኒሊቨር እና ኮካኮላን በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ውስጥ በከፍተኛ የመሪነት ቦታ ላይ ሠርተዋል።ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት የ51 ዓመቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ቺሊማ ደቡባዊ አፍሪካዊቷ አገር ማላዊ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ እያገለገሉ ነው።

በስምኦን ደረጄ

gggggggggggggg

ሰኔ 3፤2016 – በግድያ ወንጀል ተከሶ የፍርድ ቤት ውሳኔን ያገኘ ታራሚ የማረሚያ ቤት ፖሊስ የደንብ ልብስ አልብሰው ያስመለጡ የፖሊስ አባላት በእስራት ተቀጡ

በባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ መና 02 ቀበሌ ውስጥ ከሚገኘው ማረሚያ ቤት አስተዳደር በግድያ ወንጀል ተከሶ ውሳኔን ያገኘን ታራሚ የማረሚያ ቤት ፖሊስ የደንብ ልብስ በማልበስ ከማረሚያ ቤት እንዲወጣ ያደረጉ ሁለት የማረሚያ ቤት አባላት በእስራት መቀጣታቸውን የደሎ መና ወረዳ ፖሊስ አስታወቀ።

የደሎ መና ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ሀላፊ ም/ኢንስፔክተር ጫላ ተክሉ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቭዥን እንደገለፁት 1ኛ ተከሳሽ ም/ሳጅን ሰኚ ኑራ፣ 2ኛ ተከሳሽ ሳጅን ቃልኪዳን ሙልጌታ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የደሎ መና ማረሚያ ቤት አስተዳደር የፖሊስ አባላት የሆኑት ሁለቱ ተከሳሾች የተጣለባቸውን የሞያ ግዴታና ሀላፊነት ወደ ጎን በመተው የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 6:00 ሰዓት ላይ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኘው የማረሚያ ቤት አባላት የደንብ ልብስ በማልበስ ከማረሚያ ቤት እንዲወጣ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ሁለቱ የማረሚያ ቤት የፖሊስ አባላት በግድያ ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት የ21 ዓመት እስራት ከተፈረደበት ታራሚ አበበ አልዩን 47ሺ ብር በመቀበል በማረሚያ ቤቱ ሶስተኛ የጥበቃ ክፍል እንዲወጣ ማድረጋቸውን በማስረጃ መረጋገጡን ገልፀዋል።

ታራሚው በፈፀመው የግድያ ወንጀል ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም ተመዝግቦ የገባ ሲሆን በ4 ወሩ ሁለቱ የማረሚያ ቤት ፖሊሶች የማረሚያ ቤት አባላት የደንብ ልብስ አልብሰው እንዳስመለጡት ታውቋል።

የደሎ መና  ማረሚያ ቤት ፅ/ቤት የተፈፀመውን ድርጊት በምርመራ እና በክትትል ካረጋገጠ በኃላ በሁለቱ የማረሚያ ቤት የፖሊስ አባላቶች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲካሄድ ለደሎ መና ወረዳ ፖሊስ አስተላልፏል።

የደሎ መና ፖሊስ በሁለቱ የማረሚያ ቤት የፖሊስ አባላት ላይ የምርመራ መዝገብ አጠናቆ ለዓቃቢህግ ልኳል።አቃቢ ህግም የተሰጣቸውን የስራ ግዴታና ሀላፊነት ወደ ጎን በመተው ክስ የመሰረተ ሲሆን የተመሰረተውን ክስ ሲመለከት የነበረው የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለቱ የማረሚያ ቤት የፖሊስ አባላት የፈፀሙትን ወንጀል በዓቃቢ ህግ ሙሉ በሙሉ አረጋግጧል።

በዚህም 1ኛ ተከሳሽ ም/ሳጅን ሰኚ ኑራ በ3 ዓመት እስራት እና በ20ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ የተወሰነበት ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ ሳጅን ቃልኪዳን ሙልጌታ ደግሞ በ1ዓመት እስራት እና በ3000ሺ ብር መቀጮ እንዲቀጣ ውሳኔ መተታላለፉን ግንቦት 30 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ም/ኢንስፔክተር ጫላ ተክሉ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በምህረት ታደሰ

