የእስራኤል ፖሊስ በደቡብ እስራኤል ባደረገው ዘመቻ የ57 አመቷን የሃማስ መሪ እስማኤል ሃኒዬህ እህት መያዙን አስታዉቋል።የእስራኤል ዜጋ የሆነችው ሳባህ አብደል ሳላም ሃኒዬህ በቴልሼቫ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋለች ሲሆን የእስራኤል የደህንነት ኤጀንሲ ሺን ቤትን ያካተተ የምርመራ ዘመቻን መደረጉን ተከትሎ ነዉ።የሃኒዬ እህት መሆኗን ያረጋገጡት የፖሊስ ቃል አቀባይ “ከሃማስ ኦፕሬተሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና ከድርጅቱ ጋር በመገናኘት በእስራኤል ውስጥ የሽብርተኝነት ድርጊቶችን በማነሳሳት እና በመደገፍ ተጠርጥራለች” ብለዋል፡፡
በቤቷ ውስጥ “በእስራኤል መንግስት ላይ ከባድ የደህንነት ጥፋቶችን የሚያሳዩ ሰነዶች፣ ሚዲያዎች፣ ስልኮች፣ ሌሎች ግኝቶች እና ማስረጃዎች”መያዙን ፖሊስ አስታዉቋል፡፡በሌላ በኩል በፈረንሣይኛ ስያሜው ኤም ኤስ ኤፍ የሚታወቀው ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን፣ በአል አቅሳ ሆስፒታል የሚሠራው ስራ እሁድ ዕለት በእስራኤል የአየር ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ሥራ ማቆሙን እና ሽፋን እየፈለገ መሆኑን አስታዉቋል፡፡
“ቡድናችን በአቅራቢያው ከፍተኛ ፍንዳታ ሲሰማ ጥቃቱ ማለቁ እስኪረጋገጥ ድረስ በሆስፒታሉ ውስጥ የነበረንን ስራ አቁመናል” ሲሉ አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል።ኤም ኤስ ኤፍ “አፋጣኝ እና ቀጣይነት ያለው” የተኩስ አቁም ጥሪውን በድጋሚ አቅርቧል።በጥቃቱ ቢያንስ አራት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 17 ሰዎች ቆስለዋል።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስራኤል ወታደሮቿን እና ታንኮችን ከጋዛ አል-ሺፋ የህክምና ኮምፕሌክስ ዉስጥ አውጥታለች ብሏል።ሚኒስቴሩ በደርዘን የሚቆጠሩ አስከሬኖች ከፍርስራሽ ዉስጥ ተገኝተዋል ብሏል፡፡የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ ከአል-ሺፋ ሆስፒታል የተገኙት ምስሎች “አስፈሪ እና አስደንጋጭ ናቸው” ብለዋል።‹‹ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ኃላፊነታቸውን ይወጡ ይሆን? የታወቁ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች የዚህን ግልጽ የጦር ወንጀል ስፋት በተመለከተ አለም አቀፍ ምርመራን ይደግፋሉ ወይንስ መራጭ እና አድሎአዊ ባህሪው ይቀጥላል? በማለት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ በኤክስ ገጻቸዉ ላይ አስፍረዋል፡፡
የእስራኤል ጦር በበኩሉ ከጥቅምት 7 ጥቃት ወዲህ የተገደሉበት ወታደሮች ቁጥር 600 መድረሱን አስታዉቋል፡፡
በስምኦን ደረጄ