ሰኔ 3፤2016 – የ7 ዓመቷን ታዳጊ አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

በባሌ ዞን ጎሮ ወረደ ወልተኢ ቀበሌ ውስጥ የ7 ዓመቷን ታዳጊ ልጅ አታሎ በመውሰድ በጫካ ውስጥ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት የፈፀመው ግለሰብ በእስራት መቀጣቱን የጎሮ ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት አስታወቀ።የጎሮ ወረደ ፖሊስ ፅ/ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ሀላፊ ም/ኢንስፔክተር ፈቲሀ አህመድ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቭዥን እንደገለፁት አዳነ ሽመልስ የተባለው ግለሰብ መጋቢት 30 2016 ዓ.ም ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ወንጀሉን እንደፈፀመ ተናግረዋል።

የ7 ዓመቷ ልጅ ከህዝብ የቧንቧ ውሀ መጠቀሚያ ውሀ ለመቅደት ስትሄድ ማንም በስፍራው አለመኖሩን አይቶ ተሸክሟት ጫካ በመውሰድ አስገድዶ እንደ ደፈራት በማስረጃ መረጋገጡን ገልፀዋል።ህፃኗም ጥቃቱ እንደደረሰባት ወዲያውኑ በለቅሶ ለቤተሰቦቿ በማሳወቋ ቤተሰቦቿም ጉዳዪን ለፖሊስ በማሳወቃቸው ፖሊስ ተጎጂዋን የህክምና እርዳታ እና ምርመራ እንድታገኝ አድርጓል። እንዲሁም የድርጊቱን ፈፃሚ ከተሸሸገበት ቦታ ፈልጎ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልፀዋል።

የተፈፀመውን ድርጊት በህክምና እና በሌሎች ማስረጃዎች በማጠናከር የምርመራ መዝገቡን ፖሊስ ለአቀቢ ህግ አስተላልፏል።አቃቢ ህግም ከፖሊስ የተላከውን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረት ክስ መስርቷል።የተመሰረተውን ክስ ሲመለከት የቆየው የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሽ አዳነ ሽመልስ በ13 ዓመት እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ም/ኢንስፔክተር ፈቲሀ አህመድ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቭዥን ተናግረዋል።

በምህረት ታደሰ

photo_2024-06-10_13-42-28

ሰኔ 3፤2016 – እስራኤል ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን የጋዛ ሕንፃዎችን እንዳወደመች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ

የተባበሩት መንግስታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ እንደገለጸው ከጥቅምት 7 ጀምሮ በጋዛ ሰርጥ ከሚገኙት ሕንፃዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በእስራኤል ጥቃቶች ወድመዋል።የተባበሩት መንግስታት የሳተላይት ማእከል መረጃን በመጥቀስ በኤክስ ላይ ባሰፈረዉ መልዕክት “በጋዛ የደረሰው ውድመት ሊገለጽ የማይችል ነው” ሲል አስታዉቋል፡፡

“ፍርስራሹን ማጽዳት ዓመታት ይወስዳል። ከዚህ ጦርነት የስነ ልቦና ጉዳት መዳን ብዙ ጊዜ ይወስዳል” ሲል አክሎ የተኩስ ማቆም ጥሪ አቅርቧል።“ይህ መከራ ማብቃት አለበት” ሲልም አሳስቧል፡፡ በሌላ በኩል በእስራኤል መንግሥት ውስጥ ያለውን ጥልቅ ክፍፍል በግልጽ ያሳያል በተባለ ውሳኔ የአገሪቱ የጦር ካቢኔ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ የአስቸኳይ ጊዜ መንግስቱን ለቀዋል።

የሚንስትሩ ውሳኔ ከጋዛ ጦርነት በኋላ ባለው ዕቅድ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር የተፈጠረው ልዩነት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።ጋንትዝ እሑድ ዕለት በቴል አቪቭ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ሲያሳውቁ ውሳኔውን “ቀልል አልነበረም” ብለዋል።”እንደ አለመታደል ሆኖ ኔታንያሁ ወደ እውነተኛው ድል እንዳንቀርብ እየከለከለን ነው። ይህም ለቀጠለው ቀውስ ማሳያ ነው” ብለዋል።በአንዳንዶች የእስራኤል ቀጣዩ ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን ዕድል እንዳላች የሚነገርላቸው ጋንትዝ፤ ኔታንያሁ የምርጫ ቀን እንዲወስኑ ጠይቀዋል።

የሃመስ መሪ ሃኒዬ ለአልጀዚራ አረብኛ በሰጡት አስተያየት የእስራኤል ጦር ካቢኔ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ የስራ መልቀቂያ በተመለከተ “ጀልባው ከመስጠሟ በፊት ለመዝለል እየሞከሩ ነው” ብለዋል።የእስራኤል ባለስልጣናት የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸዉ የእስራኤል የፖለቲካ ስርዓት “በመውደቅ” ላይ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ሃኒዬ ተደምጠዋል።

ሃኒዬ በተጨማሪም ከኔታንያሁ ዉጪ እንደ አማራጭ የሚታዩት ጋንትዝ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ምንም ልዩነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።“ሁለቱም ጥፋት የሚፈልጉ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው” ሲሉ አክለዋል፡፡

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-06-10_09-02-03

ሰኔ 3፤2016 – በአውሮጳ ምክር ቤት ምርጫ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ተቀናቃኝ ከፍተኛ ድምፅ ማግኘታቸውን ተከትሎ ማክሮን በሀገር ውስጥ በፍጥነት ምርጫ እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተፎካካሪ ማሪን ለፔን ፓርቲያቸው በአውሮፓ ፓርላማ በተደረገው ምርጫ ትልቅ ድልን ማግኘታቸውን ተከትሎ በዚህ ወር መጨረሻ ፈጣን የፓርላማ ምርጫ እንዲደረግ ጠርተዋል። ተቃዋሚው ቀኝ አክራሪው ፓርቲ 32 በመቶ ድምፅ ከምርጫው ማግኘቱ የተገመተ ሲሆን ፤ ይህም ከፕሬዚዳንቱ ህዳሴ ፓርቲ በእጥፍ ይበልጣል።

የወቅቱ ፓርላማ መበተኑን ማክሮን ሲያበስሩ፣ የፓሪስ ኦሊምፒክ ጥቂት ሳምንታት ሲቀረው ሁለቱ ዙሮች ምርጫዎች በሰኔ 30 እና ሀምሌ 7 እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።  ማክሮን በፈረንሳይ የአውሮፓ ኅብረት ምርጫ ሂደት ድምፅ ከተዘጋ ምርጫዎች ከታወጀ ከአንድ ሰዓት በኋላ ከኤሊሴ ቤተ መንግሥት በቴሌቭዥን ቀርበው ይልደረጉት ንግግር አስደናቂ እና አስገራሚ ውሳኔ መሆኑን በርካቶች ገልፀዋል።
የ28 ዓመቱ የናሽናል ራሊ መሪ ጆርዳኖስ ባርዴላ ፕሬዚዳንቱ የፓርላማ ምርጫ እንዲጠሩ በግልፅ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ይህው ውሳኔ ከማክሮን ተሰምቷል። ፕሬዝዳንቱ ለፈረንሣይ መራጮች “መልእክትህን ሰምቻለሁ እናም ያለ ምላሽ እንዲተው አልፈቅድም” ብለዋል። ፈረንሳይ በእርጋታ እና በስምምነት ግልጽ የሆነ አብላጫ ድምጽ ያስፈልጋታል ሲሉ ተናግረዋል።

በአህጉሪቱ በሁሉም ቦታ ለቀኝ ዘመም ኃይሎች ስልጣንን መተው እንደማይችል ተናግረዋል ። የሁለተኛ ጊዜ የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ሁለት አመት ብቻ የቀራቸው ማክሮን በፈረንሳይ ፓርላማ አብላጫ ድምጽ የላቸውም፣ ምንም እንኳን ይህ የአውሮፓ ድምጽ በሀገራዊ ፖለቲካ ላይ ምንም አይነት ግንኙነት ባይኖረውም፣ በህዝብ ምክክር ስልጣን እንዲቀጥል በግልፅ ወስነዋል።

በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሁለት ጊዜ በማክሮን የተሸነፈችው ለፔን ፓርቲያቸው “ስልጣን ለመጠቀም ዝግጁ መሆኑን እና የጅምላ ስደትን ለማስቆም ቆራጥ ነን ” በማለት ወዲያው ምርጫው ይደረጋል መባሉን ተከትሎ ምላሽ ሰጥተዋል።

በስምኦን ደረጄ

ግንቦት 29፤2016 – ሩሲያ ምዕራባውያኑን ሀገራት ለመምታት የጦር መሳሪያ ልትሰጥ እንደምትችል ፑቲን አስጠነቀቁ

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሞስኮ የምዕራባውያን ሀገራት ኢላማዎች ለማጥቃት በማሰብ ሀገራትን ልታስታጠ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል። ፑቲን ይህንን የገለፁት ምዕራባውያን ለዩክሬን የረዥም ርቀት ጦር መሳሪያ መስጠታቸውን በመተቸት ነው። ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ዩክሬን ሩሲያን እንድታጠቃ የሚያስችላትን መሳሪያ ለመስጠት ውሳኔ ማሳለፋቸውን ተከትሎ ነው።

ፑቲን ለውጭ ሀገራት የመገናኜ ብዙሃን ጋዜጠኞች እንደተናገሩት እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ወደ “ከባድ ችግሮች” ሊመራ ይችላል ። ግዛታችንን ለማጥቃት እና ችግር የሚፈጥርብን የጦር ቀጠና ላይ እንዲህ አይነት መሳሪያ ማቅረብ ይቻላል ብሎ የሚያስብ ካለ ለምንድነው ተመሳሳይ የጦር መሳሪያን ለሌሎች የአለም ክልሎች የማቅረብ መብት የማይኖረን ሲሉ ተደምጠዋል። ሞስኮ የትኛዎቹን ሀገራት የጦር መሣሪያ ለማስታጠቅ እንዳሰበች ግን ፑቲን አልገለፁም።

ፑቲን ጀርመንን ለይተው የወነጀሉ ሲሆን ዩክሬን በቅርቡ በጀርመን ሰራሽ የረዥም ርቀት የጦር መሳሪያዎች በሩሲያ ውስጥ ኢላማዎችን ለመምታት መሞከሯን ተናግረዋል። በሩሲያ ግዛት ላይ ኢላማዎችን የሚመቱ ተጨማሪ ሚሳኤሎች ይኖራሉ እናም ይህ ደግሞ የሩሲያ እና የጀርመን ግንኙነትን ያበላሻል” ብለዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን በአሜሪካ በቀረበላት የጦር መሳሪያ ሩሲያን እንድትመታ ፍቃድ ሰጥቷታል ነገር ግን ጥቃቱ በካርኪቭ ክልል አቅራቢያ ብቻ የተገደበ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎርድ ካሜሮን በበኩላቸው እኛ የሰጠነውን የብሪታንያ የጦር መሳሪያ አጠቃቀምን የምትወስነው ዩክሬን ናት ብለዋል። በሩሲያ ግዛት ላይ የመምታት መብት እንዳላትም አክለዋል። የሰሜን ኮሪያ ሚሳኤሎች በዩክሬን ግዛት ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሆነም ኬየቭ ከዚህ ቀደም ሩሲያን መወንጀሏ ይታወሳል።የምዕራቡ ዓለም የስለላ ድርጅቶች ሩሲያ በግጭቱ ወቅት ኢራን ሰራሽ ድሮኖችን ስትጠቀም ቆይታለች ሲሉ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

በስምኦን ደረጄ

ግንቦት 28፤2016 – ጁዲ ቤሊንግሀም የደጋፊዎች የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ምርጫን ማሸነፏን ተከትሎ

“በመጀመሪያው ዓመቴ ይህንኑ በማሸነፌ በጣም ኮርቻለሁ እናም ለደጋፊዎቹ ክብር እንዳለኝ መግለጽ እወዳለሁ ፣ ጥሩ ዓመት ነበር ። በማድሪድ ቆይታዬ እናም የዚሁ ክለብ ቤተሰብ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ ”✨️

#BisratNews #BisratFm #BisratRadio #judebellingham

የብስራትን የተለያዩ ማህበራዊ ገጾች በመቀላቀል፤ ወቅታዊ መረጃዎችን እና ፕሮግራሞችን ይከታተሉ…

photo_2024-06-05_14-35-24

ግንቦት 28፤2016 – በቻይናው ባይትዳንስ የሚተዳደረው ቲክቶክ የሳይበር ጥቃት እንደተፈፀበት ተገለፀ

ቲክቶክ ጥቃቱ እንደ ሲኤንኤን ባሉ ብራንዶችና ታዋቂ ሰዎችን ላይ ያነጣጠረ ነበር  ብሏል

በቻይናው ባይትዳንስ ባለቤትነት የተያዘው የቪዲዮ ማጋርያ ገፅ ቲክቶክ እንደተናገረው “በጣም ውስን” የሆኑ አካውንቶች የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል ብሏል። እነዚህ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ አካውንቶች መለያቸውን ወደነበረበት ለመመለስ ከተጠቃሚዎች ጋር እየሰራ መሆኑንም ያከለው ቲክቶክ የሳይበር ጥቃቱን ፈጻሚዎች እና እንዴት እንደተፈፀመ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃን አላጋራም።

የሳይበር ጥቃት ከተፈፀመባቸው አካውንቶች መካከል አንዱ የአሜሪካው ቴሌቪዥን ጣብያ የሲኤንኤን መሆኑ ተገልፆል። የቲክቶክ ቃል አቀባይ “የመለያ መዳረሻን ወደነበረበት ለመመለስ እና የተሻሻሉ የደህንነት እርምጃዎችን በመተግበር ከሲኤንኤን ጋር በቅርበት እየሰራን ነው” ብለዋል ። አያይዘውም “የመድረኩን ታማኝነት ለመጠበቅ ቆርጠን ተነስተናል ለተጨማሪ ጥሰትና ጥቃት እንዳይፈፀም መከታተላችንን እንቀጥላለን ብለዋል።

ከሲኤነኤን በተጨማሪ ቲክቶክ የቴሌቭዥን ድራማዎች ኮከብ ፓሪስ ሂልተን አካውንትም ኢላማ እንደተደረገ የገለፀ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ችግር ግን አላጋጠመም ብሏል። በቲክ ቶክ ከ10 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት ሒልተን የመድረኩ ንቁ ተጠቃሚ ነው። ይህው ዜና የተሰማው ቲክ ቶክ በቻይናው ኩባንያ ካልተሸጠ በቀር በአሜሪካ ውስጥ እገዳ እየተጣለበት ባለበት ወቅት ነው።

መድረኩ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች አሉት፣ ነገር ግን የተጠቃሚዎች መረጃ ደህንነት እና ከመንግስት ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ጥያቄዎች አጋጥመውታል፤ ለአሜሪካ ምርጫም አዲስ የማህበራዊ ሚዲያ የጦር አውድማ ሆኖ ብቅ እያለ ነው።በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው በብሔራዊ ደኅንነት ምክንያት ሊያግዱት ሲጥሩ የነበረውን ቲክ ቶክን ተቀላቅለዋል። ቅዳሜ ዕለት አካውንታቸውን ከከፈቱበት ጊዜ አንስቶ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተከታዮችን ያፈሩት ትራምፕ “ከአሜሪካ ህዝብ ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ያለውን ማንኛውንም መሳሪያ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል”።

በአበረ ስሜነህ